ታህሣሥ 22 ፣ 2014

ለብክነት የተዳረገው የአዳማና አካባቢዋ የኤሌትሪክ ኃይል አጠቃቀም

City: Adamaምጣኔ ሃብት

ብክነትን ሁለት ዓይነት ነው ቴክኒካል እና ፋይናንሻል ነው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ለብክነት የተዳረገው የአዳማና አካባቢዋ የኤሌትሪክ ኃይል አጠቃቀም

የኢትዮጵያን የኤሌትሪክ ኃይል ሽፋን አስመልክቶ የዓለም ባንክ ከዓመታት በፊት ባወጣው መረጃ 18.5 በመቶ የሚሆነው ኃይል እንደሚባክን ይፋ አድርጓል። ሪፖርቱ በተጨማሪ 50 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንደሆነ አትቷል። የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል በበኩሉ የብክነቱን መጠን ቀንሶ 14 በመቶ ለማድረስ እንደሚሰራ አሳውቋል።

ለኃይል ብክነቱ መከሰት ልዩ ልዩ ምክንያቶች ተቀምጠዋል። የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ገጠራማ አካባቢዎችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ መስመር ቀድሞ ወዳልደረሰባቸው አካባቢዎች መስፋፋት፣ አግባብነት የጎደለው የኤሌትሪክ መገልገያዎች አጠቃቀም ደግሞ በዋናነት ተጠቅሰዋል።

“የኃይል ብክነትን ምትለካው በማሽኑ ብቃት (ኤፊሸንሲ) ነው። ብቃት ማለት ወደ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚው የገባው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከሰጠው ጥቅም ጋር ሲነጻጻር የሚገኝ ውጤት ነው” ያለችን ኤሌክትሪካል ፓወር ኢንጅነር ኢየሩሳሌም መስፍን ነች።  

“በሙያዊ አጠራሩ ‹ፖወር ፋክተር› ይባላል። ውጤቱ ከ0.8 (80%) ባላይ ከሆነ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው ማለት ነው” ትላለች።  

በሀገር ውስጥ ተመርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ ማሽኖች በጥሬ እቃዎች አመራረጥ ምክንያት ከፍተኛ ኃይል እንደሚያባክኑም ተናግራለች። “የኤሌትሪክ ምጣድ፣ ምድጃዎች፣ በኤሌትሪክ የሚንቀሳቀሱ ሞተሮች እና ሌሎችም ማሽኖች በሐገር ውስጥ ባለሙያዎች ሲመረቱ ስታንዳርዶች አልተቀመጡም። ሁሉም እንደ ፍላጎቱ ነው የሚሰራው። የኃይል ብክነትን የሚያስበው የለም። በአብዛኛው ከግምት ውስጥ የሚገባው ጥንካሬው ብቻ ነው” የሚል ማብራሪያ ሰጥታለች።

አብዱልከሪም አሊ አዳማ ከተማ ፖስታ ቤት አካባቢ የኤሌክትክ እንጀራ ምጣድ ሰርቶ በመሸጥ ይተዳደራል። "ለእኛ አሳሳቢው ጉዳይ ምጣዱ በአግባቡ ተቦርቡሮ መጋል (መስማት) መቻሉ ነው" የሚለው አብዱልከሪም የሚጠቀማቸው ግብአቶች ከማንኛውም የኤሌክትሪክ መሸጫ መደብር ይገዛቸዋል። ብዙ ኃይል በልቶብኛል ብሎ ቅሬታ ያቀረበ ደንበኛም አላጋጠመውም።

የጥገና ባለሙያው አንዱዓለም በለጠ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ይጠግናል። "ለማሞቅም፣ ኃይል ለመቆጠብም ፈጣን ስለሆነ ምጠቀመው 0.7 ሬዚስተር ነው። ከዚህ በተጨማሪ ፋይበር ግላስ እጠቀማለሁ” ላለ በኋላ አብዛኛው ሰው ቤት የሚገኙት ምድጃዎች የኃይል ፍጆታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ታዝቧል። "ከውጭ የሚገቡት ምድጃዎች አይሲ ስላላቸው ኃይልን በልኩ ይመጥናሉ። እነሱ የሚገለገሉበት ሰርኪውት ገበያ ላይ ቢገኝ እኛም ልንጠቀምበት እንችላለን" በማለት ሐሳቡን ይቋጫል።

“የኃይል አጠቃቀም ብክነት ከሰብ ስቴሽን እስከ ደንበኞች ድረስ የሚገኝ የጋራ ችግር ነው” የሚለው አቶ ነጻነት ዘለቀ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባልደረባ ነው። የኃይል መቆራረጥ እና ደንበኛ በሚፈልገው ሰዓት የሚፈልገውን ኃይል አለማግኘትንም በኃይል አጠቃቀም ዙርያ ተደጋግመው የሚነሱ ችግሮች መሆናቸውን አንስቷል።

"200 ኪሎ ዋት ትራንስፎርመር የሚፈቀደው ርቀት 500 ሜትር ነው። ነገር ግን እስከ 1000 ሜትር ርቀት ድረስ ሥራ ላይ ሊሰራ ይችላል። ይህ የኃይል ብክነትን ያስከትላል" የሚለው ነጻነት ዘለቀ የማስተላለፊያ መስመሮች እና መሳሪያዎች የመቀየር እና የአቅም ማሳደግ ስራ ሊሰራላቸው እንደሚገባ ያምናል።

በኤሌክትሪክ እቃዎች ጥገና  ላይ ተሰማርቶ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ተካበ ዘመዱ “በጋራ በምኖርበት ግቢ ውስጥ  በጋራ የምንጠቀመው የእንጀራ ምጣድ አለ እንዲሁም ሌሎች መሳሪያዎች አሉ። እነኚህ ከፍተኛ ፍጆታ እንዳላቸው አውቃለሁ። ነገር ነገር ግን ባለው የኃይል እጥረት ምክንያት ለካርድ የምናወጣው ወጪ እጅግ አማሮናል” ይላል። የዚህ መንስዔ ደግሞ የሀይል ብክነትነት መኖሩ እንደሆነ ይናገራል።

"የኃይል መጠኑ ስለሚቀያየር አንዳንዴ በ100 ብር ካርድ ሦስት ቀን ድረስ ስንጠቀም የ200 ብር ካርድ ለግማሽ ቀን የማይበቃበት ጊዜ አለ" ሲል ብክነቱ ያደረሰበትን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ኦልጅራ "ይህ ትክክለኛ ሀሳብ ነው። በዚህ ዓይነት የሚመጣን የገንዘብ እና የኃይል ብክነት ለማስተካከል ትራንስፎርመሮችን አቅም እስከ 1200 ኪሎ ዋት ድረስ ማሳደግ እየሰራን ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ኃላፊው የአዳዲስ መስመሮች ዝርጋታ ችግሩን በሚፈታ መልኩ በኢንሱሌትድ ገመዶች እና በኮንክሪት ምሰሶዎች እየተሰራ ነው። ይህንንም ስካላር በተባለ የኮምፒውተር ሲስተም ቁጥጥር ይደረግበታል ሲሉ ነግረውናል።

ማሽኖችን ከኤሌክትሪክ ምንጭ ጋር በተገቢው ሁኔታ አለማያያዝ፣ ከኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር አያይዞ መተው  በተደጋጋሚ መታዘቡን የሚናገረው በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ት/ቤት መምህር የሆነው አብነት ጎሳዬ ነው። 

ይህንን ዓይነት ችግር በተለያዩ ድርጅቶች እና ጋራጆች ውስጥ መታዘቡንም ይናገራል። "ማሽኖች በተገቢው መንገድ ስፕላይስ ተደርገው መበየድ (ሶልድ) መደረግ፣ መጠቅለል መቻል አለባቸውም" ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

"የመጀመሪያው መፍትሔ ለባለሞያዎቹ ስለሚገለገሉት ማሽኖች ባህሪ ተጨባጭ ትምህርት መስጠት ሲሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ቢያደርጉ የሚያተርፉትን ገንዘብ በቁጥር እና ተጨባጭ መረጃ ማስረዳት ያስፈልጋል።" ሲል ሀሳቡንም ይደመድማል። 

"ብክነትን ሁለት ዓይነት ነው ቴክኒካል እና ፋይናንሻል ነው። በቴክኒክ ረገድ እንደሀገር ከሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል 12% የኃይል ብክነት አለ። በፋይናንስ ረገድም በአዳማ ዲስትሪክት በቅርብ ወራት በወሰድናቸው ተከታታይ እርምጃ የመሰብሰብ አቅማችንን ከ48 % ወደ 70.8 አድርሰናል" ያሉን አቶ ብርሃኑ ኦልጅራ “ቴክኒካል ብክነት ማለት ከሰብስቴሽን ተሰራጭቶ ደንበኞች ቆጣሪ ድረስ ኃይል ላይ የሚደርስ ብክነትን ያሳያል፤ የፋይናንሻል ደግሞ በቆጣሪ አንባቢዎች በአግባቡ ከማይቆጠር ኃይል ጀምሮ በሰዓቱ እስከማይከፈል የአገልግሎት ክፍያን ያጠቃልላል” ካሉ በኋላ ተከታዩን መልእክት አስተላልፈዋል። “ሕብተረሰቡ ኃይል ቆጣቢ መሳሪያዎች ቢጠቀም፣ የኤሌትሪክ መሳሪያዎችን የመጠቀሚያ ሰዓት ቢመርጥ እና የኤሌትሪክ ክፍያውን በጊዜው ቢከፍል መልካም ነው”

አስተያየት