ታህሣሥ 27 ፣ 2014

ትኩረት የተነፈገው የአዳማ ችግኝ አፍይዎች ቅሬታ

City: Adamaምጣኔ ሃብትመልካም አስተዳደር

ከወንጂ ማዞሪያ ወደ ሥላሴ በሚወስደው የአስፖልት መንገድ ላይ ከአዳማ ትራክተር መገጣጠሚያ ፊት ለፊት የሚገኘው አካባቢ እጅግ ውብና አረንጓዴ ገጽታን የተላበሰ ነው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ትኩረት የተነፈገው የአዳማ ችግኝ አፍይዎች ቅሬታ

በአዳማ ማርያም ቤ/ክ ዙሪያ፣ ትራክተር መገጣጠሚያ ፊት ለፊት፣ ዠቃላ ገበያ አካባቢ የነበሩ የችግኝ እና የማስዋቢያ አበባ ሽያጭ ስራዎች ዛሬ ላይ እንደ ቦሌ ጫፍ፣ ቦሎ ሚካኤል፣ ገንደ ሀራ ያሉ የከተማዋ አዳዲስ ሰፈሮች ተስፋፍተዋል። የሕብረተቡ አካባቢውን የማስዋብ ባህል ስለማደጉ የሚናገሩት ነጋዴዎቹ “የቦታ ችግር፣ የስራ ደህንነት ሁኔታ እና የገበያ ትስስር አለመኖር” እንደ እክል የሚያነሷቸው ተግዳሮቶች ናቸው።

 ከወንጂ ማዞሪያ ወደ ሥላሴ በሚወስደው የአስፖልት መንገድ ላይ ከአዳማ ትራክተር መገጣጠሚያ ፊት ለፊት የሚገኘው አካባቢ እጅግ ውብና አረንጓዴ ገጽታን የተላበሰ ነው። በቦታው አራት ማኅበራት ተደራጅተው የተለያዩ ችግኞች ማፍላት እና የመሸጥ ስራ ላይ ተሰማርተዋል። 

 በስፍራው የችግኝ እንክብካቤ ላይ ያገኘናቸው አቶ ያዕቆብ አስፋው “የህይወቴን ግማሽ በአትክልተኝነት ነው ያሳለፍኩት” ይላሉ። በ2008 ዓ.ም. ከጓደኞቻቸው ጋር ተደራጅተው አሁን የሚገኙበት ቦታ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ። ቦታውን ከመፍቀድ እና መሬት መትሮ ከመስጠት በዘለለ ምንም ዓይነት ድጋፍ ከአደራጁ አለማግኘታቸውንም አጫውተውናል። ይህ ሐሳብ የአቶ ያዕቆብ ብቻ ሳይሆን ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው የሌሎች ማህበራት አባላትም ነው “የቧንቧ ውሃ የኖረን ቦታው ከተሰጠን ሁለት ዓመት በኋላ ነው" የሚሉት አቶ ያዕቆብ አስፋው በ2012 ዓ.ም. ከ2011 ዓ.ም. የአረንጓዴ አሻራ ተሞኩሮ ወስደው ብዙ የዛፍ ችግኝ ቢያዘጋጁም ከትርፍ ይልቅ ወደ ኪሳራ እንደወሰዳቸው ይናገራሉ። ለሦስት ዓመት ገበያ አጥቶ ያልተሸጠ፣ ከ2 መቶ ሺህ በላይ ችግኝ ሙሉ በሙሉ እንደደረቀና የጉልበት ወጪው ሳይታሰብ ማኅበሩ ከ7መቶ እስከ 8መቶ ሺህ ብር ኪሳራ ብር ኪሳራ ውስጥ መውደቁን ይናገራሉ።

 በሌላ ማኅበር ውስጥ የሚሰራው ኪሩቤል ማንደፍሮ ስለጉዳዩ ሲናገር "የገበያ ጉዳይ እጅጉን ቸግሮናል። የጸደቁ ዛፎች ገዢ ስላጡ ደርቀው ጥለናቸዋል" ብሎናል። ገበያ ከማጣታቸው የተነሳም መሬቱ ምንም ሳይሰራበት ጦሙን ለማደር መገደዱን አንስቷል።

 የማኅበራቱ አባላት በተለያዩ ቦታዎች በግልም በቡድንም በሚያገኙት አካባቢ የማስዋብ ስራ ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን እየደጎሙ እንደሆነ ይናገራሉ። “ከሁሉም በላይ ቆሻሻ የነበረውን አካባቢ አልምተን፣ ሁለት ዓመት በውሃ እጦት ተሰቃይተን በሰራነው ቦታ ላይ የደረሰብን ኪሳራ ታሳቢ ሳይደረግ አምስት ዓመት ስለሞላችሁ ትለቃላችሁ መባላችን አግባብ አይደለም” የሚል ቅሬታቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

 ኤፍሬም ዳምጠው በስሩ በቋሚነት ሁለት ሰራተኞች እንሉት ነግሮናል። ስራ ሲኖር እስከ ስድሰት ሰራተኞችን ይቀጥራል። ችግኝ የማፍላት ሥራውን የሚሰራው በግሉ ነው። እርሱ የሚሰራበት አካባቢ በዋናው የአዲስ አበባ ጅቡቲ መንገድ መስመር በመሆኑ ከቦታው ልነሳ እችላለሁ የሚል ስጋት አለው።

 "አንድ ኢንተርፕራይዝ መንግስት ባመቻቸለት ቦታ በመደበኛው ቆይታ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ሊቆይ ይችላል። አንዳንድ ልዩ ሁኔታዎች ሲኖሩ እስከ ስምንት ዓመት ድረስ ሊቆይ ይችላል” የሚሉት በአዳማ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዞች እና ኢንድስትሪ ልማት ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ፍቃዱ በየነ ናቸው።

 “በአሁኑ ወቅት ማኅበራቱ የገበያ ትስስር ችግር አለባቸው ብለን አናምንም ከተማ አስተዳደሩ ራሱ ከሚያፈላቸው ችግኞች በተጨማሪ ግዢ የሚያከናውነው ከማኅበራቱ ነው" ሲሉ በቢሯቸው በኩል ስላለው ሁኔታ ምላሽ ሰጥተዋል።

 አቶ መስፍን ደመቀ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ነው። ለበርካታ ዓመታት በችግኝ ስራ ላይ አሳልፏል። በችግኝ ስራው በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቦቹን ያስተዳድራል። "ከምሰራበት ቦታ ተነስቼ የመስሪያ ቦታ ስላጣሁ ለመጪው ክረምት እየተዘጋጀው አይደለም" ሲል ይናገራል።

 “ባለፉት ሁለት ዓመታት የችግኝ ሽያጭ በተለይም የዛፍ ችግኞች ሽያጭ ስለተቀዛቀዘ ከፍተኛ ዋጋ አውጥተን ገዝተን ያመጣናቸው ችግኞች አክስረውናል” ይላል። ከመስሪያ እና መሸጫ ቦታ ጋር በተገናኘ ደግሞ “ማርያም ቤተ/ክ ዙሪያ እንደተነሳን እስከ ከተማው መሬት አስተዳደር ድረስ ሄደን ቅሬታችንን አሰምተን ነበር። ነገር ግን የተሰጠን ምላሽ ይኾናል የምትሉትን ቦታ ጠቁሙን ተብለን በእንጥልጥል ቀርተናል” ብለዋል። እንደ አቶ መስፍን ማብራሪያ ለመስሪያ የሚሆን የሚጠቁሙት ቦታ ስላላገኙ ችግኞቻቸውን በየመንገዱ ዳር እና በየሰዉ ቤት አደራ አስቀምጠው እንደሚገኙ ይናገራሉ። “እጄ ላይ የቀሩብኝን ሽጬ ከጨረስኩ አክሳሪ ስለሆነብኝ ወደ ሌላ ስራ ለመሰማራት  እያሰብኩ ነው”  ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

 ማርያም ቤ/ክ አካባቢ ያገኘናቸው ሌሎችም በችግኝ ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የቦታ ችግር አሳሳቢ እንደሆነ ይናገራሉ። "ከቦታው በላይ ደግሞ ተነሱ ስንባል ቢያንስ የሳምንት እድሜ እንኳን አይሰጥም። በሦስት ቀን ተነሱ ነው የምንባለው" የሚል ቅሬታውን የነገረን ስሜ ይቆይልኝ ያለ የአካባቢው ነጋዴ ነው። “አንድ ጊዜ ከቀበሌ፣ ሌላ ጊዜ ከማዘጋጃ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከመሬት አስተዳደር የሚመጡ ሰዎች ትነሳላችሁ የሚል ማስፈራሪያ ይደርስብናል” ሲል ይናገራል።

 የአዳማ አብዛኛዎቹ ችግኝ ነጋዴዎች የተለያዩ ችግኞችን ከቢሾፍቱ አምጥተው እንደሚሸጡ ይገልጻሉ። በቢሾፍቱ በግለሰብ ደረጃ በየቤቱ ችግኝ ማፍላት የተለመደ እንደሆነም ይናገራሉ። ግለሰቦች ንግድ ፈቃድ እና ደረሰኝ የሌላቸው እንደሆኑ ይነገራል። 

 ወ/ሮ ጽጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ፊት ለፊት የኖህ ክሊኒክ አጥርን ታኮ የሚገኘው ቦታ ላይ የአበባ እና ችግኞች ዘርግታ ትሸጣለች። "ከቢሾፍቱ ችግኝ የምንገዛው ከግለሰብ ስለሆነ አብዛኛውን ጊዜ ያለደረሰኝ ነው። እዚህ እኛ ደረሰኝ ብንቆርጥም ከመንግስት አካል የገዛችሁቀትን አምጡ ስንባል እንቸገራለን" ስትል ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች “ቢሾፍቱ ያለው ሁኔታ ቢስተካከል መልካም ነው” ምትለው ጽጌ ለስራቸው ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ  አፈር መጠቅጠቂያ የፕላስቲክ ከረጢቶች፣ የአበባ መትከያ የፕላስቲክ እንስራዎች ለእጥፍ በሚጠጋ ዋጋ ጨምረው ስራው ስለመቀዝቀዙ ነግራናለች “ይኼ እንደኔ ኑሮውን በዚህ ስራ ላስመረኮዘ ሰው የፈተና ጊዜ ነው” ብላናለች።

የመስሪያ ቦታን በተመለከተ በአዳማ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዞች እና ኢንድስትሪ ልማት ጽ/ቤት አቶ ፍቃዱ በየነ "ከቦታ መነሳትና ማስፈራራት ጋር እኛ ቢሮ የመጣ ቅሬታ የለም" የሚሉት አቶ ፍቃዱ ቢሮው በክፍለ ከተማ እና በቀበሌ ደረጃ መዋቅር ስላለው በእነርሱ ሊፈታ እንደሚችል ተናግረዋል።

የመስሪያ ቦታ ማመቻቸትን በተመለከተ እነርሱ አደራጅተው ለመሬት አስተዳደር እንደሚያስተላልፉ ነግረውናል። 

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ የመሬት አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

አስተያየት