ታህሣሥ 7 ፣ 2014

የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተግዳሮቶች በአዳማ

City: Adamaመልካም አስተዳደርማህበራዊ ጉዳዮች

“አካቶ ትምህርት” ማለት አካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች ጉዳት ከሌለባቸው ጋር በጋራ እንዲማሩ የሚያደርግ የማስተማር ዘዴ ነው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተግዳሮቶች በአዳማ
Camera Icon

photo credit: ambo project

በአዳማ ከተማ በሚገኙ አራት የመንግስት እና አንድ የግል ት/ቤቶች ውስጥ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ይሰጣል። ቡርቃ ቦኩ፣ ኦዳ ሮባ፣ ደንበላ እና ገዳ ኪሎሌ የሚሰጡ የመንግስት ት/ቤቶች ሲሆኑ በግል ቅዱስ አንጦኒዮስ “የአካቶ ትምህርት” የሚሰጥባቸው ተቋማት ናቸው። “አካቶ ትምህርት” ማለት አካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች ጉዳት ከሌለባቸው ጋር በጋራ እንዲማሩ የሚያደርግ የማስተማር ዘዴ ነው። የማስተማር ዘዴው አካል ጉዳት ያለባቸው ዜጎች ከቀለም ትምህርቱ በተጨማሪ ከማኅበረሰቡ ጋር የሚኖሩበትን ሁናቴ የመለማመድ እድል እንደሚፈጥርላቸው የመማር ማስተማር ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በቡርቃ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት 14 ወንዶች እና 6 በጠቅላላው 20 የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ይገኛሉ። በአካል ጉዳት አንጻር ሲቀመጡ መስማት የተሳናቸው 10 ደግሞ የአዕምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው 10 ተማሪዎች ናቸው።

ከዚህ ቀደም ሁለቱም ክፍሎች በአንድ መምህር ይሸፈን እንደነበርና እርሷ ት/ቤቱን ከተቀላቀለች በኋላ ሁለት መምህራን ሆነው እንደሚሰሩ የምትናገረው ፍሬህይወት ካሳዬ በቡርቃ ቦኩ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የልዩ ፍላጎት መምህርት ናት። ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ ት/ቤቱ ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት መርጃ መሳሪያ እጥረት እንዳለበት ትናገራለች።

"ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ተብሎ የተዘጋጀ ምንም ዓይነት መጽሐፍ የለም። የትምህርት አጋዥ ቁሳቁሶችም የሉም” የምትለው መምህሯ የምልክት ቋንቋ በማስተማር ላይ የምትገኘው ራሷ በተማረችበት መጽሐፍ ነው። “ከመጽሐፉ ላይ ለእነርሱ እንዲመጥን አድርጌ እያዘጋጀሁ አስተምራቸዋለሁ እንጂ የተዘገጀ ‘ጋይድ’ የለም” ብላናለች።

ሌላኛው የመንግስት ት/ቤት ደንበላ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው። በቅድመ መደበኛ ክፍል ውስጥ የአካል እና የአዕምሮ ጉዳት ያለባቸው 12 ተማሪዎች ይገኛሉ። ተማሪዎቹ የአእዕምሮ እድገት ውሱንነት፣ ልዩ ልዩ አካል ጉዳት፣ መስማት መስማትና ማየት መሳን ያለባቸው መሆናቸውን የልዩ ፍላጎት መምህርት ሰርካለም ሲራጅ ትናገራለች።

“ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ወደ ት/ቤት ማምጣት ድካም ይጠይቃል። ለወላጆች ግንዛቤ የማስጨበጥ  ስራው እጅግ ፈታኝ ነው” ትላለች። ጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርገው በአዳማ ከተማ የሚንቀሳቀሱ ሁለት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መኖራቸውንም ነግራናለች።

"እስካሁን ከ4 እስከ 14 ዓመት ድረስ ያሉ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተቀብለናል” የምትለው መምህርቷ የተማሪዎቹ የጉዳት ዓይነት ከተለየ በኋላ ጉዳት ከሌለባቸው ተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው እንደሚማሩ አብራርታለች። “እድሜአቸው ወደ አስራዎቹ ሲጠጋ ሴት ተማሪዎችን የሚያስቀሩ ወላጆች አሉ። ምክንያታቸውን ለማወቅ ቤት ለቤት በተጓዝንበት ወቅትም የወላጆቹ ምክንያት የጾታዊ ጥቃት እና የመደፈር ስጋት መሆኑን ለማወቅ ችለናል” ብለዋል።

በ2006 ዓ.ም. የተመሠሰረተው የቅዱስ እንጦኒዮስ ት/ቤት ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ከሚቀበሉ ትምህርት ቤቶች መካከል ይገኝበታል። የኮቪድ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በአማካኝ 27 የአካል እና የአዕምሮ ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎች የነበሩት ትምህርት ተቋሙ በአሁኑ ሰዓት 8 ተማሪዎችን ከነርሰሪ እስከ ዩኬጂ በ”አካቶ ትምህርት” እያስተማረ እንደሚገኝ ከትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ሲ/ር ሃና መንግሥቱ የተገኘነው መረጃ ያመለክታል። በልዩ ፍላጎት ትምህርት የሰለጠነ ባለሙያ ማግኝት ከባድ እንደሆነ እና በአሁኑ ወቅት አንዲት የልዩ ፍላጎት መምህር ተማሪዎችን በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ነግረውናል።

“በአሁን ወቅት አንድ ልዩ ፍላጎት መምህርት አለችን። ነገር ግን በተለያየ ጊዜ የገጠመን ፈተና በዘርፉ የሰለጠነ መምህር ማግኘት እጅግ ከባድ ነው።" የሚሉት ሲ/ር ሃና መንግስቱ የዘርፉ ትልቅ ፈተና እንደሆነም ይናገራሉ።

ለሦሰት ዓመታት መደበኛውን ትምህርት ለመከታተል የሚያስችላቸውን ክህሎት የያዙት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተማሪዎች ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ማጣት ሌላው ችግር መሆኑንም አንስተዋል። “ተማሪዎቹ እኛ ጋር ያላቸውን የትምህርት ቆይታ ቢያጠናቅቁም በወላጆች ጥያቄ ድጋሚ ወደኛ የሚመለሱበት ጊዜም አለ” ብለዋል ርዕሰ መምህርቷ

ወ/ሮ ፋጡማ አደም የአምስት ዓመት ልጅ አላቸው። “ትምህርት ቤት መመላለስ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ለውጥ ዓይቼበታለሁ” በማለት በመሰረታዊ የመግባባት ክህሎት እና ፍላጎትን በመግለጽ ላይ ያሳየውን ለውጥ ነግረውናል።

ሦስት ልጆቻቸው “መስማት የተሳናቸው” እንደሆኑ የሚናገሩት ወ/ሮ ሶፊያ ከድር ትልቁ ገዳ ኪሎሌ (በቀድሞ አጠራሩ ቁጥር 2) እስከ አራተኛ ክፍል ተምሯል። “ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ሲሸጋገር ግን ለእርሱ የሚሆን ት/ቤት በማጣቱ ለሦሰት ዓመታት ትምህርቱን አቋርጧል። አሁን 6ኛ ክፍል ነው። ባያቋርጥ ኖሮ አሁን የ10ኛ ክፍል ተማሪ ይሆን ነበር” ብለዋል። “አቅም ያለው በቂ ትምህርት ያለበት አዲስ አበባ ወስዶ ልጆቹን ያስተምራል። ለኛ አቅም ለሌለን ደግሞ መንግሥት ቢያንስ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን አዳማ ውስጥ እንዲከታተሉ የሚያደርግ አሰራር ሊዘረጋልን ይገባል ይላሉ”

ከዚህ ቀደም ቁጥር 2 በሚል ስሙ የሚታወቀው ገዳ ኪሎሌ ት/ት ቤት ም/ርዕሰ መምህር አበበ ቶሎሳ ትምህርት ቤቱ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን “በሁለት መንገድ ያስተምራል” ብለዋል። የመጀመሪያው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ለይቶ ማስተማር ሲሆን ከ5ኛ ክፍል በኋላ ግን ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ ይደረጋል ብለውናል። ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር  የሚማሩ ተማሪዎች የትኩረት ማጣት እና የተሟላ የመማሪያ ግብአት አለመሟላት በአብዛኛው ውጤታማነታቸው እና ቀጣይነታቸው ይቋረጣል ሲሉ ነግረውናል።

መምህርት መሠረት ቀና የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ዲፓርትመንት ተጠሪ ናት። "የመምህራን እና የረዳት  መምህራን፣ የክፍል ጥበት ልጆቹን በተቀመጠው ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ  ከፋፍለን እንዳናስተምር አግዶናል። ከአራተኛ ክፍል በኋላ ወደ አካቶ ሲገቡ ትኩረት መነፈጋቸው የደከምንበትን አዝመራ ፍሬውን ዕንዳለማየት ሆኖብናል” ብላለች።

“የተሻለ የቤተሰብ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ከአምስተኛ ክፍል በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ” የምትለው መምህርት መሠረት “እዚህ መጽሐፍት፣ ማስተማሪያ ቁሳቁሶች ጉድለቶች በመኖሩ ልጆቹን በሚፈለገው መንገድ ለማብቃት ሳንካ ሆኖብናል” ስትል ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።

እንደ ኑስ ታደሰ ሐሳብ “የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ላይ የሚስተዋለው የንቃት ደረጃ በመንግሥትም ሆነ በሕዝብ ዘንድ የወረደ ነው” የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ኑስ ታደሰ ከአፋር ክልል ልጅቿን ለማስተማር የመንግስት ስራዋን እና አነስተኛ ንግዷን ጥላ እንደመጣች ነግራናለች። ዘንድሮ በት/ቤቱ መማር የጀመረችው ትልቋ ልጇ እድሜዋ ሰባት ሲሆን መስማት የተሳናት ናት። 

"ልጆቻችንን ጠዋት ትምህርት ቤት አስገብተን እስከ ስድስት ሰዓት አብረን እንሆናለን። ተምረው ሲጨርሱ ጠብቀን ነው ይዘናቸው የምንሄደው። ልጆቹን የሚንከባከብ ወይም የሚጠብቅ ሞግዚትም ሆነ ተቆጣጣሪ የለም" ስትል ከሪፖርተራችን ጋር በነበራት ቆይታ ነግራናለች። የመጫወቻም ሆነ የመጸዳጃ ሥፍራዎቹም አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ አለመሆናቸውን ታዝባለች።

በትምህርት ቤቱ የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ ህይወት ንጉሤ ማየት የተሳናት ናት። ከዚህ ቀደም እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ ሻሸመኔ መማሯን ነግራናለች። "የብሬይል መጻፊያ፣ የብሬል መጸሐፍት ማግኘት ባለመቻል ተማሪዎችን እና ቤተሰቦቼን አንብቡልኝ እያልኩ ነው የምማረው" ስትል ያለባትን ችግር ነግራናለች። የድምጽ መቅጃ መሳሪያ (ሪከርደር) ቢኖራትም የባትሪው ወጪ እንደልብ እንዳትጠቀምበት እንዳገዳት ነግራናለች።

በከተማዋ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በታዳጊዎች እና እናቶች ላይ የሚሰራው አርፒሲ (Remember the Poorest Community) ከአውሮጳውያኑ 2014 ጀምሮ በ“አካቶ ትምህርት” ላይ እየሰራ ይገኛል። “በወቅቱ በሦስት ቀበሌዎች ላይ ቤት ለቤት ሄደን ባደረግነው ጥናት መሠረት በሦስት ቀበሌዎች 60 የአዕምሮ እድገት ውስኑነትን ያለባቸውን ጨምሮ የተለያየ ጉዳት ያለባቸው ታዳጊዎች አግኝተናል” የሚሉት የድርጅቱ የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ ገመቹ ናቸው። 

ከዚህ ቀደም ከሴቭ ዘ ችልድረን ጋር አሁን ደግሞ ኤሪክስ ከተባለ አጋር ጋር በጥምረት የሚሰራው ድርጅቱ በራሱ ት/ቤት እና በ4 የመንግሥት ት/ቤቶች ላይ እንደሚሰራ ነግረውናል።

"ስራውን የወላጆች የግንዛቤ እጥረት፣ በዘርፉ የሰለጠኑ መምህራን አለመኖር፣ የትምህርት ቤት አስተዳደር እና ማኅበረሰብ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን እንደተጨማሪ ሸክም መመልከት የፈተናኑ ጉዳዮች ነበሩ" የሚሉት አቶ ዓለማየሁ ገመቹ ሌላኛው ፈታኝ ሁኔታ የወላጆች የኢኮኖሚ ዝቅተኝነት ነበር ይህንን ለማሻሻል ለወላጆች በፈለጉት የስራ መስክ ለማሰማራት መነሻ የቁሳቁስ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ ነግረውናል። በ3 ዓመት የትግበራ ጊዜ ውስጥም 4.5 ሚሊየን ብር በዚህ ፕሮጀክት ወጪ እንደሚሆን የሚናገሩት ኃላፊው ከላይ የተነሱት ችግሮች በሙሉ አለመቀረፋቸውን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር አዳማ ከተማ ተወካይ ከአቶ መሀመድ ያሲን ጋር ባደረግነው ቆይታ እንደነገሩን የዩንቨርሲቲ ምሩቃን የሆኑ በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር በ18ቱም ቀበሌ የቤት ለቤት ቆጠራ አድርገው ልየታ መስራታቸውን ነግረውናል። የተጠናቀቀ መረጃው እንዳልደረሳቸው የነገሩን አቶ መሃመድ ያሲን በተለያዩ ምክንያት ያቋረጡ ተማሪዎች ወደ ት/ቤት እንዲመለሱ፣ የኅብረተሰቡ እና የአመራሮች ግንዛቤ እንዲጎለብት እየሰሩ እንደሆነ ነግረውናል። 

“በ2013 ዓ.ም. ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን 14 አካል ጉዳተኛ ታዳጊዎችን ከአዳማ እድሮች ጋር ደጋፊነት መሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ ወደ ት/ቤት እንዲገቡ አድርገናል” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ አዳማ ሪፖርተር ተናግረዋል።

የአዳማ ትምህርት ጽ/ቤት የልዩ ፍላጎት ባለሞያዋ ትዕግስት ንጉሤ “በአካቶ እና ልዩ ፍላጎት አንድ ላይ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ 221 ተማሪዎች ይገኛሉ። ከእነዚህም 23 ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። ከከተማ ስፋት አንጻር የተደራሽነት፣ የማቴሪያል፣ የመምህራን እጥረት አለብን። ይህንን ለማሟላት ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር እየሰራን ነው” ብላለች። 

ከገዳ ኪሎሌ ት/ቤት ወላጆች የቀረበውን ቅሬታ ያነሳንላቸው ወ/ሮ ትዕግስት ንጉሤ መምህራኑ የውል እና የቅጥር ሒደታቸው ተጠናቅቆ መቀጠራቸውን እና ስራ ስለማቆማቸው እንደማታውቅ ነግራናለች።

በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ተጨማሪ አንድ ት/ቤት ለመጨመር እንዲሁም በቀጣይ ዓመት እስከ 321 ተማሪዎች ለማካተት እየሰሩ መሆኑን ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።

አስተያየት