የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ምክር ቤት የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በጋራ ተቀናጅተው በአንድ ቦታ አገልግሎት የሚሰጡበት “ሜዲካል ፕላዛ” አገልግሎት አስገዳጅ ደረጃዎችን መስከረም 20/2014 ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባዉ አጸደቀ።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጸደቀዉ ይህ አስገዳጅ ደረጃ የውስጥ ደዌ ህክምና፣ የአይን ህክምና፣ የጥርስ ህክምና፣ የቆዳ ህክምና፣ የህጻናት ህክምና፣ ላብራቶሪ፣ የመድሃኒት መሸጫ፣ የአልትራሳውንድ ምርመራ እንዲሁም ልዩ ልዩ የህክምና አገልግሎቶችን በአንድ ጣራ ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ የኤጀንሲ የደረጃዎች ዝግጅት ዳይሬክተር ይልማ መንግስቱ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
በመሆኑም በተለያዩ የዓለም ሀገራት አገልግሎት የሚሰጥበትን ይህን ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥም ለመተግበር የሚያስችለው የጥራት ደረጃ ሲጸድቅ ለየብቻ በተለያዩ የጥራት ደረጃዎች ሲሰሩ የነበሩን ተቋማት በአንድ ላይ እንዲሰሩ ከማድረጉ አኳያ ለተገልጋዩ ከሚኖረዉ ጠቀሜታ ላይ እና ውጤታማነቱ ላይ ከተለያዩ የዘርፉ ምሁራን እና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥልቅ ምክክር መደረጉን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
“በሌላው አለም ላይ ካሉት ተሞክሮዎች በመነሳት በተበታተነ መንገድ አገልግሎት የሚሰጡት ተቋማት በሜዲካል ፕላዛ አማካኝነት በጋራ አገልግሎት መስጠት ቢችሉ የዘርፉን ተደራሽነት ይጨምራል፣ የህክምና አገልግሎት ጥራቱን ይጨምራል፣ በተጨማሪም የተለያዩ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች አንድ ላይ ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ አንድ ተቋም ብቻውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት ሲል የሚኖረውን መነሻ ወጪ ለምሳሌ ለላብራቶሪ ግንባታ፣ ለሪሴፕሽን፣ ለሰው ሀብት አስተዳደር እና ወዘተ የሚያወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ስለሚረዳ እነዚህን ታሳቢ በማድረግ ነው ደረጃዎቹ የወጡት” ሲሉ አብራርተዋል።
አክለውም ደረጃዎቹ ሲዘጋጁ ሁሉም አይነት የህክምና አገልግሎቶች በተቻለ መጠን ተሳታፊ መሆን እንዲችሉ መደረጉን እና ህጉ በሚፈቅደው እና ህብረተሰቡ ሊያገኝ በሚገባው ጥራቱን የጠበቀ ሁኔታ እንዲይዙ ተደርገው በምክር ቤቱ መጽደቃቸውን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘይቤ ከህክምናው ዘርፍ ሙያተኞች በኩል ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ዋና ጸሃፊ እና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአንስቴዥያ ክፍል ሃላፊ ዶክተር አናንያ አባተ “በኛ ሀገር ሜዲካል ፕላዛን ለመጀመር ከበፊት ጀምሮ በተለይ የግሉ ዘርፍ የህክምና ማህበሩ ቡድን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በምን መልኩ ቢሰራ ለሀገሪቱ የጤና አገልግሎት አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላል በሚል ጥናት ሲደረግ ቆይቷል፣ ስለዚህ አሁን ደረጃው ከወጣለት ወደ ቀጣይ እርምጃ ለመድረስ ምቹ ይሆናል ማለት ነው” ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዉናል።
በሌላ በኩል “የሜዲካል ፕላዛ ደረጃዎች መጽደቅ ለግሉ የህክምና ዘርፍ ምን ፋይዳ አለዉ? ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሀኪሞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሜሮን ያዕቆብ “ሜዲካል ፕላዛው ላይ ሰፊ ድርሻ የሚወስዱት የግሉ ህክምና ዘርፎች መሆናቸው ስለማያጠያይቅ እና መፍትሄው ሥርዓት መዘርጋት በመሆኑ የተቀናጀ አገልግሎት ሥርዓት ወይም ኢንተግሬትድ ደሊቨሪ ሲስተም ለመፍጠር ያግዛል” ብለዋል።
በተያያዘ ምክር ቤቱ የምግብና ግብርና ዘርፍን ጨምሮ፤ በ7 ዘርፎች ላይ 332 አዲስ፣ 190 የተከለሱ እንዲሁም 184 በነበሩበት የቀጠሉ በድምሩ 706 ደረጃዎች ላይ የመጨረሻ ረቂቆች ቀርበውለት ሁሉንም ደረጃዎች መርምሮ አጽድቋል።