ታህሣሥ 27 ፣ 2014

ለተፈናቃዮዎች በሚል የሚሰበሰቡ ድጋፎች ለተረጂዎች በአግባቡ እየደረሱ አይደለም ተባለ

News

ድጋፍ ማቅረብ የሚፈልጉ አካላት የሚያቀርቡትንም ነገር ራሳቸው ማዘጋጀት ይችላሉ

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ለተፈናቃዮዎች በሚል የሚሰበሰቡ ድጋፎች ለተረጂዎች  በአግባቡ እየደረሱ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶች መዳረጋቸውን ተከትሎም በተለያዩ አካላት ድጋፎች እየተሰባሰቡ ይገኛሉ።

የአደጋው ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍ በሚደረገው ርብርብ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ማህበራት፣ ተቋማት እንዲሁም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዘርፎች እና የእርዳታ መንገዶች  እያከናወኑት የሚገኙት ተግባር መልካም ውጤት እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገልጿል።

ይሁን እንጂ የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ትምህርትና ጤናን ጨምሮ ከተለያዩ ዘርፎች ጋር በመቀናጀት የሚያቀርበው የድጋፍ ስራ ላይ እክል ሊፈጥሩ የሚችሉ አካሄዶች መኖራቸውን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

ከኮሚሽኑ ጋር የመረጃ ትስስር ሳይፈጥሩ ለድጋፍ ያዘጋጇቸውን ቁሳቁስ ራሳቸው ሄደው መስጠት የሚፈልጉ እና ይህንንም የሚያደርጉ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ቡድኖች እንዲሁም የተለያዩ አካላት ተስተውለዋል። ዳይሬክተሩ የድጋፍ ስራዎችን ለማስተባበር በወልዲያ እና ደሴ በተገኙበት ወቅት “መሰል ክፍተቶች በውስን አካላት ላይ ታዝበናል፤ በመሆኑም እነዚህ አካሄዶች አግባብ አለመሆናቸውን መግለጽ እንፈልጋለን” ብለዋል።

“ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት በራሳቸው ለመስጠት የሚሄዱበት አግባብ በየመንገዱ ከመቀናነስ አልፎ ተረጂዎች ያሉበት ስፍራ ሲደርስም ለማይገባቸው አካላት የተጋለጠ ይሆናል”

የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከክልሎች ጋር በመተባበር በጤና፣ በትምህርት፣ በዉሃ፣ በንጽሕና፣ በተመጣጠነ ምግብ እንዲሁም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በሚሰራቸው ስራዎች መረጃዎቹ በኮሚሽኑ እና በተለያዩ ማእከላት ላይ ተደራጅተው እንደሚቀመጡ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማእከል በሰመራ እና ባህር ዳር የሚገኙ ሲሆን ጎንደር እና ደሴ ላይ ደግሞ የሁኔታዎች መምሪያ (Incident Command Post) ተቋቁሟል።

“እነዚህ ተቋማት ማን ምን ይፈልጋል? የትኛው አካባቢ ላይ እንደሚያስፈልግ እና ድጋፎች መድረስ የሚችሉባቸውን መንገዶች በተመለከተ የተደራጀ መረጃ ይዘው ሳለ ድጋፍ የሚያቀርቡ አካላት ራሳችን እንሰጣለን ማለት የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ መደገፍ አለመሆኑን መገንዘብ አለባቸው” ሲሉ ደበበ ዘውዴ አሳስበዋል።

በኮሚሽኑ እና በድጋፍ ማስተባበሪያ ማእከላት ያልተደገፉ ፍሰቶች “አንዳንድ ጊዜ ተረጂ ያልሆኑ አካላት እና ጉልበተኞች እንዲወስዱ እድል የሚፈጥር ነው” ሲሉም ዳይሬክተሩ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። በተጨማሪም እንደ ደበበ ዘውዴ ገለጻ “ሰፊ የማጣራት እና በማስረጃ የመደገፍ ጉዳይ የግድ ቢልም በመረጃ ያልተደገፉ የድጋፍ ፍሰቶች ሊበዘበዙ ይችላሉ።”

ድጋፍ ማቅረብ የሚፈልጉ አካላት የሚያቀርቡትንም ነገር ራሳቸው ማዘጋጀት ይችላሉ፤ ነገር ግን የተዘጋጁት የድጋፍ ቁሳቁሶች ለማን እንደሚያስፈልጉ ለማወቅ ከኮሚሽኑ እና ከተቋቋሙ ማእከላት ጋር መናበብ አለባቸው።

ከውጭ ሀገራት የሚላኩ ድጋፎችን ጨምሮ ከየትኛዉም አካል የሚቀርብ እርዳታ “በድጋፍ ሰጪዉ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ለህዝቡ መድረስ የለበትም” ሲሉም ዳይሬክተሩ አበክረው ገልጸዋል።

“ፍራሽ ለደረሰው ተጎጂም ቢሆን መልሰህ ፍራሽ ብትሰጠው ገበያ ላይ ነው የሚያውለው” ብለዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ባለው መረጃ ላይ ተመስርቶ በወር 15 ኪሎ እህል፣ 0.45 ሊትር ዘይት፣ 1.5 ኪሎ ግራም ጥራጥሬ ለተጎጂዎች በነፍስ ወከፍ ይሰጣል ያሉት ደበበ ዘዉዴ፤ በተጨማሪም 35 በመቶ የሚሆኑት ተፈናቃዮች አልሚ ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ለህጻናት፣ ለነፍሰጡር እና አጥቢ እናቶች እንደሚደርሱ ገልጸዋል።

እስከ ታህሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በደብረብርሃን ይገኙ የነበሩ ከ255 ሺህ በላይ በጊዜያዊ መጠለያዎች የነበሩ ተፈናቃዮች በአሁኑ ሰዓት ከ2 መጠለያዎች በስተቀር ሙሉ በሙሉ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለሳቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

ለእነዚህ ተፈናቃዮች በመጠለያ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ነበሩበት አካባቢ በመመለሱ ሂደት እንዲሁም በቀዬቸው መልሰው የሚቋቋሙበትን መንገድ መንግስት በተደራጀ መልኩ እየደገፈ መሆኑን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ገልጸዋል።

በደቡብና ሰሜን ወሎ አካባቢዎች 128 ሺህ ኩንታል በላይ እህል በአካባቢዎቹ እንዲደርስ እየተደረገ ሲሆን ከ1 ሺህ 200 ኩንታል በላይ አልሚ ምግብ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ኮሚሽኑ እየላከ እንደሚገኝም ከኮሚሽኑ ማወቅ ተችሏል።

ለተጎጂዎች እርዳታ የማቅረብ ፍላጎት እና አቅም ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ኮሚሽኑን እና ማእከላቱን በመጠየቅ የተሟላ መረጃዎችን ማግኘት ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የድጋፍ ፍሰቱን ማመጣጠን የሚቻለው በመረጃ በመደገፍ ብቻ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

አስተያየት