ታህሣሥ 6 ፣ 2014

በ50 ዓመታት ጉዞ የራሱን ባህል የፈጠረው የአውራ አምባ ማኅበረሰብ

City: Gonderባህል ታሪክ

አውራምባዎች ከሌላው የኢትዮጵያም ሆነ የክልሉ ነዋሪዎች በተለየው የአኗኗር ዘይቤአቸው ይታወቃሉ።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በ50 ዓመታት ጉዞ የራሱን ባህል የፈጠረው የአውራ አምባ ማኅበረሰብ

አውራ አምባ 144 አባወራዎች 551 አካባቢ የቤተሰብ አባላትን ያካተተ ማኅበረሰብ ነው። በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ከወረታ ከተማ ወደ ደብረታቦር በሚወስደው ጎዳና በ8 ኪ.ሜ ርቀት ከ18 ሄክታር በማይበልጥ መሬት ላይ ያረፈ የመኖርያ መንደር ነው። ማኅበረሰቡ አባላቱን የሚመዘግብበት ሁለት መዝገቦች አሉ። መዝገቦቹ ነባር እና አዲስ አባላት የሚመዘግቡባቸው ናቸው። በልዩ ልዩ ምክንያት ከማኅበረሰቡ መደበኛ መኖሪያ ተበታትነው ነው ያሉት በቁጥር አይገለጹም። የማኅበር አባል የሚባለው ያለው ነው። በብዛት 551 በትውልድ ደግሞ 3ኛ ትውልድ ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ። ማኅበረሰቡ 5 መሰረታዊ ሐሳቦች እንዳሉትም አባላቱ ይናገራሉ። መሰረታዊ የተባሉት ሐሳቦች የሴቶችን እኩልነት ማክበር፣ የህጻናትን መብት ማክበር፣ በጤና፣ በእርጅና ወይም በማንኛውም ምክንያት ወላጆቻችውን ያጡ ልጆችን መንከባከብ፣ መጥፎ አነጋገር እና መጥፎ አሰራርን ማስወገድ (ስርቆት፣ ሌብነት፣ ስድብ፣ እርግማን፣ ድብደባ፣ ነገረኝነት፣ ግድያ፣ ጥላቻ)፣ የተበጣጠሰ ወገንተኛ አለመሆን ናቸው። 

ማኅበረሰቡ የተመሰረተው በ1964 ዓ.ም. በዙምራ ኑሩ (ክቡር ዶክተር) ነው። አውራምባዎች ከሌላው የኢትዮጵያም ሆነ የክልሉ ነዋሪዎች በተለየው የአኗኗር ዘይቤአቸው ይታወቃሉ። የክልሉ ነዋሪ ለየት ባለ መልኩ የፆታ እኩልነትን በተግባር ያሳየ፣ ስራን የማኅበረሰቡ እምነት ያደረገ፣ እንደ ማኅበረሰብ የሚተዳደሩበት የራሳቸው የሆነ መተዳደሪያ መርሆዎችን በማስቀመጥ የሚተዳደር ማኅበረሰብ ነው። 

የአውራምባ ማኅበረሰብ የስራ ክፍፍሉ ችሎታን እንጂ ጾታን መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ገለፀ። በአንፃሩ በአውራምባ ማኅበረሰብ በ1ዐዐ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች በአውራምባዎች ሐሳብ አልተስማሙም። 

የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማኅበረሰቡ አባላት የአኗኗር ዘያቸውን ክቡር ዶክተር ዙምራና ዙምራ ካስተማሯቸው ቤተሶቦቻቸው እንደወረሱ ይናገራሉ። ሀሳቡ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ ትችት እና ነቀፋ ተሰንዝሮበታል። አውራምባ ለሁሉም ሰው ክፍት ነው። ከማኅበረሰቡ ውጪ ያሉ ግለሰቦች ወደ አካባቢው ሲሄዱ የማኅበረሰቡን ሕግና ደንብ ጠብቀው መኖር እስከቻሉ ድረስ ተቀባይነትን ያገኛሉ። ማኅበረሰቡ ከሁሉም የሰው ልጆች ጋር ሰላምና ውህደት ፈጥሮ መኖር ይፈልጋል ይላሉ የማኅበረሰቡ አባላት።

መስራቹ ዙምራ ኑሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ተሰጥቶላቸዋል። “በ6 ወር እድሜዬ ቆሜ እንደሄድኩ፣ በ2 ዓመቴ እንደትልቅ ሰው የመናገርና የመጠየቅ ብቃት እንደነበረኝ፣ በ4 ዓመት እድሜዬ ደግሞ በርካታ ማኅበራዊ ጉዳዮችን ሳነሳ እንደነበር እናቴ ለጎረቤቶቿ አጫውታቸው ነበር። በዚያ እድሜዬ በሴቶች እኩልነት፣ በህጻናት መብት፣ ደካማ ወገኖችን በመደገፍ፣ በአጠቃላይ መጥፎ አሰራንና አነጋገርን በማሰወገድ ሰላም መፍጠር በሚሉት መሰረታዊ ሀሳቦቼ በአካባቢው ካለው ማኅበረሰብ ተለይቼና ባይተዋር ሆኜ እማደርገው አጥቼ የህጻንነት ጊዜዬን አሳልፊያለሁ” ይላሉ።

በ13 ዓመታቸው ያጋጠማቸውን ሲናገሩ “በሰው ልጆች እንደ እህልና እንደ ውሃ ተርቤ፣ ሰው እያለ ሰው አጣሁ። በአካባቢው ያኔ የሚፈልገኝ አጥቼ ሀሳቤን የሚጋራኝ ሰው ፍለጋ ከቦታ ቦታ ስባዝን ቆይቻለሁ። ይህን ሁኔታዬን ያዩ ሰዎች ከሁሉም በላይ ምንድነው እምትፈልገው ብለው ቢሉኝ የሰው ልጅ እንደ እንጀራ፣ እንደ እህል፣ እነደ ውሃ ነው እሚርበኝ፣ እሚጠማኝ ብዬ ነው እምላቸው። ናፍቆቱ ሲብስብኝ የዓለም የሰው ልጆች የኔ ሆነው ባገኛቸውም እንኳ እራቤ የሚወጣልኝ አይመስለኝም። እናም ያንን አጥቼ ጎጃም፣ ጎንደር ወሎ እያልኩ ስባዝን አሁንም እንዳሰብኩት አልሆነም። ውዬም እምነጋገረው፣ መሽቶም እማድርበት አላገኘሁም። ማታ ማታ ዛፍ ላይ እሰቀላለሁ፤ ሲጎረብጠኝ ተስፋ በመቁረጥ ወደ መሬት እወርዳለሁ። አውሬዎች እየተፈራረቁ ከበውኝ ያድራሉ። ሲነጋጋ አውሬዎቹ ጥለውኝ ይሄዳሉ”

ዙምራ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲኖሩ ዓምስት ዓመታትን አሳልፈዋል። ከዚያም ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው የእርሻ ስራቸውን ማከናወን ጀመሩ። የሚሰበስቡትን ምርት ለደካማ ወገኖች ሲያከፋፍሉ ቆዩ ይህ ድርጊታቸውም በቤተሰቦቻቸው ተቀባይነት አላገኘም። ቤተሰቦቻቸው “እሱ አይበላም፣ አይጠጣም፣ አይለብስም፣ አልታደለም። የሱን ገንዘቡን ዘመድ አያገኘውም። ለባዕድ ነው እሚሰጠው” ይሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ዙምራ ማብራሪያቸውን ቀጥለዋል ”ባዕድ ዘመድ የሚባለው ልዩነት ሲመጣብኝ በሀሳብ ብቸኛ አደረገኝ። ብቻዬን መኖር አልችልም።

በበጋው ወቅት ምናልባት እያልኩ ተስፋ አልቆርጥም። አንድ ቀን ሀሳቤን እሚጋራኝ አገኛለሁ እላለሁ። በጋ ላይ በአንዱ ቦታ ሄጄ እቆያለሁ። የእርሻ ወቅት ሲሆን እመለሳለሁ። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ያለማቋረጥ ለበርካታ ዓመታት ያክል ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርኩ የሃሳቤ ተጋሪ ማኅበረሰብ ለማግኘት እልህ አስጨራሽ ጥረት ካደረኩ በኋላ በአንደኛው ዓመት ከመኖሪያ ቦታዬ ከእስቴ ወረዳ ተነስቼ ወደ ጎንደር ስሄድ ፎገራ ወረዳ ላይ በገበሬዎች ዙሪያ ሃሳቤን የሚዳምጡ ሰዎችን አገኘሁ። ሀሳቤን ሲያደምጡኝ በዓመቱ እየተመላለስኩ ከሰዎቹ ጋር በርካታ ውይይቶችን ካደረኩ በኋላ እንግዲህ እዚያው ሄጄ ብቀመጥ እቅዴ ይሳካል ስል ስኖርበት የነበረውን የእስቴ ወረዳ ለቅቄ ሰዎቹ ወደ እሚገኙበት ፎገራ ወረዳ በ1964 ዓ.ም መጥቼ ተቀመጥኩ።

እዚህ ተቀምጬ የአውራ አምባን ማኅበረሰብ መሰረትኩ። ለማኅበረሰቡ አባለት ለማቅረብ የመጀመሪያው መነሻ መሰረታዊ ሀሳቤ የሆነው የሴቶች እኩልነት ነው። ሴት በሴትነቷ እናት ናት። ወንድ በወንድነቱ አባት ነው። አባትና እናት ሆነው ሴቷ እንደሞግዚት ወንዱ እንደ አዛዥ የሆነበት ምክንያት በጉልበት ነው? በጉልበት ከሆነ ትርፍ ጉልበታችን ለስራ እናውለው። እናት እናት ናት። አባት አባት ነው። እናት በሌለችበት አባት የለም። አባት በሌለበት እናት የለችም። እኩል ሊያደርጋቸው ይገባቸዋል። ሚስቶቻችን ስንል ባዕድ መስለውን እንደሆነ እናቶቻችን እንበላቸው። እልኩ ሀሳቤን ለሚያደምጡኝ ሰዎች አካፈልኳቸው”

በመቀጠል ያነሳሁት ጉዳይ ጠብ እስከናካቴው ከምድረ-ገጽ መወገድ አለበት የሚል ነው። ሰላምን፣ ገነትን ፈጥረን መሄድ አለብን። እዚህ ላይ የነሱ ጥያቄ ምንድነው? ጠብ እንዴት ይቀራል ትላልህ? የሚል ነው። እኔም እንዲህ ስል መለስኩላቸው። ጠብ ስር የለውም። ጠብን እኛ ካወቅንበት ማስወገድ የኛ ነው። ጠብን እምንስለው እኛ ነን። ጠብን ከመሳል ይልቅ ፍቅርን እየሳልን መሄድ ይኖርብናል። ጠብን የሚያነሳሱ ሁለት ነገሮች ናቸው። እነሱም መጥፎ አሰራርና መጥፎ አነጋገር ናቸው። መጥፎ ቢናገሩን እንደማንወድ፣ መጥፎ ቢሰሩብን እንደማንወድ፣ በራሳችን ላይ እንዲደረግብን የማይገባንን ነገር በሰው ልጆች ላይ ማስወገድ ነው። ያን ጊዜ ጠብ የለም። እላቸዋለሁ።

ሌላው የጠየቁኝ ነገር ሰላም እንዴት ይመጣል ትላለህ? ብለው ነው። ሰላም የሚመጣው ሁሉም የሰው ልጆች ነጩም ጥቁሩም ሁሉም እህት፣ ሁሉም ወንድም ሆነን ከመካከላችን ችግር የደረሰበት ሰው ቢኖር ሁላችንም እጃችንን አንስተን የዚያን ሰው ችግር በማስወገድ ነው። ችግሩን ስናስወግድለት ደስታ ይሰማዋል። ገንዘባችን ደስታው ነው። ደስታውን መካፈል ያስፈልጋል። ከዚያ ተሳስበን ተዛዝነን ከሄድን ውስጥ ያለው ደስታ ነው። ደስታን ፈጠርን ማለት ሰላምን ፈጠርን ማለት ነው። ሰላምን ፈጠርን ማለት ደግሞ እምንፈልገውን ገነት ፈጠርን ማለት ነው። ይህን እራሳችን እምንሰራው ነው። ገነት እሚገኘው እዚህ ሳለን በሰራነው ስራ ነው። እዚያ ከሄድን በኋላ አይበስልም። ጠብን ማስወገድ ሰላምን መፍጠር ከሰማይ እንዲወርድልን አንጠብቅ። እዚሁ እኛ እምንፈጥረው ነው።

ይህን ተማምነንበት ስንቀጥል በአካባቢው ያሉ ሰዎች ይህ አልዋጥላቸው ብሎ መኖሪያ ቢያሳጡንም የተማሩ ሰዎች እስከሚያገኙት ድረስ ህይወታችን መስዋት አድርገን ስንታገል ቆይተናል። የተማሩ ሰዎች እነማን ናቸው? የሀይማኖት አባቶችም ይሁኑ የቀለም ምሁሮች ያገኙት ነው ይበሉ ያንሱት። አይደለም ካሉ ይተውት። እስከሚያገኙት ድረስ ግን ህይታችን መስዋት አድረገን ለተማሩ ሰዎች ማድረስ አለብን ብለን ሀሳባችን መስርተን ትግላችንን ቀጠልን። በአካባቢው ያሉ ሰዎች ይህ አልዋጥላቸው ብሎ መኖሪያ ቢያሳጡንም ትግላችን በዚያው በመቀጠል ስንሄድ እነሱ ሲያቅታቸው በደርግ ጊዜ በ1980 ዓ.ም. ወደ ፖለቲካው እያጋጩ ወያኔ የሚባል ስያሜ እያስጠጉ ሲሉ ደርግ ደግሞ እኛን ሊያጠፋ ሲመጣ እግሬ አውጭኝ ብለን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ተፈናቅለን ተሰደድን።

ስደት ባለበት ስራ የለም። ስራ በሌለበት ገንዘብ የለም። እሚበላ እሚጠጣ የለንም። ብንታመም እምንታከምበት የለንም። በዚህም ሳቢያ የሞቱ ወገኖቻችንን በየቁጥቋጦው ስር አፈር እያለበስን ዓላማችንን ለተማሩ ሰዎች ለማድረስ ትግላችንን ቀጠልን።

በ1985 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከስደት ስንመለስ መሬታችን በአካባቢው አርሶ አደሮች ተይዞ አገኘነው። መሬታችንን ለማስመለስ ለወረዳ፣ ለዞንና ለክልል ብናመለክትም ምላሽ አላገኘንም። ያገኘነው ምላሽ ቢኖር የመሬት ስሪቱ ሲመጣ ታገኛላችሁ የሚል ነበር። የመሬት ስሪቱ እስኪደርስ ድረስ ለቤተ-ቦታ የሚሆን ብሎ ወረዳው 17.5 ሄክታር ብቻ ሰጠን። የመሬት ስሪቱን መንግስት ለሁሉም እኩል እንዲደርስ ቢያወርድም ፊልድ የወጣው ቡድን ግን ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመደራደር መሬቱን ሊሰጠን አልቻለም። በመሆኑም ለስራ እጦት፣ ለእንግልት፣ ለረሀብ፣ ለበሽታ ተዳርገናል። ከዚህም በከፋ ሁኔታ በርካታ የሀሳብና የስራ አጋሮቼ ለህልፈተ-ህይወት ተዳርገዋል። በኋላም ህይወት የተንጠለጠለው በመሬት ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪም ማደግ ይቻላል ብለን በማሰብ በማኅበር ተደራጅተን ወደ ስራ ገባን። ነገር ግን በአዲስ አበባም መሬት እንዲሠጠንና ስራችንን እንድናስፋፋ እየጠየቅን ነው።

የዙምራ ማኅበረሰብ ላይብረሪዎችን፥ የእደ ጥበባትን፣ የሸማኔ መሳሪያዎችን፣ የሸማ ስራ ውጤቶችን፣ የአዛውንቶችን መኖርያ፣ መዋለ ህጻናት ይገኙበታል። 

የማኅበረሰቡ አስጎብኙዎች ብርቱካንና ጥሩሰው "በማኅበረሰቡ የተሰጠን የሥራ ኃላፊነት ማስጎብኘት ነው" ይላሉ። እያንዳንዱ የአካባቢው ነዋሪ ውጤታማ ይሆናል በተባለበት የሥራ ዘርፍ ይሰማራል። አንድ የአውራምባ ነዋሪ ጠዋት ከተነሳች ወይም ከተነሳ በኋላ ቤት ውስጥ ያለውን ሥራ አብሯት ከሚኖረው ወይም ከምትኖረው ሰው ጋር በጋራ ይወጣሉ። አስከትለውም ወደየተመደቡበት መደበኛ ሥራ ያቀናሉ። ብርቱካንና ጥሩሰውን ስናገኛቸው "የተመደበልን ሥራ ማስጎብኘት ይሁን እንጂ ሌላ ማከናወን የምንችለውን ሥራ ከመሥራትም ወደኋላ አንልም" ብለውናል።

ብርቱካን ክብረት “የጾታ እኩልነት ከሥራ ክፍፍል በዘለለ የአውራምባ ስም እየገነነ ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለአንድ ወገን የተለየ ሥራ አለመኖሩ ነው። 'የሴቶች ሥራ' እንዲሁም 'የወንዶች ሥራ' የሚለውን የተዛባ ክፍፍል አንቀበልም ይላሉ። ብርቱካን እንደምትለው በሴቶችና ወንዶች መካከል ጾታን መሰረት ያደረገ የሥራ ክፍፍል አለመኖሩ አንድ የማኅበረሰቡ መገለጫ ነው። በአንድ ቤት ውስጥ ወንድም ሆነ ሴት ልጅ እኩል የትምህርት እድል እንዲያገኙም ይደረጋል። በማህበረሰባችን የጾታ እኩልነት አለ ስንል መገለጫው የሥራ ክፍፍል ጾታን መሰረት አለማድረጉ ብቻ አይደለም። እኩል ሀሳብን መግለጽና ውሳኔ መስጠት ሌሎቹ መገለጫዎች ናቸው" ብላናለች። 

አስተያየት