ማኅበራዊ ሚዲያ ለበርካቶች መረጃዎችን መለዋወጫ መድረክ መሆኑን ያህል እንደዚያውም የገቢ ምንጭ መሆኑ ይታመናል። ብዙዎች ለመዝናናት፣ ጊዜ ለማሳለፍ እንዲሁም ቁምነገር ለማግኛነት ሲጠቀሙትም ይስተዋላል። የማኅበራዊ ሚድያ መስፋፋትን ተከትሎ በርካቶች ሐሳባቸውን በሚልዮኖች በቀላሉ ማድረስ ችለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ተጠቃሚ ካላቸው የማኅበራዊ ሚድያ አውታሮች መካከል ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም፣ ዋትስ አፕ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
በተለይም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን መስፋፋት ተከትሎ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ጨምሯል። የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያለመው የእንቅስቃሴ ገደብ እና ከቤት ያለመውጣት ክልከላ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።
በጫናው አስገዳጅነትም ቢሆን ከዚህ በፊት ቴክኖሎጂውን የማይጠቀሙ ዘርፎች ሥራቸውን በኢንተርኔት አማካኝነት ፈጽመዋል። ግብይቶች፣ የማድረስ (የዴሊቨሪ) አገልግሎቶች፣ የውይይት መድረኮች፣ የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች፣ መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ ትምህርቶች ኮቪድን ተከትለው በኢንተርኔት መከወን የጀመሩ ወይም በዚያን ወቅት የተስፋፉ የሥራ ዘርፎች ናቸው።
በዚህ ጽሑፍ የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም የተለያዩ ጠቃሚ እና አስተማሪ የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ የሚገኝ የቴሌግራም ግሩፕ እንመለከታለን።
ይህ የቴሌግራም ግሩፕ የሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ተማሪዎች ማኅበር (ጄሲ ሳ) በመባል ይታወቃል። ከ1700 በላይ አባላት አሉት። በየሳምንቱ በወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከሁሉም ዮኒቨርሲቲ ከሚሳተፉ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ከስመ-ጥር የሀገራችን ጋዜጠኞች ጋር በመሆን የልምድ ልውውጥ እና ውይይቶችን ያካሂዳሉ። ይህም ለሁለት ዓመታት ያህል ቆይቷል።
የዚህ የቴሌግራም የውይይት መድረክ አዘጋጅ የነበረው እና የወቅቱ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ተማሪዎች ማኅበር (ጄሲ ሳ) ፕሬዝዳንት ጋዜጠኛ እያሱ አጀማመሩን ነግረውናል "የጄሲ ሳ ማኅበር በቴሌግራም ሲመሰረት የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋቱን ተከትሎ ሁሉም ተማሪዎች ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ ከተደረገ በኃላ ነው። የውይይቱ ዓላማ ተማሪዎች በቀለም የሚማሩትን ትምህርት ወደ ስራው ዓለም ሲወጡ ያለው ልዩነት ምን እንደሆነ ማስገንዘብ እና በነፃነት ሀሳባቸውን በመግለፅ ጋዜጠኝነትን እንዲተገብሩት ለማስቻል ነው። በውይይቱ ላይ በርካታ ሐሳቦች ተዳስሰዋል። ስለ ህዳሴ ግድብ፣ የኮሮና ቫይረስ በጋዜጠኛው ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ፣ ጋዜጠኝነት እና ስፖርት፣ እንዲሁም ከውጪ ጣልቃ ገብነት ጋር በተገናኘ የሀገር ውስጥ ሚዲያ አዘጋገብ የተቃኘበት እና ከ20 በላይ ጋዜጠኞች የተጋበዙበት ነበር"
በሀገራችን ከሚገኙ ከአርባ በላይ ዮኒቨርስቲዎች ውስጥ የቴሌግራም መተግበሪያን በመጠቀም የልምድ ልውውጥ እና የመማማርያ መድረክ በመፍጠር ቀዳሚ እና ብቸኛ የሆነው የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ተማሪዎች ማኅበር መቀመጫውን በዋናው ግቢ በሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ አድርጓል።
32ኛዙር የውወይት መድረክ ላይ የሚገኘው ማኅበሩ ከ20 በላይ ከተለያዩ ሚዲያዎች የተወጣጡ ጋዜጠኞችን በመጋበዝ ለተማሪዎች ልምዶቻቸውን እንዲያካፍሉ አስደርጓል። ለአብነት ያክል ጋዜጠኛ ዓለምነህ ዋሴ፣ ኤልያስ መሰረት፣ ሰለሞን ኃ/እየሱስ፣ አዳነ አረጋ፣ ሶዶ ለማ፣ ሰይድ ኪያር እና መኳንት በርሄ፣ ስለአባት ማናዬ፣ ሰላም ሙሉጌታ፣ አስማማው አየነው፣ አንተነህ ደግፌ፣ መቅደስ ኃይሉ፣ ስሜነህ ባይፈርስ እና ሌሎች በርካታ የሀገራችንን ጋዜጠኞች በየሳምንቱ እሁድ በቀጥታ በድምፅ ከተማሪዎች፣ ከመምህራን እና ከተሳታፊዎች ለሚነሱላቸው ጥያቄ ማብራሪያ እንዲሰጡ መደረጉንም ሰምተናል።
"የጄሲ ሳ ማኅበር ተማሪዎች በነበርንበት ወቅት ለነገአችን ግብዓት የሚሆኑ ቁምነገሮችን መውሰድ ወስጃለሁ። ዛሬ ላለሁበት ስራ መሰረት ሆኖኛል ማለት እችላለሁ " ሲል የሚያስታውሰው ጋዜጠኛ ዘልዓለም ዳዊት ነው።
ሌላኛዋ የባህር ዳር ዮኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ተማሪ የሆነችው ወንጌል ፈቀደ ገና ወደ ትምህርት ክፍሉ ሳትቀላቀል የቴሌግራም ግሩፑን መቀላቀሏን አንስታ “ጋዜጠኝነትን እንድወድ እና እንድናፍቅ አድርጎኛል ብላናለች” በማኅበሩ የሚደረጉ እያንዳንዳቸው ውይይቶች አያመልጡኝም አጋጣሚ በዕለቱ መሳተፍ የማልችል እንኳን ቢሆን የተደረጉትን ውይይቶች በድምፅ ተቀድቶ ስለሚቀመጥ ማድመጥ እችላለሁ። ሙያዊ አስተያየቶቹ ይጠቅሙኛል” ትላለች።
መምህር መሳይ ቦጋለ የሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ት/ክፍል መምህር ናቸው። በውይይቱ በእንግድነት ተጋብዘው እንደነበር ያስታውሳሉ "በማኅበሩ አማካኝነት እየተካሄደ የሚገኘው ውይይቱ እጅግ አመርቂ ለውጥ በተማሪዎቻችን ላይ ያየንበት ነው። ይህ ዕድል በመፈጠሩ እኛም ከተለያዩ ስመ-ጥር ጋዜጠኞች ጋር ዕድሎችን አግኝተን የተሟገትንበት እንዲሁም የሚናፈቅ የውይይት መድረክ ነው” የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል።
“ለአጠቃቀም ቀላል ሁሉም በሚገኝበት ቦታ ሁሉ ውይይቱን መሳተፍ እንዲችል የተመቻቸ እድል ስለሆነ አለመወያየት አይቻልም” የሚሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዲህ ዓይነት መድረክ በሌሎች ዮኒቨርሲቲዎችም ቢቀጥሉ ጠቀሜታው ይጎላል የሚል ሐሳባቸውን አጋርተውናል።
“በልዩ ዘርፍ” በአምስተኛው የጣና ሽልማት ላይ የታጨው ማኅበሩ በቀጣይ የሀገሪቷን ሁኔታ አስታኮ በኦላይን የነበረው ቶውክሾው በአካል እንደሚጀምር አዘጋጆቹ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።