ታህሣሥ 13 ፣ 2014

የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግሥት ላይ የተጋረጠው የመፍረስ አደጋ

City: Gonderማህበራዊ ጉዳዮችቱሪዝም

ግንቡ የተሠራው ከ300-400 ዓመታት በላይ በኖረ የድንጋይ ካብ ሲሆን በዋናነት ድንጋይ፣ ኖራና እንጨት ለግንባታ ጥቅም ላይ ውለዋል።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግሥት ላይ የተጋረጠው የመፍረስ አደጋ
Camera Icon

photo:getahun asnake

ጥቂት ስለ ፋሲለደስ ቤተመንግሥት

የአፄ ፋሲለደስ ቤተ-መንግሥት የሚደነቅ የኪነ-ሕንጻ ጥበብ ያለው ኢትዮጵያዊ ቅርስ ነው። ለ200 ዓመታት የኢትዮጵያ መናገሻ በነበረችው፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ፋሲለደስ እንደተቆረቆረች በሚነገርላት ጎንደር ከተማ ይገኛል። (ከፋሲለደስ ንግሥና 300 ዓመታት ቀድማ እንደተቆረቆረች የሚናገሩ የታሪክ አዋቂዎችም አሉ) በሚዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ላይ በ1979 ዓ.ም. የሰፈረው የአፄ ፋሲለደስ ቤተ-መንግሥት 70ሺህ ስኩዌር ሜትር የሚሸፍን የመሬት ይዞታ አለው። ፋሲል ግቢ ወይም ነገሥታት ግቢ በ1628 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን ምሽጎችንና ቤተ-መንግሥት የያዘ ነው። ቤተ-መዛግብት፣ የአፄ ፋሲል መዋኛ፣ ቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ራስ ግምብና ደረስጌ ማርያምን አቅፏል። በተጨማሪም 9መቶ ሜትር ርዝመት ያለው የግቢው አጥር የቅርሱ አንድ አካል ነው። 

ግንቡ የተሠራው ከ300-400 ዓመታት በላይ በኖረ የድንጋይ ካብ ሲሆን በዋናነት ድንጋይ፣ ኖራና እንጨት ለግንባታ ጥቅም ላይ ውለዋል። በአፄ ፋሲለደስ ግንብ ውስጥ ያሉትን ቤተ መንግሥቶች ልዩ የሚያደርጋቸው እያንዳንዱ ነገሥታት የራሳቸውን አሻራና ታሪክ ለትውልድ ትተው ማለፋቸው ነው። አፄ ፋሲለደስ የመጀመሪያውንና ታላቁን ግንብ ያሰሩ እንጂ፣ ከእርሳቸው በኋላ የተነሱት ነገሥታትም ለ220 ዓመታት የየራሳቸውን ሕንጻ በመስራት ቦታው በቅርስ እንዲዳብር የድርሻቸውን አዋጥተዋል።

ፋሲል ግቢ፣ የውሃ እጥረት እንዳይገጥመው በማሰብ የተመሰረተው አንገርብ እና ቀሃ በተሰኙ ሁለት ምንጮች መካከል ነበር። ከግቢው በስተደቡብ የጎንደር አደባባይ ሲገኝ ቦታው ለገበያ፣ ለአዋጅ መንገሪያ እና ለወንጀለኛ መቅጫ አገልግሏል። በአሁኑ ወቅት የጎንደር ከተማ የሕዝብ መናፈሻ ነው። ማቀባበያ የሚሰኘው የግቢው አጥር ግምብ በዙሪያው 12 በሮች አሉት። በሮቹ ግልጋሎታቸውን የሚወክሉ ስያሜ ነበሯቸው። አንዳንዶቹ በሮች ከውጪኛው ዓለም ጋር የሚገናኙት በትላልቅ ድልድዮች ነበር። ምንም እንኳ አብዛኞቹ የግቢው ቤቶች በጦርነትና በእሳት ቢወድሙም ዋና ዋናዎቹ ሕንጻዎች ግን እስከ አሁኑ ዘመን ዘልቀው ይታያሉ።

ከእነዚህ ጉልህ ሕንጻዎች መካከል የፋሲለደስ ግምብ፣ ትንሹ የፋሲል ግምብ፣ የታላቁ ኢያሱ ግምብ፣ የዳዊት ፫ኛ ዙፋን ቤት፣ ምንትዋብ ግምብ፣ የምንትዋብ መዋኛ፣ የፈረሶች ቤት፣ የፈረሰኞች አለቃ ቤት፣ አንበሶች ቤት፣ የባካፋ ግምብ፣ የባካፋ ሰገነት፣ የቀዳማዊ ዮሐንስ ጽሕፈት ቤት፣ ዮሐንስ ቤተ-መጻሕፍት፣ አዋጅ መንገሪያን፣ ክረምት ቤት፣ ቋል ቤት (የሰርግ ቤት) እና ግምጃ ቤት ማርያም፣ አጣጣሚ ሚካኤል የሚሰኙ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል። በተጨማሪ ከፋሲል ግቢ ወጣ ብሎ በስተሰሜን ራስ ግምብ ይገኛል።

የአሁን ገጽታው

በጎንደር አስጎብኚዎች ማኅበር አስጎብኚ የሆነችው ዘነብ ጥላሁን “የፋሲል ግንብ የታሪካዊነቱን፣ የአስደናቂነቱን እና የዓለም ቅርስነቱን ያህል እየተጎበኘ አይደለም” ትላለች። ዘወትር በተመለከተችው ጊዜ ታሪክ ያላቸው፣ ታሪክ የሰሩ ታላለቅ ህዝቦች እንደነበሩ እንደምታስታውስ የምትናገረው ዘነብ ትኩረት ተሰጥቶች አስፈላጊው ጥገና እና እንክብካቤ ስላልተደረገለት እንዲሁም አግባብነት በጎደለው አጠቃቀም ምክንያት የቀድሞ ይዞታውን እያጣ እንደሚገኝ መታዘቧን ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

ፎቶግራፍ ለመነሳት እድሜ የተጫነው ቅርስ ላይ የሚወጡ ሰዎች፣ በሰርግ ሥነ-ስርአት ምክንያት የሚፈጠር ግርግር እና ጭፈራ፣ የሙዚቃ ቪድዮ እና ሌሎች ፕሮግራሞችን የመቅረጽ መርሃ-ግብሮች፣… አግባብነት በሌላቸው አጠቃቀሞች ውስጥ የተካተቱ ናቸው። "ቤቶቹ በማንኛውም ሰዓት ሊደረመሱ ይችላሉ" የምትለው አስጎብኚዋ የቤቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ መቆም እንደሚገባቸው ታምናለች።

የጥናት ወረቀታቸውን በቅርሱ ላይ ለመስራት በተደጋጋሚ እንደጎበኙት የሚናገሩት አቶ ጌታሁን ሥዩም በበኩላቸው ቅርሱን የወዳጅ ያህል እንደሚያውቁት ይናገራሉ። “ያለ በቂ ጥናት የሚካሄዱ ጥገናቶች በቅርሱ ላይ ችግር ሲያስከትሉ ተመልክቻለሁ። ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትኩረት አላገኘም” የሚል ሐሳባቸውን አጋርተውናል።

የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር አስተዳደሪ አቶ ጌታሁን ሥዩም በቅርሱ ላይ የተከሰተውን ችግር እንዲህ አብራርተዋል። “በቅርሱ ጣርያ ላይ ከሚታዩ ችግሮች በተጨማሪ ግድግዳዎች ተሰነጣጥቀው ነበር። የመንሸራተትና የመዝመም እክሎችም ገጥመውት ነበር። በአእዋፋትና በእፅዋት ንክኪ የተነሳ ተሸርሽሮም ነበር። ካቦቹም ወዳድቀው የነበር” ያሉ ሲሆን አሁን የጥገና ሥራ ተሰርቶ ከበፊት የተሻለ ሁኔታ ላይ ቢገኙም በቂ አይደለም ብለዋል።

የዳዊት ቤተ-መንግሥትና የአፄ ባካፋ ቤተ-መንግሥትም እንዲሁ አደጋ ላይ እንደሚገኙ ሌሎችም በርካታ ስንጥቆች እንዳሉባቸው ገልፀዋል። በአንድና በሁለት ሴንቲ-ሜትር ይለካ የነበረው ስንጥቅ አሁን ወደ 5 ሴንቲ ሜትር የሰፋ ቢሆንም የተቻለንን እየጠገንን እንገኛለን ብለዋል።

አቶ ጌታሁን ስዩም አክለውም “በምስጥና በፈንገስ ምክንያት የእንጨት አካሎቻቸው እየተበሉና እየበሰበሱ ይገኛሉ። አስፈላጊው ጥገና ካልተደረገ የመውደቅ ወይም የመደርመስ አደጋ ማጋጠሙ ጥርጥር የለውም። የመኪና ንዝረትና ግጭትም ቅርሶቹን ይፈታተኗቸዋል” ብለዋል።

አቶ ጌታሁን መፍትሔውን አስመልክቶ ሲናገሩ “ቅድሚያ የሚሰጠውን መለየት፣ ለቅርሱ ኃላፊነት ወስዶ የሚሠራን ሰው መመደብ፣ መገምገምና ክትትል ማድረግ ይገባል። በቂ በጀት መመደብም ከመንግሥት ይጠበቃል” ይላሉ። እንደ ቅርስ አስተዳደሩ ማብራሪያ የቅርሶቹ የጉዳት መጠን በጥናት ታውቆ በቅርሱ አካባቢ የከባድ መኪኖችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በየዓመቱ ከ1 ሚሊዮን ብር ያላነሰ በጀት ይመድባል። ከሌሎች ድጋፍ ሰጪዎች ጋር በጋራ በመሆንም ቅርሱን ከአደጋ ለመጠበቅ እየተሠራ እንደሆነ አቶ ጌታሁን ገልፀዋል። በተጨማሪም ማኅበረሰቡ የሚሳተፍበት 6122 የተሰኘ እርታ የማሰባበቢያ ቁጥር መዘጋጀቱን ነግረውናል። ማንኛውም የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ 6122 ላይ ok ብሎ በመላክ ለቅርሱ ጥገና የሚውል እርዳታ ለማበርከት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ቤተ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያሉት ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ንጽህናቸው ተጠብቆ በጥንቃቄ እየተያዙ እንዳልሆነ በማንሳት ቅርሱ አደጋ ላይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። 

አስተያየት