ታህሣሥ 6 ፣ 2014

አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ክፍል

City: Addis Ababaጤናማህበራዊ ጉዳዮች

በድንገተኛ ክፍሉ የሚታዩት ክፍተቶች አዲስ አለመሆኑን የሚገለጹት የክፍሉ ባለሞያዎች በጊዜ ሂደት ዉስብስብ እየሆኑና ለስራው አስቸጋሪ በመሆን የቀጠሉ መሆናቸውን አጽናኦት ሰጥተዋል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ክፍል

ቸርነት ዳኛቸው በግንበኝነት ሙያ በቀን ስራ የሚተዳደር ወጣት ሲሆን በስራ ላይ ሆኖ በደረሰበት ጉዳት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ተወስዶ ህክምና እየተደረገለት ይገኛል። ቸርነት በክፍሉ ከሚገኙት አግዳሚ ወንበሮች በአንዱ ላይ ተኝቶ በባለሞያ እየተረዳ ቢሆንም የተኛበት ወንበር እግር ለመዘርጋት እንኳን የማይመች ሆኖበት ቁጭ ብሎ በህመም ስሜት ውስጥ ሲያቃስት ይታያል።

የህክምና ባለሙያዎቹም በከፍተኛ የአገልጋይነት ስሜት ከአንድ ታካሚ ወደ ሌላ ታካሚ፣ ከአንዱ ክፍል  ወደ ሌላ ክፍል ይሯሯጣሉ። በአዲስ ዘይቤ ምልከታ ወቅት ከ20 የማይበልጡ የህክምና ባለሙያዎች ታማሚዎችን ለማዳረስ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የታያሉ። ከነዚህ ዉስጥ ግማሽ ያህሉ የእጅ ጓንት እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አላደረጉም።

በክህምና ስፍራው ያለው ሁኔታ አስጨናቂ ስሜት እንደፈጠረበት የሚናገረው ቸርነት የህክምና ባለሙያዎቹ የቻሉትን ቢያደርጉም “ከታካሚዎች ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ አይመስለኝም፤ ይህ ደግሞ ተገቢውን ህክምና የማግኘቴ ነገር እንዲያሳስበኝ አድርጎኛል” ሲል ይናገራል። 

ከእዚህ ቀደም እንዲህ ያለ አደጋ ገጥሞኝ ወደ ሆስፒታል ገብቼ አላውቅም ያለው ቸርነት በተለያዩ አጋጣሚዎች ግን የተለያዩ የህክምና ተቋማትን ማየቱን ያስታዉሳል። “የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደዚህ ይሆናል ብዬ አስቤ አላውቅም፤ በድንገተኛ ክፍሉ ወዳድቀው የሚታዩት ቆሻሻዎች ሌላ በሽታ የሚፈጥሩ ይመስለኛል። የህክምና ተቋም በእዚህ ልክ የተዝረከረከ መሆን ያለበት አይመስለኝም።” ይላል።

የሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል በቂ የተፈጥሮ ብርሃን አያገኝም፤ በክፍሉ የተገጠሙት መብራቶችም ቢሆኑ አጥጋቢ በሚባል ደረጃ ብርሃን አይሰጡም። የክፍሉን የንጽሕና ሁኔታ ለታዘበውም የህክምና ተቋምነቱን የሚያሳጣው ይመስላል። የተጣሉ የህክምና ጓንቶች፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች፣ ጥቅም ላይ የዋሉ የንጽህና መጠበቂያ ወረቀቶች  በክፍሉ ወለል እዚም እዛም ወዳድቀው ይታያሉ።

በድንገተኛ ክፍሉ ዉስጥ ከ10 የማይበልጡ ታካሚዎች አልጋ ላይ ሆነው ህክምና ቢደረግላቸውም ያንኑ ቁጥር የሚያህሉ ታካሚዎች ደግሞ ካርቶኖች እና አነስተኛ ጨርቆች በተነጠፉባቸው ለወትሮዉ ለወረፋ እና ለአስታማሚዎች በተዘጋጁ አግዳሚ ወንበሮች ላይ ጋደም ብለው በባለሞያዎች ክትትል ሲደረግላቸዉ ያታያል።

አይደለም ለማስታመም ለሚመጡ ቤተሰቦች፤ ለታካሚዎች እንኳን ምቹ ባልሆነው የህክምና ስፍራ የተወሰኑ አስታማሚዎች ወንበሮችን ለታማሚዎች ለቀው በመተላለፊያ መንገዱ ወለል ተቀምጠዋል፤ የተወሰኑት ደግሞ ከሚያስታምሙት ቤተሰባቸዉ ጋር ተጠጋግተው በአግዳሚ ወንበሮች ላይ ይታያሉ።

በጣት የሚቆጠሩ የድንገተኛ ህመም ታካሚዎች ደግሞ በዊልቼር ላይ ተቀምጠው እዚም እዛም የሚሯሯጡት የህክምና ባለሙያዎቻቸውን በጉጉት ይጠባበቃሉ። አብዛኛዎቹ ታካሚዎች የግልኮስ መሸከሚያ ብረቶችን ከጎናቸው አድርገው እጆቻቸው ላይ የማስተላለፊያ ገመዶቹ ተጠምደዉላቸው አረፍ ብለዋል።

የድንገተኛ ህክምና ክፍሉ ከመግቢያው ጀምሮ ለአገልግሎት አሰጣጥ አመቺ ባልሆነ መልኩ በሚሯሯጡ ታማሚዎች፣ አስታማሚዎች እና የህክምና ባለሙያዎች ተጨናንቋል። በርካታ ታማሚዎች እና አስታማሚዎቻቸው ሲወጡ እና ሲገቡ ቢታይም ከ10 እስከ 15 በሚሆን ደቂቃ ምልከታ ውስጥ ከ30 በላይ የሚሆኑ ታማሚዎች በድንገተኛ ክፍሉ ሲስተናገዱ አዲስ ዘይቤ  ለመታዘብ ችላለች።

የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ክፍል የተለዩ አደጋዎች የሚከሰቱባቸውን ክስተቶች ሳይጨምር በመደበኛ ቀናት ላይ በየቀኑ ከ90 ያላነሱ ታካሚዎችን እንደሚያስተናግድ በክፍሉ ከሚሰሩ የህክምና ባለሞያዎች አዲስ ዘይቤ ማረጋገጥ ችላለች።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እያገለገለች የምትገኛ የህክምና ባለሙያ እንደገለጸችው፤ ሆስፒታሉ 100 ሺህ ታካሚዎችን ለማስተናገድ የተዘጋጀ መሰረተ ልማት እና የሰው ኃይል ያለው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት ለሚመጡ በቁጥር ላልተገደበ ተገልጋዮች ህክምና ለመስጠት እየጣረ የሚገኝ እንደመሆኑ በሆስፒታሉ የሚታየው መጨናነቅ የሚጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ በድንገተኛ የህክምና ክፍል ያለው ሁኔታ እጅግ የከፋ መሆኑን ትገልጻለች።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ያለው የስራ ሁኔታ ለሰራተኞችም ሆነ ለተገልጋዮች ምቹ አለመሆኑ በግልጽ የሚታይ  ነው። እነዚህ ሁሉ ክፍተቶች የሚስተዋሉበት አንጋፋው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና ባለሞያዋ እንደገለጸችው ጥቂት የማይባሉ ህክምናዎችን በብቸኛነት እንደሚሰጥ እና በርካታ ታማሚዎችን ከመላው ሃገሪቱ ክፍሎች ለማስተናገድ የተቋቋመ እንደመሆኑ ላያስገርም ይችላል።

ይሁን እንጂ የህክምና ባለሞያዎች ባለው ሀብትም ቢሆን የመጣውን ታካሚ በሙሉ ለማስተናገድ የሚጥሩበት ሁኔታ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከባለሞያዎቹ አቅም በላይ የሆኑ ክፍተቶች ችላ የሚባሉ አለመሆኑን ከሀኪሞች አንደበትም ከአዲስ ዘይቤ ምልከታም መገንዘብ ይቻላል።

በሆስፒታሉ የሚገኘው የድንገተኛ ህክምና ክፍል የንጽህና ጉድለቱ በርካታ ታማሚዎች የሚስተናገዱበት በመሆኑ ለተለያዩ ተጨማሪ ተላላፊ ህመሞች የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው። በተጨማሪም ለታካሚዎች አገልግሎት የተዘጋጁት የመጸዳጃ ክፍሎች ከንጽህና ጉድለታቸው በላይ የታማሚዎችን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ አለመሆኑን አዲስ ዘይቤ ያናገረቻቸው የድንገተኛ ክፍል ሀኪሞች ይገልጻሉ።

የድንገተኛ ህክምና ክፍሉ የስራ ቦታ ምቹ ካለመሆን በተጨማሪ ካሉበት ችግሮች ዋነኞቹ የህክምና ተቋምን የማይመጥን ንጽሕና፣ በቂ የዉሃ አቅርቦት አለመኖር፣ እንደ ጓንት፣ ጥጥ፣ የቁስል ማሸጊያ (ሰርጂካል ፕላስተር)፣ የባክቴሪያ ማጽጃ ኬሚካሎች (Antiseptics) የመሳሰሉ ራስን የመጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት እንዲሁም ለድንገተኛ ህክምና በቂ ያልሆነ የላብራቶሪ አገልግሎትና የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ እጥረት ይገኙበታል።

በክፍሉ የምትሰራ የህክምና ባለሙያ እንደገለጸችው፤ ከእዚህ ቀደም በሆስፒታሉ ሲቀርብላቸው የነበረው የህክምና ጓንት በአሁኑ ሰዓት ታካሚዎች ወደ ህክምና ባለሞያቸው ሲቀርቡ ባለሞያው የሚጠቀምበትን የህክምና ጓንት  ገዝተው መቅረብ አለባቸው።

ይህ ካልሆነ በቻሉት አቅም ባለሞያዎቹ ጓንት ለማግኘት የሚጥሩ ሲሆን አንዳንዴ ጓንቱ ማገልገል ከሚገባው ሰዓት በላይ ጥቅም ላይ እንዲዉል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ።

በድንገተኛ ክፍሉ የሚታዩት ክፍተቶች አዲስ አለመሆኑን የሚገልጹት የክፍሉ ባለሞያዎች በጊዜ ሂደት ዉስብስብ እየሆኑና ለስራው አስቸጋሪ በመሆን የቀጠሉ መሆናቸውን አጽናኦት ሰጥተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በድንገተኛ ክፍሉ የሚሰሩ ባለሞያዎች፤ እነዚህን ክፍተቶች ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሳል ብለው አሁንም ተስፋ አድርገው ከሚጠብቁት ጉዳይ፤ ሆስፒታሉ የሚያስገነባው የድንገተኛ ህክምና መስጫ ማዕከል ቀዳሚው ነው።

የድንገተኛ ህክምና ማዕከሉን ግንባታ ለሚከውነው የግንባታ ስራ ተቋራጭ ድርጅትም በ2007 ዓ.ም. ውሉን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲረከብ በአንድ ዓመት ዉስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ የግንባታ ሂደቱ ከተቋረጠ ከዓመት በላይ እንደሚሆን በአሁኑ ሰዓት በድንገተኛ ክፍሉ የሚያገለግሉ ባለሞያዎች ገልጸዋል። አዲስ ዘይቤ በክፍሉ የስራ ሁኔታ እና በአዲሱ ህንጻ የግንባታ ሂደት ላይ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

በአዲስ ዘይቤ ቅኝት ወቅት ሃሳባቸውን የሰጡ የህክምና ባለሞያዎች እና ታካሚዎች፤ በጊዜያዊነት ችግሩን የሚቀርፍ ለምሳሌ የህክምና መገልገያዎችን ለሀኪሞችና ለታካሚዎች በበቂ ሁኔታ ማቅረብ፣ ህክምናው የሚሰጥበትን ከባቢ ንጹህ ማድረግ የሚያስችል አሰራር መፈጠር እንደሚገባው ገልጸዋል።

አስተያየት