ኢትዮጵያ እና ኬንያ ከወራት በፊት የስንዴ ግብይት ለመፈፀም ስምምነት ተፈራርመው ነበር። ሪሊፍዌብ የተባለው በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ዳሰሳና ሪፖርት የሚያቀርበው ተቋም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ባወጣው መረጃ መሰረት በኬንያ ያለው የምግብ ዋስትና አሳሳቢነት እየጨመረ ሲሆን ካለፈው ዓመት ስጋቱ በ43 በመቶ መጨመሩን ገልጿል።
እ.አ.አ ይህ አኃዝ ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ ከነበረው የምግብ ዋስትና ስጋት የ43 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን በሚልዮን ከሚቆጠሩት ተጎጂዎች መካከል በግምት 774 ሺህ የሚሆኑት ድንገተኛ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ደረጃ ላይ ናቸው። በዚህም ሳቢያ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ችግር ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ።
በሪፖርቱ መሰረት ሁኔታዎች እየተባባሱ እንደሚሄዱ ብቻ ነው የሚጠበቀው። የዚህ ማሳያ ደግሞ ከመጋቢት እስከ ሰኔ 2023 ድረስ ሌላ 5.4 ሚሊዮን ኬንያውያን ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ስጋት ይገጥማቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን የሚገመቱት ለሞት በሚያደርሰው የድንገተኛ ደረጃ ይመደባሉ። አሁን ያለው አስጨናቂ ሁኔታ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ተጨማሪ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያስገድዱ መሆናቸውን የሪሊፍዌብ ሪፖርት አመላክቷል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአዲስ አበባ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ባደረጉት ውይይት ነበር የስንዴ አቅርቦት ስምምነቱ የተደረሰው። የኬንያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እንደገለፀውም ኢትዮጵያ ስንዴ ለኬንያ በወጪ ንግድ ለመላክ የተደረሰው ስምምነት በኬንያ የሚስተዋለውን የምግብ ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋት አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ነበር።
የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ መርሃግብር ማስጀመራቸውን ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያው ዘግቦ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ “መንግስት ስንዴን በስፋት በማምረት በአጭር ጊዜ ከውጭ የሚገባ ስንዴን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ችሏል” ያሉ ሲሆን ከሀገሪቱ ፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደሚኖር በመረጋገጡ በዚህ ዓመት ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ስራ በይፋ ተጀምሯል ብለዋል።
ይሁን እንጂ፤ ኢትዮ ኤፍ ኤም ከሰሞኑን የስንዴት ምርት እጥረት መፈጠሩን ዘግቦ ነበር። የዱቄትና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ ዋቢ ያደረገው ዘገባ “ስንዴ በአሁኑ ወቅት ኮንትሮባንድ ሆኗል፤ማንም እንደፈለገ መግዛትም ሆነ መሸጥ አይችልም” ብለዋል።
መንግስት ለወጪ ንግድ የሚሆን ስንዴ ለማግኘት ሲል ህብረት ስራ ማህበራት ብቻ እንዲገዙ የፈቀደ ቢሆንም ለዱቄት አምራቾችም በዩኒዮኖች በኩል ታገኛላችሁ ተብሎ 12 ባለሃብቶች ተመርጠው ወደ ስራ ገብተዋል። ዱቄት አምራቾች ግን ስንዴ ሊያገኙ እንዳልቻሉ የተገለፀ ሲሆን ይህ ችግር ከተፈጠረ 2 ወራትን አስቆጥሯል ተብሏል። ይሁን እንጂ አምራቾች በእጃቸው የነበረውን ስንዴ እየቆጠቡ ሲጠቀሙ ቆይተው አሁን ላይ ስራ እስከማቆም ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተገልጿል።
መንግስት በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ250 ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸውን በመጥቀስ 'ኢትዮጵያን ኤይድ' በሚል ስንዴ ለመለገስ እንደሚሰራ ተገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሺመልስ አብዲሳ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ዓመት 10 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ዝግጁ መሆኑን ገልፀው ነበር። ዘንድሮ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ስድስት አገራት ጋር የ3 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት ተፈርሟል ተብሏል።