የካቲት 28 ፣ 2015

ከዓላማው የመራቅና የመበተን ስጋት የተፈጠረበት የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር

City: Hawassaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

የዎህዴግ አመራሮች የቀድሞ እና አዲሶቹ በሚል ተከፋፍለው ህብረተሰቡን በመከፋፈል እና ፓርቲዉን በማፍረስ በሚል እርስ በእርስ እየተወነጃጀሉ ሲሆን ከአመራርነት ታግደዋል የተባሉ አመራሮች እግዳውን አልተቀበሉም

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከዓላማው የመራቅና የመበተን ስጋት የተፈጠረበት የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር

የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እዉቅና አግኝቶ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀስ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረዉ አለመግባባት ዎህዴግን እየሰነጠቀው ይገኛል።

ከሰሞኑ የዎሕዴግ ማዕከላዊ ምክር ቤት እንዳስታወቀዉ የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙሉጌታ አኔቦ የፓርቲዉን አሰራር በሚጥስ መልኩ መግለጫዎች በማውጣታቸው እና በህዝብ ዘንድ አመኔታ የሚያሳጡ ፅሁፎችን ፅፈዋል በሚል ከአመራርነት አግዷቸዋል። ማዕከላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀ መንበሩ የፓርቲዉን መተዳደሪያ ደንብ ጥሰዋል ያለ ሲሆን የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን ህልዉና አደጋ ላይ የሚጥሉ አሉባልታዎችንም አሰራጭተዋል በማለት ወቅሷቸዋል። 

አዲስ ዘይቤ ከዎህዴግ ምክትል ሊቀ መንበርነት ተነስተዋል የተባሉትን አቶ ሙሉጌታ አኔቦን ባነጋገረችበት ወቅት አሁንም በስራ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል። “የተላለፈዉን እግድ በተመለከተ የደረሰኝ ደብዳቤ የለም፣ ህጋዊ የሆነ ማህተም የለዉም ዉሳኔዉ ተቀባይነት የለዉም ህገ ወጥ ነዉ" ሲሉም ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

(አቶ ጎበዜ ጎአ- የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር)

ዎህዴግ ድርጅታዊ ዓላማዉን በመተዉ አሁን ላይ ለግል ጥቅማቸዉ በሚሰሩ ግለሰቦች ተከቦ ይገኛል የሚሉትና ህጋዊ የእግድ ደብዳቤ አልደረሰኝም ያሉት ምክትል ሊቀ መንበሩ “ከሁለት ዓመት ወዲህ በፓርቲዉ የአሰራር ግልፀኝነት ባለመኖሩ በአመራሮች መካከል ከፍተኛ ክፍፍል እየተፈጠረ” እንደሚገኝ ገልፀዋል። 

የዎሕዴግ ማዕከላዊ ምክር ቤት ያሳለፈዉ ዉሳኔ የስራ አስፈፃሚዉ ባልተገኘበት እና ጉዳዩ የሚመለከተዉ ሰዉ ባልቀረበበት ከአመራርነት መነሳቱን የሚገልፀዉን የማህበራዊ ሚዲያ ፅሁፍ “አሉባልታ” ነዉ የሚሉት አቶ ሙሉጌታ አኔቦ “በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 13 ንዑስ አንቀፅ 2 (መ) መሰረት “ለማዕከላዊ ምክር ቤቱ የቀረቡ አጀንዳዎችን መርምሮ ግለሰብ ከሆነ በአካል ቀርቦ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና ሲያምኑበት ነዉ የሚያግዱት” እንደሚል አስታውሰዋል። ነገር ግን ምክትል ሊቀ መንበሩ “እኔ ባልተገኘሁበት የተወሰነ ነው” ብለዋል።

አሁን ላይ የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በሁለት ሊቀ መንበሮች እንደሚመራ አዲስ ዘይቤ ሰምታለች። ከምስረታዉ ጀምሮ በሊቀ መንበርነት እየሰሩ የሚገኙት አቶ ተክሌ ቦረና እንዲሁም በጥር ወር 2014 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ፓርቲው ባካሄደዉ አስቸኳይ ስብሰባ ሊቀ መንበር ሆነዉ የተሾሙት አቶ ጎበዜ ጎአ ፓርቲዉን እየመሩ ይገኛሉ። ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑትን እና ህጋዊ እግድ አይደለም በሚል በስራቸው ላይ የቀጠሉትን አቶ ሙሉጌታን ያሰናበቱት እኚሁ ሊቀ መንበር አቶ ጎበዜ ጎአ ናቸው።

(አቶ ተክሌ ቦረና- የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር)

በሁለቱ አመራሮች የሚዘወረዉ ዎህዴግ ፓርቲ በሁለት ጎራ የተከፈለ የስራ ሂደት እንደፈጠረ ከምስረታው ጀምሮ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ተክሌ ቦረና ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። “አዲስ አመራሮች ከመጡ ወዲህ በፓርቲዉ ዉስጥ ጤናማ የሆነ ስራ ሂደት አይታይም፤ ቀድሞ ይዞት የነበረዉ ዓላማ አሁን የለም ማለት ይቻላል። ድርጅታዊ፣ ህዝባዊ እና ሀገራዊ ዓላማዉን በመልቀቅ ከግል ጥቅም ጋር የተሳሰረ ሆኗል” የሚሉት ሊቀ መንበሩ አቶ ተክሌ ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርጉት ሌላኛውን ሊቀ መንበር አቶ ጎበዜ ጎኣን ነው።  

ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ፓርቲዉ ግምገማና ዉይይት አድርጎ አለማወቁ፣ የድርጅቱ ወጪ እና ገቢ መጠን ኦዲት እንዲደረግ አለመፈቀዱ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ድርጅቱ ዉስጥ ያለዉን አለመግባባት ስር እንዲሰድ ማድረጋቸውን የፓርቲው አባላትና አመራሮች ይገልፃሉ። ይህን በሚመለከት አዲስ ዘይቤ ለዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ጎበዜ ጎኣ በእጅ ስልካቸዉ በተደጋጋሚ በመደወል ለማግኘት ያደረገችዉ ጥረት አልተሳካም። 

ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ የፓርቲዉ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አኔቦ እንደሚሉት “ፓርቲው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በቆመለት ዓላማ እየሰራ የሚገኝ ቢሆንም አሁን በአዲሱ አመራሮች አማካኝነት የግል ጥቅም ተጭነዉበት ህብረተሰቡን በመከፋፈል ዘመቻ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፣ ይህም በቀጥታ ፓርቲዉን የማፍረስ ዓላማ ያነገበ” መሆኑን ያስረዳሉ። 

የፓርቲዉን ቀጣይነትን አስመልክቶ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አመራሮቹ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዉን የሚመለከቱ መግለጫዎች እንዲሁም ሌሎች በጋራ የሚሰሩ ተግባራቶች በሁለት ቡድን ተከፍሎ እየተሰራ ቢገኝም የተፈጠሩ ችግሮች እንዳይቀጥሉ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የተጀመሩ ሂደቶች መኖራቸው ታውቋል።

አስተያየት