ታህሣሥ 27 ፣ 2014

ዓመታዊው የፈረስ ጉግስ ትርዒት በጎንደር

City: Gonderባህል ቱሪዝም

ፈረሰኞቹም በቄኝጠኛ ግልቢያ እና የጦር አወራወር የታዳሚን ቀልብ ይይዛሉ።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ዓመታዊው የፈረስ ጉግስ ትርዒት በጎንደር

ፈረስ ጉግስ ከዓለም አቀፍ ስፖርታዊ መዝናኛዎች መካከል አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ሰዎችንም ሆነ ቁሳቁሶችን የማጓጓዝ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ፈረስ በጦርነት ጊዜም ከአርበኛው ጋር የውጊያ ሜዳ ድረስ ዘልቆ ከመዋጋት ጀምሮ ስንቅ እና ትጥቅ እስከማመላለስ ድረስ ባለውለታ ነው።

የፈረስ ጉግስ ከጎንደር ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል አንዱ ነው። ጥር 24 ቀን የሚከበረው ዓመታዊው የቅዱስ መርቆርዮስ ክብረ-በዓል በርካታ ፈረሰኞች በሕብረት አደባባይ ከሚወጡባቸው በዓላት አንዱ ነው። (ዕለቱ በኦርቶዶክስ ክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ የፈረሰኛው እለተ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የፈረሰኛው ቅዱስ መርቆርዮስ በዓል የሚከበርበት ነው) በ“አጅባር” የሚካሄደው ባህላዊ የፈረስ ጉግስ ትርዒት ከሐይማኖታዊ ትርጓሜው ባልተናነሰ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ፋይዳውም የጎላ ነው። “አጅባር” በደቡብ ጎንደር የሚገኝ ለፈረስ ጉግስ እና ለመሳሰሉ ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ ለጥምቀት በዓል ለታቦት ማደሪያ የሚያገለግል ሜዳማ ቦታ ነው።

ፈረስን እንደ አክሱም ሃውልት ቀጥ አድርገው የሚያቆሙት ጎንደሮች በእለቱ ቀልብ የሚማርክ ትርኢት ያሳያሉ። ሽምጥ ጋልበው ተጋጣሚዎቻቸው ላይ ልምጭ ይወረውራሉ። ዐይንን እና ቀልብን የሚስበው የጉግሥ ተሳታፊዎች ትርዒት እና ውድድር የሚያካሄደው በዓመት አንድ ጊዜ በዚህ ዕለት ነው።

“አጅባር ሜዳ” የቅዱስ መርቆርዮስ “ታቦት ማደሪያ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲከወን ከ73 ዓመት በላይ እንዳስቆረ የሚነገረው የፈረስ ጉግስ ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ መሰረት አለው። የኦርቶዶክስ ክርስትና ሰማዕት የሆነው ቅዱስ መርቆርዮስ ፈረሰኛ መሆኑ አንዱ ሐይማኖታዊ ሰበብ ነው። አክባክሪዎች ፈረሶቻቸውን ይዘው ለንግሥ የሚመጡት ይንን በማሰብ እና ክብር በመስጠት እንደሆነ ይነገራል። ሁለተኛው ከዚህ ጋር የተያያዘ ሀይማኖታዊ ምክንያት ቅዱስ መርቆርዮስ ወላኒዎስ በሚባል ቤተ-ክርስቲያንን ያፈርስ የነበረን ሰው ጥር 25 ቀን በጦር ወግቶታል። ከዚያ በኋላም የቤተ-ክርስቲያን ችግር አብቅቷል። በዓሉ በፈረስ እና በፈረስ ጉግስ የሚከበረው በዚህ ምክንያት ነው የሚለው ነው።

ታሪክ አጣቃሾች በበኩላቸው ስለ በዓሉ አጀማመር ሲያወሱ ፊት አውራሪ አለነ ገብሬን ያነሳሉ። የራስ ጉግሳ ወሌ ባለሟል የነበሩት ፊት አውራሪ አለነ ገብሬ በተወለዱበት አካባቢ ይከበር የነበረውን ዓመታዊ የፈረስ ጉግስ በዓል በደብረ-ታቦርም እንዲከበር አድርገዋል። የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር የጀመሩት ክብረ-በዓል አሁን ያለንበት ዘመን ድረስ ዘልቋል። በዕለቱ ከፈረስ ጉግስ በተጨማሪ መንፈሳዊና ኪነ-ጥበባዊ ክዋኔዎችን አካቶ በድምቀት ይከበራል።

ከ1940 ዓ.ም. ጀምሮ ሲከበር እንደቆየ የሚነገርለት የደብረታቦር የፈረስ ጉግስ ትርዒት ለሁለት ተከፍለው በቡድን በተደራጁ ፈረሰኞች መካከል ይካሄዳል። በቡድን የተደራጁት ፈረሰኞች ከእጽዋት ጦር መሰል ዘንግ ያዘጋጃሉ። ያዘጋጁትን ልምጭ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ይወረውራሉ።ከሌላኛው ወገን የሚወረወርባቸውን እየመከቱ ተቃራኒውን ቡድን ያጠቃሉ። በተመልካችነት የቆሙት ደጋፊዎቻቸው በግጥምና በዜማ ያወድሷቸዋል። በጦር መልክ የተዘጋጀውን ልምጭ ከወደቀበት እያነሱ ያቀብሏቸዋል። በዚህ ጨዋታ ፈረሶች ተሸልመው፣ አምረው ይቀርባሉ። ፈረሰኞቹም በቄኝጠኛ ግልቢያ እና የጦር አወራወር የታዳሚን ቀልብ ይይዛሉ። በሌላኛው ዓመት የአንድ መንደር ነዋሪዎች ለሌላኛው መንደር ነዋሪዎች የጨዋታ ግብዣ ይልካሉ። በወረቀት ጥሪ የደረሰው ሰፈር ነዋሪዎቹን አስተባብሮ፣ ፈረሶቹን ሸልሞ፣ ልምጩን አዘጋጅቶ ለግጥሚያ ይሰናዳል።

ከጨዋታው በኋላ አሸናፊው እና ተሸናፊው በጋራ በመሆን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ባህላዊ ምግብና መጠጥ እየተገባበዙ የሳቅና የጨዋታ ጊዜ ያሳልፋሉ። በፈረስ ጉግስ ጨዋታው ወቅት የነበረው መሸናነፍ ወደ ጸብ አያመራም። ዓመት ዓመት ያድርሰን ተባብለው ተመራርቀው ይለያያሉ።

የደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ ወረዳ የአንጋጫት ቀበሌ ተወላጅ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ እናናዬ ጫኔ የፈረስ ጉግሥ ጨዋታዎች ሲኖሩ እንደሚሳተፉ ነግረውናል። በልጅነታቸው ዘመን በየዓመቱ ይካሄድ የነበረው የፈረስ ጉግስ ጨዋታ የደመቀ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ እናናዬ “ፈረስ ጉግስ ለትውልድ ከምናስተላልፋቸው ባህላዊ እሴቶቻችን መካከል አንዱ ነው” ይላሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአክባሪዎች መቀነስ እና የአከባበሩ መቀዝቀዝ ቅሬታ እንዳሳደረባቸውም ተናግረዋል።

በጥንታዊቷ የበጌ ምድር መናገሻ ደብረ ታቦር ከራስ ጉግሳ ወሌ እስከ ራስ ወንድወሰን ከግቢ እስከ አራዳ የቅዱስ መርቆርዮስ ዓመታዊ ክብረ-በዓል በፈረስ እና ጠጅ ተከብሮ ይውል እንደነበር ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።

ቀደም ባለው ጊዜ ነገስታት ለፈረሶቻቸው የተለየ ፍቅር እና ክብር እንደነበራቸው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። መጠሪያ ስማቸው ሳይቀር በፈረሶቻቸው ስም የተቀየረ ነገሥታት ቁጥር በርካታ ነው። አባ ታጠቅ፣ አባ በዝብዝ፣ አባ ዳኘው፣ አባ ጠቅል፣ አባ ግርሻ፣ አባ ባህር፣ አባ መቻል፣ አባ ቃኘው ከነገሥታቱ እኩል የሚታወቁ እና የነገሥታቱን ዋና ስም እየተኩ መጠሪያቸው እስከመሆን የደረሱ ናቸው።

የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ስፓርት ጽ/ቤት የማህል እሴቶች ልማት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ሄኖክ ተካ እንደሚሉት የመርቆርዮስ በዓል የፈረስ ጉግስ ትርዒት በጥር ወር ባህላዊ ትርዒት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል ጎንደር አንዷ ነች። ጥር 24 እና 25 የሚከበረው የቅዱስ መርቆርዮስ በዓልና የፈረስ ትርዒት በዓመታዊነት በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

አቶ ሄኖክ ጥር ወርን አስመልክቶ ሲናገሩ “ጥር የወራት ሁሉ ሙሽራ ነው። በሀገራችን በጫጉላ ውስጥ የሚያልፍ ብቸኛው ወር ጥር ብቻ ነው። ጥር በማኅበራዊ ትስስሩ፣ በሐይማኖታዊ ቀኖናው፣ ቱሪዝምን መሰረት ባደረገው ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅሙ እና ጥንታዊ ቀደምትነትን በሚያጎላው ባህላዊ እሴቱ ፋይዳው የጎላ ነው” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተጨማሪም ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ…

“እንሶስላ በጥፍር ቀለም ተተክቶ ይደምቃል። ኩል፣ አደስ እና አርቲ ቻፕስቲክን፣ ሊፕስቲክን እና ሽቶን ያስንቃሉ። ቁንጮ፣ ጋሜ እና ሹርባ ቅጥ ያጣውን ዘመናዊ የፀጉር አሰራር ተክተው ይውላሉ። ድሪ፣ አምባር፣ አልቦና ጥርስም የውበት ዳርቻ፣ የልጃገረዶች የአጊያጊያጥ ቀንዲል ይሆናሉ። ሎሚ በተረከዝ፣ ሎሚ ደረት ላይ ይወረወራል” ብለዋል።

እክለውም ይሄን የፈረስ ጉግስ ትርዒት ወይም ባህል በዩኒስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሂደት ላይ መሆናቸውን ነግረውናል። “በዘንድሮው የደብረ ታቦር ቅዱስ መርቆሪዎስ ክብረ በዓል ለሚዲያ ሽፋን 300,000 ብር ተመድቧል። ሆቴሎችን ጨምሮ ሌሎች ጎብኚዎችን የሚስቡ ቅድመ-ዝግጅቶች ተጠናቀዋል። በቅርቡ ሀገራቸው የገቡት ዲያስፖራዎች ከሚታደሙባቸው በዓላት መካከል አንዱ እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል” ብለዋል።

አስተያየት