የካቲት 18 ፣ 2015

በድርቅ የተጎዳው የቦረና ህዝብ በወረርሽኝ እና ረሀብ ስጋት ውስጥ ነው

City: Adamaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

በድርቁ ምክንያት የቦረና ዞን ከ33 ቢልየን ብር በላይ የተገመት ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን አሁንም የከፋ ረሃብ እና ወረርሺኝ የመከሰት ስጋት ውስጥ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ይገኛሉ

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በድርቅ የተጎዳው የቦረና ህዝብ በወረርሽኝ እና ረሀብ ስጋት ውስጥ ነው
Camera Icon

(ፎቶ- ዩኒሴፍ 2021 ቦረና)

መ“35 ከብቶች ነበሩን፣ አሁን ሁሉም ሞተዋል” የሚሉት የቦረና ዞን ነዋሪ እና የ8 ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጅሎ ሞሉ ናቸው። በአሁኑ ሰዓት የሚተዳደሩባቸውን ከብቶች በሞት በመነጠቃቸው ቤተሰባቸው የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ተቸግረው እንደሚገኙ አቶ ጅሎ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል። 

“ከኖርንበት የጠረሶ ቀዬ ወጥተን እርዳታ በቅርብ ይገኝበታል ወዳልነው ወላቃ ጡሬ መጥተናል” ያሉት የቦረና ነዋሪው አሁን በያቤሎ ከተማ አቅራቢያ በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ። 

ነዋሪዎች የቦረና ሰማይ ጥቁር ደመና ካየ ሶስት ዓመት ሞላው ይላሉ። ውሃ ለጠየቀ ወተት የሚያጠጣው የቦረና ህዝብ ዘንድሮ ውሃ አጥቶ  የወተቱን ጌቶችም ሞት ነጥቆታል። አቶ ጅሎን ጨምሮ ሌሎች የቦረና አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸው ሁሉ አልቀው አሁን ድርቁ ለራሳቸውና ለልጆቻቸው እንዳሰጋቸው ገልፀዋል።

ብዙዎች በድርቁ ሳቢያ ያጡትን ጥሪት ማመን ተስኗቸው ራሳቸውን ማጥፋታቸው ከአካባቢው ነዋሪዎች ይሰማል። በዱብሉቅ ወረዳ ያነጋገርናቸው የአዲስ ዘይቤ ምንጮች እንደገለፁት በዚህ ወር ብቻ 4 ሰዎች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ይገልጻሉ።

ምንም እንኳን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ በተደጋጋሚ ስልክ ደውለንላቸው ባይመልሱም ከሚዲያ ተቋም ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “ከድርቅም በላይ ረሃብ ይከሰታል ብለን እንፈራለን” ሲሉ ተደምጠዋል። ለዚህም በኮሚቴ ጥናት ተሰርቶ ለሚመለከተው አካል መቅረቡን ገልፀዋል። 

(ፎቶ- ዩኒሴፍ 2021 ቦረና)

በተከሰተው ድረቅ ከ3 ሚሊዮን በላይ እንስሳት ሲሞቱ 85 በመቶ የሚሆነው የቀንድ ከብቶች ናቸው ተብሏል። በርካታ ቤተሰቦች በመንግስት እርዳታ ነው የሚኖሩት የሚሉት የዞኑ አስተዳደር አቶ ጃርሶ ቦሩ ከዚህ ውስጥ 13 ሺህ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ያላቸውን ጥሪት ያጡ ናቸው ብለዋል። የቦረና ዞን አስተዳዳሪ እንደሚገልፁት በአካባቢው የፀጥታ ስጋት እና ተደጋጋሚ ግጭት መኖሩ በእርዳታ ስራው ላይ ስጋት የመፍጠር አዝማሚያ አለው።

ተጠባቂው የበልግ ዝናብ ከመደበኛው እጅግ ያነሰ እንደሚሆን ትንበያ እንዳለ የሚያትተው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሪፖርት ድርቁ በጠናባቸው በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ኩታ ገጠም አካባቢዎች 22 ሚሊዮን ሰዎች በስጋት ውስጥ ናቸው። የዓለም ምግብ ፕሮግራም በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ያስፈልገኛል ካለው 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር፣ 30 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ ለሚገኙ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተጎጂዎች እንደሆነ ይገልፃል።

ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ እና በቦረና ዞን አንድ ወረዳ ውስጥ የሚሰራ የጤና ባለሞያ እንደተናገረው ችግሮች ከቀን ወደ ቀን እየተባባሱ መሆኑን ያስረዳል። በዱብሉቅ ወረዳ፣ ከሜጋ እና ሌሎች የዞኑ አካባቢዎች የመጡ 8 ሺህ ቤተሰቦች በጠቅላላው ከ54 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ ያለው ባለሞያው “በአስደንጋጭ ሁኔታ የተፈናቃዮች ቁጥር ከቀን ቀን፣ ከወር ወር እየጨመረ ነው” ብሏል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ለዘመናት የተለፋበት ሀብትና ጥሪትን ማጣት፣ ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ መሆንና ሌሎችም የሚያሰጓቸው ጉዳዮች እንዳሉ የሚገልፁት ነዋሪዎች “በመንግስት ዘንድ ተፈናቃይ ናቸው ተብሎ ተቀብሎ ድጋፍ ለማድረግ ዳተኛነት መኖር ነገሮችን እጅግ እያወሳሰበ” እንደሆነ ተናግረዋል።

ለአረጋውያን፣ ለእርጉዝ፣ ለእናቶች እና ለህፃናት የሚደረገው ድጋፍ ምንም የለም የሚባል መሆኑን የሚገልፀው የህክምና ባለሞያው ወደፊት ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን ስጋቱን ይናገራል። የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ቢኖሩም የመድሃኒት እና የህክምና እቃ አቅርቦት እጥረት አለ ተብሏል። 

“ለመንግስት ከምንልከው ሪፖርት ተጨማሪ  ለረድኤት ተቋማት ትይዩ ሪፖርት እንልካለን” የሚለው ባለሞያው “መንግስት ያሉትን ተፈናቃዮች እንደሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ለመቀበል ባለመፈለጉ የረድኤት ድርጅቶቹ ተጎጂዎችን እንደሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ቆጥሮ ለመርዳት አስቸግሯቸዋል” ብሏል። 

ሞያሌ እና አካባቢው የኮሌራ ወረርሽኝ ስጋት ቀጠና ነው የሚለው ባለሞያው “ሞያሌ ለመጠለያ ካምፑ ካለው ቅርበት አንፃር ስጋታችን ለመጠለያው ነው” ይላል። የውሃ አቅርቦት ካለመኖሩና የስደተኞች የአኗኗር ሁኔታ የተጋላጭነት እድሉን እንደሚያሰፋውም ይናገራል። ከባለፈው ሀምሌ ጀምሮ በተለያዩ የባሌ እና ሊበን ዞኖች የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ወደሌሎች አካበቢዎች እየተስፋፋ ይገኛል።

አስተያየት