ታህሣሥ 18 ፣ 2014

የዶ/ር ህይወት መስፍን ህልፈት ውዝግቦች ዳሰሳ

City: Addis AbabaNews

የሟች ወላጅ እናት እንደሚገልጹት የአዲስ አበባ ፖሊስ በፈለገው ጊዜ የአስክሬን ምርመራ ውጤት ሶፍት ኮፒው ከቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ጠፍቷል መባላቸውን ይገልጻሉ።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የዶ/ር ህይወት መስፍን ህልፈት ውዝግቦች ዳሰሳ

‘ሸገር ኢንፎ’ በተሰኘ የዩቲዩብ ቻነል ታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ላይ በተሰራጨው ቪድዮ የሟች ዶ/ር ህይወት መስፍን ወላጅ እናት መሆናቸዉን የገለጹ ወ/ሮ ጽዮን ደረሰብኝ ያሉትን በደል ሀዘን በተመላበት ስሜት ያስረዳሉ። ወ/ሮ ጽዮን በቃለ ምልልሱ ወቅት ጥቁር ነጠላ ለብሰው፣ በእንባ ታጅበው እና ለካሜራው ጀርባቸዉን ሰጥተው ስለ ልጃቸው አሟሟት በመግለጽ “የፍትሕ ያለ” ብለዋል። 

ከእዚህ ቪድዮ መለቀቅ በኋላ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በርካታ ግለሰቦች እንዲሁም ቡድኖች ገጾቻቸዉ የሟቿ ምስል ላይ 'ፍትሕ ለዶ/ር ህይወት' በሚሉ ጽሁፎች እና ምስሎች በስፋት ሲዘዋወሩ ቆይተዋል፤ አሁንም እይተዘዋወሩ ይገኛሉ። በአጠቃላይ የወጣቷ ዶክተር ህልፈት ኢፍትሃዊ ነው በሚሉ አስተያየቶችና ፅሁፎች በማህበራዊ ሚድያው ገነው ሰንብተዋል። በህልፈቷ ዙሪያ ተጠያቂ በተደረጉት ተቋማት፣ በተነሱት እውነታዎች እንዲሁም ወላጅ እናት ባቀረቡት ሀተታዎች ዙሪያ በተለያዩ ያልጠሩ ውዝግቦች ታይተዋል። እነዚህን ብዥታዎች ለማጥራት በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ወገኖችን በማናገር፣ መረጃዎችን በመመልከት እንዲሁም የህግና የህክምና ባለሙያዎችን በማማከር ይህን ዳሰሳ ለማቅረብ ተሞክሯል።

በዚህም መሰረት መጀመሪያ ልናገኛቸው የሞከርነው የሟች ዶ/ር ህይወት መስፍን እናት ወ/ሮ ጽዮን ተጨማሪ ቃለ መጠይቅ ለመደረግ እንደማይፈልጉና በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ የጠቀሷቸውን መረጃዎች እንድንጠቀም የነገሩን ሲሆን፣ “እኔ ድምጼ እንዲሰማ ነበር የፈለግኩት፤ ድምጼ ተሰምቶልኛል አመሰግናለሁ” በማለት መልሰዉናል።

የባለታሪኳ ወላጅ እናት ወ/ሮ ጽዮን በቃለ መጠየቃቸው ወቅት ልጃቸው ዶ/ር ህይወት በጥር 19 2009 ዓ.ም. በህክምናው አጠራር ‘Cleansing Enema’ የሚባለውን ለሆድ ድርቀት ታማሚ የሚሰጥ የትልቁ አንጀት እና የፊንጢጣ እጥበት (በተለምዶ የሆድ እጥበት) ህክምና ለማግኘት በወቅቱ ቦሌ ካርጎ አካባቢ በሚገኘው (አሁን ልደታ ኮካኮላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው) አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል መሄዷን ገልጸዋል።

በእጥበት ላይ ሆና ከእናቷ ወንድም ጋር ተደዋውለው እየታጠበች እንደሆነና ልትጨርስ መሆኑንም ነግራዋለች። ታካሚዋ ዶ/ር ህይወት ከአሚን ሆስፒታል ወደ ሃሌሉያ ሆስፒታል ተወስዳ የሆስፒታሉ ባለሞያዎች ‘የሚቻል አይመስልም ግን እንሞክራለን’ እንዳሏት የምትገልጸው እናት፤ እጥበቱ እየተደረገላት ባለበት ሰዓት ትንሽ ጨለምለም አለብኝ ብላ ራሷን መሳቷን ህምናውን ከሰጠቻት ነርስ ተነግሮኛል ብላለች።

አዲስ ዘይቤ ከአሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ባገኘችው መረጃም በሆስፒታሉ የዶ/ር ሕይወት መስፍንን ሕይወት ለማትረፍ የሚቻለውን ሁሉ አድርገናል ያሉ ሲሆን፣ በወቅቱ የአተነፋፈስ ችግሯ እየተባባሰ ሲመጣ ለተሻለ የመተንፈሻ ችግር ህክምና አገልግሎት በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ሃሌሉያ ሆስፒታል በራሳቸው ባለሙያዎችና አንቡላንስ ይዘው መሄዳቸው ታውቋል።

በተዘዋወረችበት ሆስፒታልም ዶ/ር ህይወትን የማዳን ሂደት ቢቀጥልም ከሰዓታት በኋላ የዶ/ር ህይወት መስፍን ህይወት ማለፍ ለቤተሰቧቿ ተገለጸ። ቤተሰቦቿ ከፖሊስ ያገኙትን የአስከሬን ምርመራ ውጤት በመያዝም በጊዜው ክስ መስርተዋል።

የዶ/ር ህይወት ወላጅ፣ አሚን ጄኔራል ሆስፒታልና ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ

የዶ/ር ህይወት ወላጅ እናት እንደሚገልጹት የአስክሬን ምርመራው በህክምና ሂደት ሳይሆን “በቀጥታ ተደብድባ” መሞቷን ያሳያል ብለዋል። ለእዚህ ማሳያ የሚያደርጉትም በሟች ጭንቅላት ላይ የመበለዝ ምልክትና የውስጥ ደም መፍሰስ መኖር፣ ሁለቱም እጆቿ እና አስሩም የጣት መደቦቿ መበለዝ፣ ሌሎች በውስጥ አካላቷ ላይ ደርሰዋል ያሏቸውን ጉዳቶችም ወ/ሮ ጽዮን ዘርዝረዋል።

አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል በአስክሬን ምርመራው ላይ የተጠቀሱትን እና በሟች እናት ዶ/ር ህይወት ላይ ድብደባ እንደተፈጸመ ያመለክታሉ ያሏቸውን አካላዊ ጉዳቶች ሲያስረዳ፣ “የቆየ ተደጋጋሚ የነስር ሕመም ያስቸግራት እንደነበረ፣ የደማው የውስጥ አካላቷ እንደሆነ፣ የጭንቅላት ውስጥ አካል መድማት እንደነበረባት፣ ደረቷ ላይና ከጡቷ በታች ያለው መቧጨር ትንፋሽዋን ለማስነሳት ደረት ላይ የሚደረግ ልብን ደጋግሞ በመጫን የሚደረግ (CPR) በተደረገበት ጊዜ የተከሰተ መሆኑ እንዲሁም የጣቶችዋ መበለዝ ከማንኛውም የልብ ሥራ መስተጓጐልና ሞት በኋላ የሚከሰት መሆኑም በተደጋጋሚ ተገልጾላቸዋል” በማለት ሆስፒታሉ ገልጿል።

“ዶ/ር ህይወት አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል በቆየችበት ጊዜ መጀመሪያ ያያት ሐኪም ድርቀት እንዳለባት አረጋግጦ የሆድ እጥበት ከመስጠት ውጪ አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ለተከሰተው ችግር መንስኤ የሚሆን አንድም ኬሚካል ወይንም የሚዋጥ መድኃኒትም ይሁን መርፌ ያልተሰጣት መሆኑም በተደጋጋሚ ተገልጾላቸዋል” ሲሉ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አክለው ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

ፖሊስ የወንጀል ክስ ለመመሥረት የሀኪሞች ቦርድ ውሳኔ ያስፈልጋል ቢልም የቦርዱ ውሳኔ 1 ዓመት ከ7 ወራት መፍጀቱን ወ/ሮ ጽዮን በቃለ መጠይቁ ተናግረዋል።

የሀኪሞች ቦርድ የሰጠው ውሳኔ፣ ‘የዶ/ሯ ህይወት ያለፈው በደም መፍሰስ እንደሆነና የደም መፍሰሱ ምክንያት ለሌላ ሳይንሳዊ ምርመራ ክፍት ተደርጓል’ ተብለናል ያሉት ወ/ሮ ጽዮን፤ ዉሳኔው የአስክሬን ምርመራውን ወደ ጎን ያደረገ ነው ብለዋል።

በአስክሬን ምርመራው ዉጤት ላይ እንደተገለጸው ‘ሁሉም ቁስለቶች ከሞት በፊት የተከሰቱ ናቸው፤ የሞቱን መንሳኤ በተመለከተ ደግሞ የደረሰባት ጉዳት ባስከተለው የሳንባ መጠጠር የአተነፋፈስ ሂደት በመታወኩ ህይወቷ አልፏል።’ እንደሚል በወ/ሮ ጽዮን እጅ የሚገኘው መረጃ ያሳያል።

የሟች ወላጅ እናት እንደሚገልጹት የአዲስ አበባ ፖሊስ በፈለገው ጊዜ የአስክሬን ምርመራ ውጤት ሶፍት ኮፒው ከቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ጠፍቷል መባላቸውን ይገልጻሉ።

በአንፃሩ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ‘ህዝብ እንዲያውቅልን’ ሲል በይፋዊ የማህበራዊ ገጹ ባሰራጨው ጽሁፍ፤ ወ/ሮ ጽዮን ጠፍቷል ተብለናል ያሉት የአስክሬን ምርመራ ውጤትን በተመለከተ “የማቿ የሞት ምክንያት መረጃ በፍጹም አልጠፋም። መረጃዎችን የምንይዝበት የራሳችን የዘመነ አሰራር አለን። ከዚህ ቀደም ለሚመለከተው የሰጠነው ሕጋዊ ማስረጃ በከፍተኛ ባለሙያዎች ምስክርነት የተሰጠ ነው። አሁንም ቢሆን የዶ/ር ሕይወትን የሞት ማስረጃ የሚፈልግ በሕጉ መሰረት መስጠት ይቻላል።” ሲል ገልጿል።

ከእዚሁ ጋር በተያያዘ ወ/ሮ ጽዮን ከአዲስ አበባ ከተማ የምግብ የመድኀኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በሰጣቸው ደብዳቤ፣  “ሆስፒታሉ የህይወት አድን ግብአቶችን አሟልቶ ባለመገኘቱና የጤና ባለሙያዎችን የክህሎት ክፍተት እየፈተሸ ብቁ ማድረግ ላይ ችግር ያለበት በመሆኑ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል” የሚል አስተያየት ታክሎበታል ብለዋል።

በአጠቃላይ ጉዳዩ ላይ አዲስ ዘይቤ ያናገረቻቸው የአሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ፤ “ከሆስፒታላችን ጋር የተገናኘ ተመሳሳይ ታሪክ በመኖሩ እንጂ ከሰሞኑን በስፋት በተዘዋወረው ቃለ መጠይቅ ላይ ያሉት ሴት የሟች ወላጅ እናት መሆናቸውን እርግጠኛ ሆነን አይደለም መረጃውን የሰጠናችሁ” ብለውናል።

አሚን ሆስፒታል ይፋ ባደረገው መግለጫው ላይ፣ “የሙያ ሥነ-ምግባር በጎደለው መልክ ተዘጋጅተውና መሃረብ ይዘው ለቀረጻ በመቅረብ አብረው በማልቀስና በማላቀስ ተራኪዋ መልካቸውን በመደበቅ ጀርባቸውን ሰጥተው እንዲቀመጡና አምነው ለሚያቀርቡት ክስ እንኳን እንዲደባበቁ በማድረግ የተናገሩትን ሁሉ እውነት ለማስመሰልና እውነት ለማላበስ የተመረጡ ስሜትን ሊኮረኩሩ የሚችሉ ጥያቄዎችን ሰጥቶ በመምራት የተሳሳተ ግንዛቤ ማህበረሰቡ እንዲይዝ የሄዱበት ርቀት ከስም ማጥፋትና ዝና ከማጉደፍም በላይ ነው።” ብሏል።

“አሁን ከ (አምስት) ዓመት በኋላ እየተናፈሰ ያለው ጉዳይ በየደረጃው ባሉ የፌደራል የመድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም በየደረጃው ባሉ የሕክምና ቦርድና የሕክምና መማክርት ጉባኤዎች ሙያዊ ውሳኔ የተሰጠበት፣ ከፖሊስ ጣቢያ አንስቶ እስከ ፌደራል ወንጀል ምርመራና ፌደራል አቃቤ ሕግ ቀርቦ በከፍተኛ ደረጃ የታየና ውሳኔ የተሰጠበት አሚን አጠቃላይ ሆስፒታልን የሚያስጠይቅ የተለየ ወንጀል ያልተገኘበትና ተጣርቶ ያለቀ ጉዳይ ነው፣” ያለው ሆስፒታሉ “ፍርድ ለማዛባት የሚደረግ ስምና ዝናን ማጉደፍ በሕግ ያስጠይቃል።” ሲልም ገልጿል። አዲስ ዘይቤም ይህንኑ ቃል ከሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ መስማት ችላለች።     

አሁን እየተካሄደ ያለውን ጉዳይ በሙሉ አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል “የሆስፒታላችንን ስምና መልካም ዝና ለማጠልሸት በተለያዩ የማህበራዊ ገጾች እየተናፈሰ ያለውን ውሸትና ቲያትር ተመልክተነዋል” በማለት ነው የገለጸው።

እንዲሁም “የወንጀል ክስ የማይሆንላቸው መሆኑን ሲረዱ ልጄ ሐኪም ነበረች ስለዚህ 3.5 ሚሊዮን ብር የካሳ ገንዘብ ሊሰጠኝ ይገባል በማለት በተደጋጋሚ አማላጅ በመላክ ሳይሳካላቸው በፍርድ ቤት በፍትሃብሔር ለካሳ ክፍያ ከስሰው የፍርድ ቤቱ የክርክር ሂደት ላይ እያለን የውሳኔ ጊዜው ሲቃረብ አምስት ዓመት ጠብቀው የተለመደ ድራማቸውን ሊያሳኩላቸው የሚችሉ ማመዛዘን የጐደላቸው ግልብ ማህበራዊ ሚድያዎችን መርጠው ቀርበዋል።” በማለት አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ምላሽ ሰጥቷል።

በህክምና ስህተት ዙሪያ የሙያ ስነ-ምግባር እና ህጉ ምን ይላል?

ይህን ጉዳይ በተመለከተ አዲስ ዘይቤ የኢትዮጵያ የህክምና ሕግ እና ሥነ ምግባር ማህበር መስራች እና ፕሬዝዳንት የሆኑትን ዶ/ር መልካሙ መዓዛን አናግራለች። ባለሙያው እንደሚገልጹት በጤና ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ ጉዳት የሚያስከትሉ ክሥተቶች በሁለት ይከፈላሉ።

“መከላከል የሚቻሉ” ወይም “የህክምና ግድፈት” ክስተቶች ስህተት ቢፈጠርም በታካሚ ላይ ጉዳት የማያስከትሉ ሲሆኑ ይኼውም የታቀደውን አገልግሎት በአግባቡ ካለመተግበር (የአፈፃጸም ግድፈት) ወይም ትክክለኛውን አገልግሎት ካለማቀድ (የፕላን ግድፈት) ሊመጣ ይችላል። 

“መከላከል የማይቻሉ” ክስተቶች የሚባሉት ደግሞ ከሕክምና ግድፈት ውጪ በተፈጥሯዊ ሂደት የሚመጡ መሆናቸውን ዶ/ር መልካሙ ገልጸዋል። 

እንደ ዶ/ር መልካሙ ገለጻ የሕክምና ግድፈት ግልጽ (በቦታው የተፈጸመ) ወይም የተዳፈነ (ከቦታው ውጭ የተፈጸመ) ሊሆን ይችላል። ግልጽ ግድፈት በጤና ባለሙያው በቀጥታ የሚፈጸም ሲሆን፤ የተዳፈነ ግድፈት ደግሞ ከጤና ባለሙያው ውጭ ባለ የአሠራር ሰንሰለት ውስጥ ከተፈጸመ በኋላ፣ ዘግይቶ ውጤቱ በግልጽ የሚከሠት ይሆናል። 

በጤና አገልግሎት ወቅት ለሚደርስ አደጋ ቅርቡ ምክንያት የባለሙያው ግልጽ ግድፈት ቢሆንም፣ አብዛኛው ግልጽ ግድፈት እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያደርገው ቀድሞ የተፈጸመና የተዳፈነ ግድፈት መሆኑን ጥናቶች ያስረዳሉ። ከዚህ በመነሣት፣ በጤና ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ አብዛኛው የሕክምና ግድፈቶች ምንጭ አጠቃላይ የአሠራር ሥርዓቱ ችግር ነው ብሎ መደምደም ይቻላል ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ሌላኛው የህክምና ስህተት መንስኤ የሚሆነው የሕክምና ቸልተኛነት ነው። የህክምና ቸልተኛነት የሚባለው ከጤና አገልግሎት ደረጃ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወዘተ. ወይም በተመሳሳይ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይተገብራሉ ተብሎ ከሚገመተው አሠራር አኳያ ሙያዊ ኃላፊነት ካልተወጣና በሕግ የተቀመጠውን የቸልተኛነት መስፈርት ካሟላ ነው። በህክምና ቸልተኛነት የሚከሰቱ ግድፈቶች ከአጠቃላይ ስህተቶች ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚሆን ድርሻ እንዳላቸው ባለሙያው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዝቅተኛና መሀከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ሆስፒታሎች ውስጥ 134 ሚሊዮን ጉዳት የሚያደርሱ ክሥተቶች እንደሚፈጠሩና በዚህ ምክንያት 2.6 ሚሊዮን ታማሚዎች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የተገለጸ ሲሆን፤ ከመድኃኒት ጋር የተያያዙ ግድፈቶች በዓመት 42 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚያደርሱ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ አድርገው ዶ/ር መልካሙ አብራርተዋል።

የሕክምና ስሕተት ሲፈጸም ቀዳሚው ተጎጂ ታካሚው ሲሆን፣ ይኼውም የደረሰው የጤና፣ የአካል፣ የሕይወት፣ የኢኮኖሚ፣ የሞራልና የሥነ ልቡና ጉዳት በሚያስከትለው ኪሳራ ይገለጻል። ሁለተኛው ተጎጂ ደግሞ ስሕተቱን የፈጸመው ጤና ባለሙያ ሲሆን፤ ይህም የጥፋተኝነት ስሜት፣ የመንፈስ መረበሽ፣ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የመግባት ችግር ሊያስከትል ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ አጠቃላይ የጤና ሥርዓቱ እና የሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ በቀላሉ የማይገመት ነው።

የጤና ባለሙያዎች፣ የታካሚዎችና የሕክምና ተቋማት ኃላፊነትና ተጠያቂነትስ?

የጤና ባለሙያዎች፣ የታካሚዎችና የሕክምና ተቋማት ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ከውል፣ ከሕግ ወይም ከሥነ ምግባር መርሆች ሊመነጭ እንደሚችል የሚገልጹት ዶ/ር መልካሙ መአዛ ይህም ጉዳት ሲደርስ ኃላፊ የሚሆነውን አካል ለመለየት እንደሚያስችል ያስረዳሉ። የሐኪም ወይም የተቋማት እና የታካሚ ግንኙነት ከውል የመነጨ ግንኙነት የሚባለው ሁለቱም ወገኖች በፍላጎትና በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርተው በጽሑፍ፣ በቃል ወይም በድርጊት የሚያደርጉት ስምምነት ነው። 

የጤና ባለሙያዎች ዋነኛ ኃላፊነት ሙያው በሚፈቅደው መጠን ደረጃውን የጠበቀና ሥነ ምግባር የተላበሰ አገልግሎት መስጠት ሲሆን፤ በምርመራም ሆነ ሕክምና ወቅት በሚሰጠው ውሳኔ ዙሪያ ጥቅምና ጉዳትን በማስረዳት፣ የጎንዮሽ ጉዳት ካለው እና አማራጭ ሥነ-ተግባር ወይም ህክምና ካለ ታካሚውን በማሳተፍ እንዲሁም ጥያቄዎችን እንዲጠይቅ በማድረግ በራሱ እንዲወስን ዕድሉን የማመቻቸት ግዴታ አለበት።

የታካሚ ዋነኛ ግዴታ ደግሞ በራሱ ጤና ጉዳይ የመወሰን ሙሉ መብት እንዳለው ተገንዝቦ ጤናውን በተመለከተ ለሐኪሙ የሚሰጠው መረጃ ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ፣ በሚረዳው ቋንቋ መረጃ እንዲሰጠው መጠየቅ እና በጤና ባለሙያ የሚሰጥ ማንኛውም ትዕዛዝ ወይም ምክር ሲኖር በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ መሆናቸውን ዶ/ር መልካሙ ይገልጻሉ።

የሕክምና ተቋማት ኃላፊነት ደግሞ ሲቋቋሙ በየደረጃቸው ክሊኒክ፣ ሆስፒታል፣ አጠቃላይ ሆስፒታል እንዲሁም ልዩ ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ያወጣውን ዝቅተኛ መስፈርት በመሰረተ ልማት፣ በሰው ኃይል እንዲሁም በስራ ቦታ ማሟላት የሚጠበቅባቸው ሲሆን በደረጃቸው ልክ ለሚከሰቱ የህክምና ግድፈቶች ተጠያቂ ይሆናሉ። 

በተጨማሪም ታካሚዎች አንድ ጊዜ ካርድ ሲያወጡ ከተቋሙ ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል ስለሚባል ለታካሚዎች ደረጃውን፣ ህጉን እና ሥነ ምግባርን የጠበቀ ህክምና ለመስጠት ይገደዳል። በተጨማሪም ተቋማት የታካሚን ትክክለኛ ማስረጃ ማስፈር፣ መጥፋትና መበላሸትን ለማስቀረት በአግባቡ ማስቀመጥ እና ለሚመለከተው አካል እንደአስፈላጊነቱ ማቅረብ ግዴታቸው ነው።    

የሐኪም/ የተቋማት እና የታካሚ ግንኙነት ከሕግ የሚመነጨው የሕይወት አድንና ድንገተኛ የጤና ችግር በሚያጋጥም ጊዜ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት ማንኛውም ባለሙያ ወይም ተቋም አስፈላጊውን ምርመራና ሕክምና ለድንገተኛ ታካሚ በማድረግ ሕይወት የማዳንና አካል ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ግዴታ እንዳለበት በህግ ተቀምጧል።

የወንጀል እና የፍትሐብሔር ተጠያቂነትን በተመለከተ

በሕክምና ስህተት ጉዳት ደረሰብኝ የሚል አካል 4 ነገሮችን ማሟላት የግድ ይሆናሉ። የሐኪም/ ተቋም እና የታካሚ ግንኙነት መኖርን ማረጋገጥ፣ ባለሙያው ወይም ተቋሙ ኃላፊነቱን አለመወጣት፣ ባለሙያው/ ተቋሙ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ጉዳት እንደደረሰበት መግለጽ እንዲሁም በደረሰበት ጉዳት ምክንያት የገጠመውን የሞራል፣ የገንዘብ፣ የጤናና የአካል ጉዳት ማስረዳት እንደሚጠበቅበት የህክምና ህግ ባለሙያው ገልጸዋል። 

ከእነዚህ ውስጥ የሙያ ግንኙነት፣ ኃላፊነትን ባለመወጣት የደረሰ ጉዳት እና በጉዳቱ ሳቢያ ታካሚ የደረሰበት ችግሮች በህግ አግባብ የሚታዩ ሲሆን ኃላፊነትን አለመወጣት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የሕክምና ሙያ ሥነ ምግባር ኮሚቴ የሚታይ ሲሆን ሙያዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ምክረ ሀሳብ የሚያቀርቡ ይሆናል። 

የሕክምና ስህተቱ ወንጀል ነክ ሳይሆን ሲቀር እና በተከሰተው ስህተት ታካሚ ኪሳራና ጉዳት ደርሶብኛል፤ ካሳ ሊከፈለኝ ይገባል ካለ ጉዳዩ በፍትሃብሔር ክስ የሚታይና ውሳኔ የሚያገኝ ይሆናል። በወንጀል ህግ የሚታየው ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ከተከሰተ ነው። ይህም የሚመዘነው በሙያው መደረግ የሌለባቸውና ያልተለመዱ ጉልህ ስህተቶች ከተፈጠሩ ወደ ወንጀል ክስ ይመራሉ። 

ለሞት የሚያበቁ ምክንያቶችን በተመለከተ

የመጀመሪያው ክሊኒካል ምክንያት ሲሆን ለሟቹ ምርመራና ሕክምና በሚደረግበት ወቅት ከተከሠቱ የሰውነት አሠራር ሥርዓት ችግሮች በመነሳት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የአስክሬን ምርመራ ውጤት Pathological/ Post mortem ሲሆን የሟቹ አካል ክፍሎችና የሰውነት ፈሳሾች ላይ በሚደረግ የፓቶሎጂ ምርመራ ነው። ዶ/ር መልካሙ እንደሚገልጹት ክሊኒካል ምክንያትና የአስክሬን ምርመራ ውጤት ሊለያይ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለና በአንዳንድ የበሽታ ዓይነቶች እስከ 60% የሚደርስ ልዩነት ሊታይ እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ። 

ሶስተኛው ምክንያት ከሕግ ጋር የተያያዘ ፓቶሎጂ ምርመራ Forensic Pathology ሲሆን ይህ የሚሆነው የአስክሬን ምርመራውን ከአካባቢያዊ፣ የአይን ምስክሮች፣ የፎቶ፣ የቪዲዮ፣ የፖሊስ ምርመራ ወ.ዘ.ተ ጋር አመሳክሮ ማጠቃለያ በመስጠት ነው። የመጨረሻው ሕጋዊ ምክንያት Cause- Effect ሲሆን የተለያዩ ሕጋዊ መመዘኛዎችን ተጠቅሞ ከሞት ጋር ያለውን ግንኙነት በመገምገም የሚከወን ነው።

የሕክምና ስሕተት እንዳይከሠት በዘላቂነት ምን ይደረግ?

ባለሙያው ዶ/ር መልካሙ መአዛ እንደሚመክሩት የታካሚን ደህንነት የሚያስጠብቅ የስራ ባህል መፍጠር፣ በሳይንሳዊ ዕውቀትና ሥነ ምግባር የበቁ ባለሙያዎች ስልጠና ላይ ትኩረት ማድረግ፣ የተቋማትን አመራር ብቃትና ክህሎት ማሳደግ፣ ባለሙያዎችና የሥራ ክፍሎች መረጃ በግልፅ የሚለዋወጡበት ጤናማ የስራ ግንኙነት ማፍጠር፣ የግድፈት መረጃ ቋት በተቋምና በፌዴራል ደረጃ ማቋቋም ዋነኞቹ ናቸው።

አስተያየት