መላው ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ለ6 ወራት የሚቆየው አዋጁ የተወሰኑ መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ይገድባል። ከአዋጁ ክልከላዎች መካከል አንዱ ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ መስጠት እንዲቋረጥ የሚያዘው ይገኝበታል። ማንነትን ገላጩ መታወቂያ የቀበሌ፣ የሥራ፣ የትምህርት ቤት ወይም ፓስፖርት መሆን የሚችል ሲሆን ባይታደስም አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ተቀምጧል። ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ከእነዚህ ጋር ተመጣጣኝነት ያለው መታወቂያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት አገልግሎት ይሰጣል።
መነሻው የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት፣ ግቡ የማኅበረሰብን ደህንነት መጠበቅ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላ ተግባራዊ ማድረግ እንደከበዳቸው ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተፈናቅለው ጎንደር ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በድርቅ እና በጦርነት ምክንያት የቀደመ መኖርያቸውን የለቀቁት ግለሰቦች “ቤት ንብረታችንን በድንገት ስለለቀቅን ማንነታችንን የሚገልጽ መታወቂያ የለንም” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። “ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ግለሰብ መታወቂያ መያዝ እንዳለበት በሚያስገድድ አዋጅ ስር መታወቂያ አለመያዝ ስህተት መሆኑን እናውቃለን። ችግራችን ግን የተለየ ነው። ከቤታችን ስንወጣ ተዘጋጅተን ባለመሆኑ ራሳችንን የሚገልጽ መታወቂያ የለንም። ያንን የሚተካ ጊዜያዊ መታወቂያም ሆነ መግለጫ ወረቀት አልተሰጠንም” የሚል ማብራሪያ የሰጡን ተፈናቃዮቹ ሁኔታው እንቅስቃሴአቸውን ስጋት የተመላበት እንዲሆን ስለማድረጉ ነግረውናል።
ከቤተሰቦቹ ተለይቶ ከወልዲያ ከተማ የተፈናቀለው አቶ ቢያምረው አስረስ ጎንደር ከመግባቱ በፊት በጥበቃ ሥራ ይተዳደር እንደነበር ነግሮናል። በሕብረት ባንክ ወልዲያ ቅርንጫፍ ውስጥ ያገለግል የነበረው ግለሰቡ “መታወቂያ ስለሌለኝ እንደልብ መንቀሳቀስ አልቻልኩም” ይላል። በተለይ በምሽት ሰዓታት ወደ ቤቱ ለመግባት እንደሚቸገር አንስቷል። በአንድ ምሽት በፖሊሶች ቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበርና ከማጣራት ሂደቱ በኋላ መለቀቁን ነግሮናል።
የአዲርቃይ ገጠራማው አካባቢ በግብርና እየተዳደሩ ይኖሩ እንደነበር የሚናገሩት እማዋይ ቢሆነኝ በጎንደር ከተማ ሲንቀሳቀሱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታውሳሉ። መታወቂያ ስለሌላቸው ተጠላፊ ዋስ በማቅረብ ከእስር መፈታታቸውን ተናግረዋል።
“የሽብር ቡድኑ ተላላኪ ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ እንግልት ደርሶብኛል” ያለን ወጣት ስሙን ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆነም። ከሚኖርበት አካባቢ ከተፈናቅሎ ጎንደር ከተማ ከገባ በኋላ ለአንድ ሳምንት ያህል ጎዳና ላይ አድሯል። በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ዋስ የሚሆነው ሰው በማጣቱም ብዙ እንደተንገላታ ለአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር አብራርቷል። “ጊዜው እና ሁኔታው ጤነኛውን ከአሸባሪው፣ ነዋሪውን ከስደተኛው ለመለየት አስቸጋሪ ቢያደርገውም፤ ስደተኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ከመንገላታታቸው በፊት ጊዜያዊ የስደተኛ መታወቂያ የሚያገኙበት አሰራር ቢመቻች መልካም ነው” ብሏል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የፋሲል ክ/ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳኛቸው ቢምር “ያለ መታወቂያ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ሰው ይያዛል” ብለውናል። “ራሱን የሚገልጽ መታወቂያ ያልያዘ ግለሰብ ሲያዝ ወደ ማረሚያ ቤት ይላካል። ይህንን የምናደርገው ግለሰቡ የሽብር ቡድኑ ተላላኪ ወይም ከሐገር መከላከያ እና ከአማራ ልዩ ኃይል ተልእኮ በተቃራኒ የቆመ ሐሳብ እንዳለው እና እንደሌለው ማረጋገጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው” ካሉ በኋላ ፖሊስ ጣቢያው የግለሰቡን ሁኔታ ካጣራ በኋላ እንደሚለቀቅ አስረድተዋል። “ግለሰቡ በእርግጥ ተፈናቃይ ከሆነ ተጠላፊ ዋስ እንዲጠራ ይደረጋል። ጊዜያዊ መታወቂያም ይሰጠዋል። ከጊዜያዊ ማቆያ ወይም ከፖሊስ ጣቢያ የሚወጣው በዚህ ሁኔታ ነው” ብለዋል።
መታወቂያ የሌላቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ የተገኘን ሁሉ እንደ አስፈላጊነቱ ማረፊያ ቤት እንደሚያቆዩ እና እየተጣራ እንደሚለቀቁ ነግረውናል።
“በከተማዋ ማንኛውም ሞተር ተሽከርካሪ ከምሽት ከ12:00 በኋላ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከምሽት ሁለት ሰዓት በኋላ ያለ ፈቃድ መንቀሳቀስ አይችሉም” የሚሉት አቶ ዳኛቸው ቢምር “አስፈላጊ ሁኖ ከተገኘ በአዋጁ መሰረት ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቀቁ ለማዘዝ ይችላል” ብለዋል።
“ሰዎች ድንገት ቢታመሙ፣ ምጥ ቢያዙ፣ እና የመሳሰሉት ነገሮችን ሆነው ትራንስፖርት ሲፈልጉ በእኛ በኩል በየቀበሌው ያመቻቸናቸው ተሸከርካሪዎች ስላሉ በእነርሱ መጠቀም ይቻላል” ብለዋል። አክለውም “ህዝባችን ጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመደራጀት አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁና ተፈናቃይ ወገኖችን በቻሉት አቅም እንዲተባበሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል”