መምህር ይርጋወሰን የማርያምወርቅን የሚያውቁ “ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ ስር እንደሌለው ዛፍ ይቆጠራል” በምትል ዘወትራዊ አባባላቸው ያስታውሷቸዋል። የዚህ አስተሳሰባቸው ውጤትም ይርጋወሰን “ጥንስስ” አጠቃላይ የግል ሙዝየም እንዲመሰርቱ ምክንያት ሆኗል። በግል ሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙት ቅርሶች ለ39 ዓመታት ተሰባስበው ለ26 ዓመታት ያለ ምንም ክፍያ ለሕዝብ ዕይታ የቀረቡ እድሜ ጠገብ ቅርሶች ይገኛሉ። መምህር ይርጋወሰን ኢትዮጵያ የታሪክ ባለቤት መሆኗን፣ የብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ምድርነቷን፣ ለውጭ ኃይሎች እንዳልተንበረከከች ያሳያሉ ያሏቸውን አብዛኛዎቹን ቅርሶች ያሰባሰቡት በግዢ ነው። በሥራ ምክንያት በተዘዋወሩባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች ታሪካዊነታቸውንና ጥንታዊነታቸውን ያመኑባቸውን ቅርሶች በራሳቸው ገንዘብ ይገዛሉ። የተግባራቸውን በጎነት የተመለከቱ ሰዎችም ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ መጻሕፍትን በስጦታ እንዳበረከቱላቸው ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
“ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በመምህርነት የተመረኩት በ1974 ዓ.ም. ነው። ከምርቃት በኋላ ለሥራ ምደባ እጣ ሳወጣ አስመራ ደረሰኝ። በወቅቱ አስመራ የኢትዮጵያ አንድ ክፍለ ሀገር ነበረች። አስመራ ባርካ አውራጃ አርቆርዳት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አስመራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሰባት ዓመታት ያህል በመምህርነት አገልግያለሁ” በማለት የሥራ ጅማሬያቸውን የሚናገሩት መምህር ይርጋወሰን ከአስመራ በተጨማሪ አርሲ ነገሌ፣ በጉራጌ፣ በሐዋሳ በድምሩ ለ39 ዓመታት በመምህርነት ስለ ማገልገላቸው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። መ/ር ይርጋወሰን የጆኦግራፊ እና የታሪክ መምህር ናቸው።
ከዚህ በፊት “ተናጋሪው ዛፍ” የሚል መጠሪያ ያለው የግጥም መጽሐፍ ለሕትመት አብቅተዋል። ዝግጅቱ ተጠናቆ አሳታሚ በማጣት ለህትመት ያልበቃ “ከዶቃ እስከ ሙዚየም የሕይወት ልምድና ቅርሶቻችን” የተባለ የግለ-ታሪክ መጽሐፍም አዘጋጅተዋል።
ለተማሪዎቻቸው የተግባር ማስተማሪያ እንዲሆን የጀመሩት ቅርሶችን የማሰባሰብ ሥራ ሕብረተሰቡን ወደ መጥቀም የተሸጋገረው በ1987 ዓ.ም. ነበር።
ቅርሶችን ወደ አንድ ቦታ ለመሰብሰብ የፈለጉበት ዋነኛ ምክንያት ለተማሪዎች የመማሪያ ማገዣ ይሆናል የሚል ሲሆን ቀድመው በእጃቸው የገባዉ ቅርስ የትግረኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት እንደሆነ ያስታውሳሉ።
በቤታቸው ውስጥ ብቻ የተገደበው የታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ማሰባሰብ ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው “ጥንስስ” ተመሰረተ። "ትርፌ ትውልድ ስለ ሀገሩ ማወቁ ነው። ለእዚህ ነው ያለምንም ክፍያ በፍላጎቴ እየሰራሁ የምገኘው። ትርፌ ብዙ ሰዎች መጥተው ኢትዮጵያ ሀገራችው ምን እንደምትመስል ቢያንስ በትንሹ ማወቃቸው እና ለሌሎች ማስተማራቸው ነው" ብለዋል። ወደፊት ሰፊና ምቹ የማሳያ ስፍራ ኖሯቸው ሥራቸውን አጠናክረው የመቀጠል ፍላጎት አላቸው። መንግሥትን ጨምሮ ፍላጎቱ እና አቅሙ ያለው ማንኛውም ድርጅትና ግለሰብ እንዲደግፋቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ከስብስቦቻቸው መካከል ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው እድሜ ጠገብ የፊደል ገበታ ስለመኖሩ አጫውተውናል። “ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ተጽፎ ሲያገለግል ለቆየው የፊደል ገበታ ልዩ ስሜት አለኝ” የሚሉት መምህሩ፤ የፊደል ገበታው ከደርግ ውድቀት በኋላ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት አቋርጧል። ከፊደሎቹ መካከል አስራ አምስቱ አሁን ባለው ትውልድ አለመታወቃቸው እና አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ “ነገሩ ሆነ ተብሎ የተደረገ ነው” ብለው እንዲያምኑ እንዳስገደዳቸውም አልሸሸጉም።
ጥንስስ ሙዚየም በአሁን ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። እነደ መስራቹ እምነት ዩንቨርሲቲው ለሙዚየሙ ማረፊያ የሚሆን አነስተኛ ክፍል ያበረከተው የያዛቸው ቅርሶች ለመምህራን እና ተማሪዎች የመማማሪያ ግብአት እንደሚሆኑ በማመንና በቅንነት ነው።
የ"ጥንስስ" ሙዚየምን ቅርሶች በሁለት ዋና ዋና ምድቦች መመልከት ይቻላል። ጥንታዊ መጽሐፍት፣ መዛግብት፣ ስዕሎች እና ሰነዶች የመጀመርያዎቹ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ጥንታዊ የሆኑ ባህላዊ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ቅርጻ ቅርጾችም ይገኛሉ።
በዚህ የግል ሙዚየም ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ግልግጋሎት ላይ የዋሉ የመገበያያ ገንዘቦች፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ሲጠቀሙበት እና ከሶስት ሺህ ዓመት በፊት ያስቆጠረው ከቆዳና ከእንጨት የተሰራ አልጋ፣ ከ1891 ዓ.ም. ጀምሮ የተጻፉ የታሪክ መጻሕፍት፣ ከጉማሬ ቆዳ የተሰራ ጋሻ፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪኮች እና ስፍራዎች የሚያመላክቱ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ የብራና መጻሕፍት ይገኙበታል። ኢትዮጵያ የዋሻ ዉስጥ ስዕሎች በመስራት ቀዳሚ መሆኗን የሚጠቁሙ ሃያሺህ ዓመት ያስቆጠረ ፖስትካርድ በአጋጣሚ እጃቸዉ ያስገብት መ/ር ይርጋወሰን በሙዚየማቸዉ ዉስጥ እንደማሳያ አስቀምጠዋል።
ሙዚየሙን በመጎብኘት ላይ የነበሩ ተማሪዎች ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወጣቱ ትውልድ ማንነቱን እንዲረዳ የሚያደርጉት ተመሳሳይ ቅርሶች ተጠብቀው መቆየታቸው አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።