ጥቅምት 18 ፣ 2014

ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ አሽርካሪዎች የተማረሩ የድሬዳዋ ነዋሪዎች

City: Dire Dawaመልካም አስተዳደርኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ምሽት ላይ የትራንስፖርት እጥረት፣ አቆራርጦ መጫን የተለመደ ነው። ባለ ታክሲዎቹ ይህንን የሚያደርጉት የርቀቱ ዋጋ እንዲጨምርላቸው ነው። መንገዱን ቆርጠው ሲጭኑ የሚያስከፍሉትን አይቀንሱም።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ አሽርካሪዎች የተማረሩ የድሬዳዋ ነዋሪዎች

ሰይፈዲን ኢድሪስ የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የማታ መርሃ-ግብር ተማሪ ነው። ነዋሪነቱ ገንደገራዳ አካባቢ ነው። ዘወትር ወደ ዩንቨርሲቲ የሚጓጓዘው በቀጣዮቹ የሚጓጓዘው እንደ ታክሲ፣ ባጃጅ እና ፎርስ ያሉ የትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም ነው። (ፎርስ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኝ ባጃጅ መሰል መጓጓዣ ነው) ከምሽት 11፡30 ጀምሮ የታክሲ መናኸሪያ የሆነውን አሸዋ ይደርሳል። ተጋፍቶ፣ ጠብቆ፣ ከታሪፍ በላይ ከፍሎ፣ የአንድ ጊዜ ጉዞ መንገዱን በሁለት ትራንፖርት ተሳፍሮ ትምህርት ገበታው ላይ ይገኛል። አብዛኛውን ጊዜ ቀጥታ ትራንስፖርት ስለማያገኝ አቆራርጦ ለመጓዝ እንደሚገደድ ይናገራል። ከ“አሸዋ” ወደ “ዋናው” በቀጥታ በመጓዝ ፋንታ ከአሸዋ መስቀለኛ ከዚያም ከመስቀለኛ ወደ ዋናው ይሳፈራል። በሂደቱ ጊዜውን እና ገንዘቡን እንደሚያባክንም በምሬት ይናገራል። “በየቀኑ በምመላለስበት ጊዜ ሦስት ፎርስ እይዛለሁ። በተማሪ አቅም ከባድ ቢሆንም ከመክፈል ውጪ አማራጭ የለኝም” ብሎናል።  

በተለይ በስራ መውጫ ምሽት ከ11 ሰዓት በኋላ ያለው ጊዜ ማቆራረጥ እና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ሕጋዊ አሰራር እየመሰለ ስለመሆኑ የምትናገረው የሳቢያን አካባቢ ነዋሪዋ ጸደኒያ ዓለሙ ነች። ፀደኒያ የስራ ቦታዋ አሸዋ ስለሆነ በየቀኑ ከሰኢዶ ወደ አሸዋ ለመመላለስ ትራንስፖርት ትጠቀማለች። እንደ ፀደኒያ ገለጻ ምሽት ላይ የትራንስፖርት እጥረት፣ አቆራርጦ መጫን የተለመደ ነው። “ባለ ታክሲዎቹ ይህንን የሚያደርጉት የርቀቱ ዋጋ እንዲጨምርላቸው ነው። መንገዱን ቆርጠው ሲጭኑ የሚያስከፍሉትን አይቀንሱም” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።  

በከተማ ታክሲ ስራ ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎች ተገልጋዩን በአግባቡና ለርቀቱ በተቀመጠው ታሪፍ ሊያስተናግዱ እንደሚገባ የሚገልፀው አቶ መሳይ ተክሉ ነው። እንደ አቶ መሳይ ገለፃ “አሽከርካሪዎች ሕጉን ተከትለው እንዲሰሩ ሁል ጊዜ አጠገባቸው ሕግ አስከባሪ መኖር የለበትም። በተጨማሪም ሕብረተሰቡ አግባብ ያልሆነ ክፍያ ሲጠየቅ “አልከፍልም” ማለት ይኖርበታል። መብቱን እራሱ ማስከበር ይችላል። የማይሆን ከሆነ ደግሞ ለሕግ አካላት መጠቆም ተገቢ ነው። ማሕበረሰቡ ከሕግ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ላይ የተወሰነ ክፍተት አለ። ምክንያቱም አሽከርካሪዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ አይጠቁሙም ወይም አልከፍልም አይሉም።  እያጉረመረሙ ይከፍላሉ።”

በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪነት የተሰማራው አቶ ጌትነት ኃይሉ ጥቂት ስነ-ምግባር የጎደላቸው አሽከርካሪዎች መንገድ አቆራርጠው ሲጭኑ መመልከቱን ነግሮናል። “አሽርካሪዎቹ አቆራርጠው የሚጭኑት ከታሪፍ በላይ ለማስከፈል ነው። በተለያየ ምክንያት ሥራ ላይ ያላሳለፉበትን የቀኑን ክፍለ ጊዜ ገቢ ለማካካስ በስራ መውጫ ሰዓት እጥፍ አስከፍለው የዕለት ገቢያቸውን ለመሙላት ይጥራሉ” ያለን ሲሆን የአሽከርካሪዎቹ ሕገ-ወጥ ድርጊት ተጠቃሚውን ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጉን እንደታዘበ አጫውቶናል።

በድሬደዋ አስተዳደር በጥቅሉ ከ11ሺ በላይ መደበኛ ታክሲዎች እና ተባባሪ ሚኒባሶች በተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰማርተው የታክሲ አገልግሎትን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። በትራንስፖርት ባለሥልጣን ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህዝብ እና ጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት አደረጃጀት ስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ነጋ “ከተገልጋዮች ጥቆማ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ተገንዝበናል” ይላሉ። “ይህንን መሰል ሕገ-ወጥ ተግባር ሚፈፅሙ አሽከርካሪዎችን በጥቆማዎቹ መነሻነት ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ጠንከር ያለ እርምጃ እንወስዳለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አክለውም “በከተማዋ የተሽከርካሪ እጥረት በሌለበት ሁኔታ መሰል ችግሮችን ለመፍጠር መንቀሳቀስ ተገቢ አይደለም። ማኅበረሰቡም መሰል ችግሮች ሲገጠጥሙት በአቅራቢያው ላሉ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች እና ትራፊክ ፖሊሶች ሊያሳውቅና መብቱን ሊያስከብር ይገባል” ብለዋል።

አቶ ተፈራ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ “ከታፔላ ወይም ከመስመር ውጭ መንቀሳቀስ እንዲሁም መነሻና መድረሻን አክብሮ አለመንቀሳቀስ ሌላው በከተማዋ የሚስተዋል ችግር ነው። በቀጥታ መጫን ሲገባቸው ግማሹን መንገድ በመቁረጥ ሙሉ ክፍያ ይቀበላሉ። ድርጊቱ ነዋሪውን ላልተገባ ተጨማሪ ወጪ እና ለእንግልት ይደርገዋል። በሕጉ በግልጽ እንደተቀመጠው ከታፔላ ውጭ መንቀሳቀስ ብር 300 የሚያስቀጣ ጥፋት ነው። ከታሪፍ ውጭ መጫን ደግሞ የብር 500 ቅጣት ያስከትላል” ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን በመገንዘብ አሽከርካሪው ከመሰል ተግባራት እንዲታቀብ ማኅበረሰቡም መብቱን ሊያስከብር ይገባል ብለዋል።  ስለሆነም አሽከርካሪው ቀደም ሲል አገልግሎት እየሰጠ ባለበት ሕጋዊ ታሪፍ መሰረት ለኅብረተሰቡ አገልግሎቱን እንዲሰጥ ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ በቅርቡ የታሪፍ ክለሳ በማድረግ ይፋዊ መረጃ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። በስተመጨረሻም ማኅበረሰቡ ሕገ-ወጥ አሽከርካሪዎችን እንዲጠቁም እና ከሕግ አስከባሪው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየት