ታህሣሥ 9 ፣ 2014

ለዓመታት የተጓተተው የባህርዳር ከተማ የቤት ማኅበራት ጥያቄ

City: Bahir Darማህበራዊ ጉዳዮች

በኪራይ ቤት እንግልት የተማረሩት ቤት ፈላጊዎች የገቢ መጠናቸውን ተመልክተው ማኅበራቸውን አደራጅተዋል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ለዓመታት የተጓተተው የባህርዳር ከተማ የቤት ማኅበራት ጥያቄ
Camera Icon

photo: peniel tafesse

እያደገ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በሐገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል። ችግሩን ለማቃለል በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ የተካሄዱት ሙከራዎች ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያንን የቤት ባለቤት ማድረጋቸው አይካድም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ለቤት ገንቢዎች እና ገዢዎች ብቻ ብድር ለመስጠት የተቋቋሙ ‘ሞርጌጅ’ ባንኮች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉ በባህርዳር ከተማም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ተስተውሏል። በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በኩል ነዋሪው እንደ ገቢ አቅሙ እንዲደራጅ አማራጮች ቀርበዋል። የአማራጮቹ ክፍፍል ከቤት ፈላጊው የገንዘብ አቅም አንጻር የተቃኘ ነው።

የመጀመርያው አማራጭ የተሻለ ገቢ ያላቸውን ቤት ገንቢዎች ያቀፈ ነው። በዚህ ቡድን ውስጥ የተካተቱት በባህር ዳር ከተማ ውስጥ መሬት አግኝተው ቤት ለመስራት ያለሙ ናቸው። ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ደግሞ በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ አካባቢዎችን ለቤት ግንባታ እንደሚያውሉ ተስፋ አድርገዋል። “ሳተላይት” የሚል መጠርያ ያላቸው ቦታዎች ቤት ፈላጊዎቹ በተደራጁበት ቅደም ተከተል እና ማሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታ እንዳሟሉበት ፍጥነት መሬት እንደሚያገኙ ተስፋ ተሰጥቷቸዋል። አካባቢዎቹ መሸንቲ፣ ዘንዘልማ፣ ዘጌ እና ጢስ ዓባይ የተሰኙት አነስተኛ ከተሞች ናቸው።

በኪራይ ቤት እንግልት የተማረሩት ቤት ፈላጊዎች የገቢ መጠናቸውን ተመልክተው ማኅበራቸውን አደራጅተዋል። የመደራጀት ሂደቱን አጠናቀው ከአራት ዓመታት በላይ የቆዩት ማኅበራቱ የቤት መስሪያውን መሬት እስካሁን አልተረከቡም። የሂደቱን መጓተት የተመለከቱት የባህርዳር ነዋሪዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አቋቁመው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

በባህርዳር ከተማ በማኅበር ተደራጅተው ቦታ ለማገኘት የሚጠባበቁ ከ13 ሺህ በላይ አባላት ያሏቸው 598 በላይ ማኅበራት መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ማኅበራቱ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው፣ በከተማ አስተዳደሩ ዕውቅና አግኝተው የተደራጁት በ2010 ዓ.ም. ሲሆን 1.6 ቢልየን ብር በዝግ አካውንት መቆጠብ ችለዋል። መሬቱን ባጠረ ጊዜ ተረክበው የመኖርያ ቤት ችግራቸውን ለመቅረፍ በማለም መቆጠብ የጀመሩት ቤት ፈላጊዎች የሂደቱ መጓተት ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደዳረጋቸው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

አቶ ዘገየ ታከለ በማኅበር ከተደራጁት ቤት ፈላጊዎች አንዱ ነው። የመደራጀት ዕድሉ እንዳያመልጠው ቅድሚያ ክፍያውን ከብድር እና ቁጠባ ተበድሮ እንደከፈለ ነግሮናል። በዝግ አካውንት የተቀመጠው ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ከወቅቱ አንጻር በጣም ያነሰ መሆኑ ቁጠባውን እና ውጥኑን ገደል እንደከተቱበት ያምናል ‘‘የባከኑት ዓመታት ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከበቂ በላይ ናቸው። ሁኔታው ሞራላዊም ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም አሳድሮብኛል። ተበድሬ ቅድሚያ ክፍያውን ስቆጥብ ቤቱ በፍጥነት ተሰርቶ ከቤት ኪራይ እንደምላቀቅ በማሰብ ነበር፤ ግን አልሆነም’’ ሲል ምሬቱን ይገልጻል። ክስተቱ የእርሱ ብቻ ሳይሆን የበርካታ የማኅበሩ አባላት ቅሬታ እንደሆነ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ካነጋገራቸው የማኅበሩ አባላት ተረድቷል።

የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው አባል አቶ ማስረሻ በላይ ‘‘በመኖሪያ ቤት ሕብረት ስራ ማኅበራት ማደራጃ መመሪያ ቁጥር 28/2009 መሰረት በመኖሪያ ቤት የሕብረት ስራ ማኅበራት የዕውቅና ሰርተፍኬት በተሰጠ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የቤት መስሪያ ቦታ እንደሚሰጥ መመሪያው ይደነግጋል። ይህ ካልሆነ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍ/ቤት መውሰድ አንደሚቻል መመሪያው ላይ በግልፅ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ ማኅበራቱ ከሚያዝያ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ዕውቅና ቢሰጣቸውም እስካሁን ቦታ አላገኙም። ሁኔታው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከማስከተሉ በተጨማሪ መሰረታዊ የመመሪያ ጥሰት ነው’’ ያሉ ሲሆን፣ የማኅበር አባላቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ የከተማዋን ገጽታ ማበላሸት መሆኑን በመገንዘብ በሰከነ መንገድ ለመጨረስ እየጣሩ እንደሆነ ይናገራሉ።

‘‘በከተማው ብዙ ሄክታር መሬት በማኅበር ለተደራጁ አባላት ለመስጠት ካሳ ተሰልቶለት ተከልሎ ይገኛል’’ የሚሉት አቶ ማስረሻ መሬቱ ታጥሮ ምንም ዐይነት ጥቅም አለመስጠቱ ብክነት ስለመሆኑ አብራርተዋል። ‘‘ከገበሬዎች ተወስዶ ታጥሮ የተዘጋጀው መሬት ለግብርና ሥራ አልዋለም። ለማኅበራቱም አልተሰጠም። ገበሬዎቹም የካሳ ክፍያ አልተፈጸመላቸውም’’

የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው 13ሺህ የሚጠጉ የማኅበሩ አባላትን ጥያቄ ይዘው የሚመለከተውን የመንግሥት አካል ስለማነጋራቸው የኮሚቴው አባላት ይናገራሉ። ለከተማዋ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ማመልከቻ ቢያስገቡም በአመራሮች በፍጥነት መቀያየር፣ ጉዳያቸውን በትኩረት የሚመለከት አመራር በማጣት እና በመሰል እንቅፋቶች መፍትሔ ሳያገኙ ቆይተዋል። ‘‘ሐገራችንም ሆነ ክልላችን የሚገኙበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንረዳለን’’ የሚሉት የማኅበሩ አባላት መንግሥት በድህረ ጦርነቱ አኮኖሚውን ሲያነቃቃ በሂደት ላይ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችን የሚያበረታቱ ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንደሚገባው መክረዋል።  

አስተያየት