የድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 520 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ድሬደዋ ከመሀል ከተማ በስድስት ኪ.ሜ. ርቀት ከከተማዋ በስተምስራቅ ለገሐሬ ፈሳሽ ወንዝ ዳር ይገኛል። ኩባንያው በጣሊያን ወረራ ወቅት በ1939 እ.ኤ.አ ተቋቋመ። ከ5 ዓመታቱ ጦርነት በኋላ ጣሊያን ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ ሲወጣ በ1943 እ.ኤ.አ በወቅቱ ለነበሩ ባለሀብቶች ተሸጠ። “የኢትዮጵያ ጥጥ ኩባንያ” በሚል ስያሜ በአንድ ሚልየን አምስት መቶ ሺህ ብር የምስራቅ አፍሪካ ሽልንግ ካፒታል አክስዮን ተቋቋመ። በአክስዮን መልክ የተወራጀውን የሽርክና ፋብሪካ ገዝተው ካቋቋሙት ባለሀብቶች መካከል ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እና ቤተሰቦቻቸው፣ ሳቢያን ዩቲሊቲ ኮርፖሬሽን የተባለ የግል ኩባንያ ዋናዎቹ ናቸው። ሌሎች ኢትዮጵያዊያን፣ ግብፃውያንና፣ እንግሊዛውያን ባለሀብቶችም ነበሩበት።
ደርግ ሥልጣኑን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ “የኢትዮጵያ ጥጥ ኩባንያ” በቦርድ ሲመራ ቆይቷል። በዚህ ወቅት 9,240 እንዝርት ያለው አንድ የፈትል ክፍል፣ 390 የሸማኔ መኪና ያለው አንድ የሽመና ክፍልና ሁለት ባለ 300 ኪሎ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ባለው ጄኔሬተር በመጠቀም የአንድ ፈረቃ ስራ ይከናወን ነበር።
ከ1963 እ.ኤ.አ ጀምሮ በወቅቱ በጨርቃ ጨርቅ ቴክኖሎጂ እድገትና ስልጣኔ የወቅቱ መሪ የነበረችው ጃፓን ዜጎች ሽርክናውን ተቀላቀሉ። ኩባንያውን በራሳቸው አመራርና አሰራር ለወጡት። ፋብሪካውን ከነ ሰራተኛው በአለበት ደረጃ ተረከቡ። “የኢትዮጵያ ጥጥ ኩባንያ”ም “የድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ” የሚል ስያሜውን ያገኘው በዚያን ወቅት ነው። ኩባንያው በአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግስት ከ35 ዓመታት በላይ በግል ይዞታ ስር ቆይቶ ወታደራዊው ደርግ የሶሻሊዛምን መመሪያ በመተግበር የግል ንብረቶችን ወደ መንግሥት ባዞረበት ወቅት ይህ ግዙፉ ፋብሪካ የመንግስት ሆነ።
ፋብሪካውን 60ኛ ዓመት አስመልክቶ በታተመው መጽሔት እንደሰፈረው የበድሬዳዋ ከተማ የድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ለማቋቋም ምክንያት የሆነው የከተማዋ አቀማመጥ ነው። ድሬደዋ ከጅቡቲ ወደብ እና ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ የባቡር ሐዲድ ባለቤት መሆኗ፣ ለፋብሪካው አስፈላጊ የሆነ ግብዓትም ሆነ መለዋወጫ ዕቃዎችን ወጪ በቆጠበ መንገድ ለማጓጓዝ፣ ለምርት ሂደት አስፈላጊ የሆነ የውሀ ክምችት ያላት መሆኑ፣ ለጨርቃ ጨርቅ ምርት አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ የሆነው የማይለዋወጥ የአየር ንብረት መኖሩና እነዚህን መሰል ነገሮችን ያሟላች ከተማ መሆኗ ለፋብሪካው መቀመጫነት አስመርጧታል።
ኩባንያው በግለሰብ እጅ ከመውደቁ ከቅርብ ዓመታት በፊት በውስጡ 7,660 ሰራተኞች ነበሩት። ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጪ ሽያጭ የሚውል ምርት በበቂ ደረጃ ያመርት ነበር። በቀን 24 ሰዓት በሦስት ፈረቃ የሚያመርት ግዙፍ ኩባንያ ነበር። በጨርቃ ጨርቅ የምርት 37 በመቶ ያህሉን የሐገር ውስጥ ገበያ ውስጥ የሚሸፈነው የድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
ወ/ሮ ሽብሬ ጉሩሙ በጨርቃጨርቅ ፋብሪካው ከልጅነቷ ጀምሮ ጡረታ እስከምትወጣ ድረስ እንዳገለገለች ተናግራለች። በወቅቱ በኩባንያው ግዙፍ ማሽኖች እንደነበሩት እና ቀስ በቀስ በሌሎች ዘመናዊ ማሽኖች ይተካሉ በሚል ተወስደው እንዳለቁ ትናገራለች። እንደ ወ/ሮ ሽብሬ ገለፃ “ጥሩ እየሰራን በመሀል ድንገት ለአስር ቀን እረፍት ይሰጠናል። ምክንያቱ ደግሞ የዚያ አካባቢ መብራት ስለሚጠፋ ነው። ወደስራ ስንመለስ ግን የሆነ ማሽን በቦታው አይኖርም። የሚነገረን ምክንያት ‘የድሮ ብረቶች ከባድ ስለሚሆኑ እና የሰው ጉልበት በጣም ስለሚፈልጉ በዘመናዊ እና በአዲስ ለመተካት አስበን ነው’ የሚል ነበር። የቅርብ አለቆቻችንም ይህን ነበር የሚያውቁት። ነገር ግን በእንደዚህ ዓይነት መልኩ የተወገደ እቃ ተተክቶም ተመልሶም አያውቅም” ስትል ትዝብቷን አጋርታናለች።
አቶ ሽመልስ ጥላሁን “ቀስ በቀስ የከሰመ ግዙፍ ፋብሪካ ነበር” ይላል። እንደ አቶ ሽመልስ ገለፃ የድርጅቱ መዳከም ድሬደዋ ከተማ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል። “ኩባንያው የተዳከመው ቀስ በቀስ በማያስታውቅ ሁኔታ ነው። ከፍተኛ የሰው ኃይል ያስፈልገው ስለነበር ከፍተኛ የስራ ዕድል ለነዋሪው ፈጥሮ ነበር። የድሬደዋ ሰውም በወቅቱ የስራ ሰው ነበር”
አቶ ሽመልስ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካው ሰርቷል። “ያ ሁሉ ማሽን የት ገባ የሚል ጥያቄ ሁሌ ይፈጠርብኛል” ይላል። ኩባንያው እድገቱ እያሽቆለቆለ በመጣበት ወቅት የተለያዩ ምክንያቶች ይሰጡ እንደነበር ያስታውሳል። “የሠራተኛው ለምርታማነት መነሳሳትና የስራ ዲሲፕሊን የሚደነቅ ቢሆንም በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ፋብሪካው ትርፋማ ሆኖ ለዕድገት ተጠቃሚ መሆን አልቻለም። ለምሳሌ ድሬዳዋ በልባሽ ጨርቆች በመጥለቅለቋ ማሽኖቹ የጥንት ስለሆኑ በዘመናዊ መተካት አለባቸው እየተባለ ተመዘው አለቁ። የተተካ ዘመናዊ ማሽን የለም” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።
ስለ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አበርክቶዎች ሲነሳ የእግር ኳስ ክለቡና የሙዚቃ ቡድኑ አይዘነጉም። በወቅቱ ድሬደዋ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች የእግር ኳስ ክለቦች ነበሯቸው። አቶ ንጉሤ ውቃው በምድር ባቡር ኩባንያ በጡረታ ምክንያት ስራ እስካቆመበት ጊዜ አገልግሏል። በወቅቱ ስለነበረው የእግር ኳስ ሁኔታ ሲገልፅ “በደጋፊ ደረጃ በጣም ተፎካካሪ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ምድር ባቡር ኩባንያ እና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የእግር ኳስ ክለቦች ነበሩ። ድሬዳዋን ለሁለት ይከፍላት የነበረው ሁለቱ የእግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በነበራቸው ጊዜ ነው። አብዛኛው የአዲስ ከተማ እና ደቻቱ ሰፈር ሰዎች የኮተኒ ደጋፊ ሲሆኑ ከዚራ፣ ዲፖ፣ ኮኔል የመሳሰሉት የምድር ባቡር አሻራ ያረፈባቸው ሰፈሮች ደግሞ የምድር ባቡር ኩባንያ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊ ነበሩ” ሲል ትውስታውን አጋርቷል።
ልክ እንደ እግር ኳስ ክለቡ ሁሉ በድሬደዋ ውስጥ በስፋት ይንቀሳቀስ የነበረ የሙዚቃ ቡድንም ነበር። የጨርቃ ጨርቅ የሙዚቃ ቡድን በድሬደዋ ብቻ ውስጥ ሳይሆን እስከ በዴሳ፣ መቻራ እና አሰበ ተፈሪ እየተዘዋወሩ የሙዚቃ ሥራቸውን አቅርበዋል። በሙዚቃ ክለብ ውስጥ በቅርቡ በሞት ያጣነው መምህር ስለሺ እና የድሬደዋ ቆንጆ በመባል የምትታወቀው ወ/ሮ መሰሉ ካሳን ይጠቀሳሉ።
ፋብሪካው በምርቶቹ ጥራትና ብዛት ከተለያዩ ድርጅቶች የምስጋናና የዕውቅና ደብዳቤዎች ይደርሱት እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። የ22ኛው የሠላምና ትብብር ጉባኤ በ1975 ዓ.ም. በተከበረበት ወቅት ዓለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪ ተሸላሚ ሆኗል፣ ጳጉሜን 4 ቀን 1981 ዓ.ም. ብሔራዊ የጨርቃጨርቅ ኮርፖሬሽን በአዋሳ ከተማ ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ውጤቶች ኤግዚቢሽን በጠቅላላ አቀራረብና የምርት ጥራት ከሴክተሩ አንደኛ በመውጣት የምርት ኤግዚቢሽን ዲፕሎማና የወርቅ ዋንጫ አግኝቷል።
በአሁኑ ሰዓት የድሬደዋ ጨርቃ ጭርቅ ፋብሪካ የድሮው ግርማ ሞገሱ የለም። በድሬደዋ ነዋሪዎች ዘንድም መጠሪያው እንኳን በብዛት አይታወቅም። ስያሜውን ሬድዋን ጨርቃ ጨርቅ ወደሚል ቀይሯል። በግለሰብ ይዛታ ስር የሚገኘው ሬድዋን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በሥራ ላይ የሚገኙት “ፈትል”ና “መታስ” የሚባሉት ክፍሎች ብቻ ናቸው። እነዚህ ክፍሎች ድርና ማግ እየሰሩ ለደንበኞች ያቀርባሉ። በአንድ ሽፍት ብቻ ከ2፡30 እስከ 10፡30 የስራ ሰዓታቸው ነው። በአሁን ሰዓት 125 ሰራተኞች ብቻ ሲኖሩት ሙዚቃ እና ስፖርትን የመሰሉ ማኅበራዊ ግልጋሎቶቹ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠዋል። በአዲስ ይተካሉ በሚል የተወሰዱት ማሽኖች በተባለው መሰረት አልተተኩም። አሮጌዎቹም የት እንዳሉ አይታወቅም።
ቁጥሩ የበዛ ሥራ አጥ በሚገኝባት ድሬዳዋ እንደዚህ ዓይነት ፋብሪካዎች ከአገልግሎት ውጭ መሆን በቀላል ሊታይ እንደማይገባ ለዚህ ዘገባ ያነጋገርናቸው የቀድሞ ሰራተኞች ይናገራሉ። የከተማዋ ቀደምት ነዋሪዎች ቢያንስ አንድ የቤተሰባቸው አባል በፋብሪካው በማገልገሉ ለፋብሪካው እና ለምርቱ ከፍ ፍቅር እንዲኖራቸው ማድረጉን እንደ በጎ እድል ተጠቅሞ ፋብሪካው በቀደመ ሞገሱ እንዲገኝ የብዙዎች ምኞት ነው።