ታህሣሥ 28 ፣ 2014

ከ450 ዓመታት በላይ የኖረው “ጎባጢት” ድልድይ

City: Gonderታሪክ

ከኢትዮጵያ ቀደምት የንግድ ማዕከላት አንዷ በነበረችው እንፍራንዝ ከተማ እና በታሪካዊው የጉዛራቤተ መንግሥት መካከል የጋርኖ ወንዝ ይገኛል።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከ450 ዓመታት በላይ የኖረው “ጎባጢት” ድልድይ

“ጎባጢት” ከኢትዮጵያ ቀደምት የንግድ ማዕከላት አንዷበነበረችው እንፍራንዝ ከተማ እና በታሪካዊው የጉዛራቤተ መንግሥት መካከል የአፄሰርፀ ድንግል ባለቤት በሆነችው በእቴጌ ስነወርቅ ማርያም እንደተሰራ ይነገራል።

ከኢትዮጵያ ቀደምት የንግድ ማዕከላት አንዷ በነበረችው እንፍራንዝ ከተማ እና በታሪካዊው የጉዛራቤተ መንግሥት መካከል የጋርኖ ወንዝ ይገኛል።በቀደመው ጊዜ በዚህ ወንዝ ምክንያት የአፄሰርፀ ድንግል ባለቤት እቴጌ ስነወርቅ ማርያም ከጉዛራ ወደ እንፍራዝ ልደታ ቤተክርስቲያን ለመሄድና ፀሎት ለማድረስ ይቸገሩ ነበር።የጉዛራና እንፍራዝ ከተሞች ግንኙነትም በቅርብ ርቀት ማዶ ለማዶ በመተያየት ብቻ የተወሰነ ነበር።ወንዙን መሻገር የማይሞከር ነበር።ይህንን ችግር ያስተዋሉት እቴጌዋ ወንዙን የሚያሻግር ድልድይ እንዲሰራ አዘዙ። 

‘’ማንያሻግረኝ ብለሽ እንዳትጨነቂ፣

በጎባጢት ድልድይ በግንቡ ዝለቂ’’ 

የሚለው የአዝማሪ ግጥም የተዘፈነው የወቅቱ ነዋሪዎች ቅርጹን ተመልክተው “ጎባጢት” የሚል ስያሜ የሰጡት ድልድይ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ እንደነበር ይነገራል።

ጎባጢት ድልድይ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ ታሪክ ያስታውሳል። በቀሃ እና በጋርኖ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድዩ በአጼ ፋሲለደስ ዘመነ መንግሥት ከተገነቡ ሰባት ድልድዮች መካከል አንዱ ነው። ከሰባቱ ድልድዮች መካከል በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ሁለቱ (ጎባጢት እና የአንገረብ) ብቻ ናቸው። ጢስ ዓባይ የሚገኘው ዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው “የአለታ ድልድይ”፣ የሞጣ እና የእዳ ቤት ወረዳን የሚያዋስነውና በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው “ሰባራ ድልድይ” በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት አይሰጡም።

የጎንደር ከተማ ቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶዓይቼው አዲሱ “ጎባጢት” በአፄሰርጸ ድንግልዘመነ መንግሥት በ1560ዎቹ እንደተገነባ ይናገራሉ። ከባህር ዳርጎንደር ከተዘረጋው አስፓልት 200 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጎባጢ ትድልድይ በስተሰሜን አቅጣጫ በጋራ የተከበበ ሲሆን ደቡባዊ ወሰኑ ለጣና ሐይቅ እጅግ የቀረበ ነው። በሰሜናዊ ምስራቅ አቅጣጫም ጥንታዊው የጉዛራ ቤተ መንግሥት በውሱን እርምጃዎች የሚደረስበት መስሎ በቅርብ ርቀት ይታያል።

“በጉዛራ ቤተመንግሥት መቀመጫቸውን ያደረጉት አጼ ሰርጸ ድንግል ከሱዳን፣ከኤርትራ ጅቡቲና ከመላው ኢትዮጵያ አካባቢዎች የጠነከረ የንግድ ልውውጥ ያካሂዱባት ነበር።እንፍራንዝ ከተማም የንግድ ማዕከል ነበረች። የጥርኝሽቶ፣ ቅመማቅመም፣ የዝሆን ጥርስና አሞሌጨው ዋና ዋናዎቹ  የንግድ ዘርፎች ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ የብርእና የወርቅ ንግድ ይካሄድባት እንደነበረም ይነገራል። 

ከ454 ዓመት በላይ ያስቆጠረው ድልድዩሲገነባ ምንም ዓይነት ብረት ጥቅም ላይ አልዋለም። በኖራ እየተጣበቀ ድንጋይን በድንጋይ በማነባበር የተሰራ ነው። 12 ሜትር ርዝመት፣ 9 ሜትር ቁመት፣ 4 ሜትር ስፋትና 1 ሜትር ውፍረት አለው። ግማሽ ክብ ሆኖ መሰራቱም ከባድ መጠነ ቁሶችን ለመሸከም አስችሎታል። ከፋሲል አብያ ተመንግስታት ጋር በዓለም የቅርሶች መዝገብ ላይ የተመዘገበው የጎባጢት ድልድይ በአለታማ ቦታ ያለአንዳች ብረት የተገነባ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። 

የ“ጎባጢት” ድልድይ አሰራር የወቅቱን የኢትዮጵያውያን የግንባታ ጥበብ አጉልቶ ያሳያል። የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ቡድን መሪው እንደሚሉት “ቅርሱ ምንም ዓይነት እድሳት ሳይደረግለት የነበረውን ገጽታ እንደያዘ ያለንበት ዘመን ድረስ መኖሩ የወቅቱን የግንባታ ጥበብ መራቀቅ የሚያሳይ ነው”