ሚያዝያ 11 ፣ 2015

የምሽት እግር ኳስ ጨዋታዎች በድሬደዋ ከተማ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል

City: Dire Dawaዜናየአኗኗር ዘይቤወቅታዊ ጉዳዮች

በድሬዳዋ ከተማ ከ6 በላይ አርቲፊሻል ሳር የለበሱ እግር ኳስ ሜዳዎች እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ እግር ኳስ ጨዋታዎች ይካሄድባቸዋል

Avatar: Ephrem Aklilu
ኤፍሬም አክሊሉ

የምሽት እግር ኳስ ጨዋታዎች በድሬደዋ ከተማ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ገናና በሆነችው ድሬዳዋ ከተማ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የእግር ኳስ እየተዘወተረ መምጣቱ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል። ሰው ሰራሽ ሳር የተነጠፈባቸው ሜዳዎች ለአንድ ሰዓት 900 ብር ይከፈልባቸዋል።   

የከተማዋ የአየር ጠባይ ሙቀታማ በሆነው ድሬዳዋ ባልተለመደ መልኩ የምሽት እግር ኳስ ጨዋታዎች እየተለመዱ ሲሆን የከተማዋን ነዋሪዎችን ቀልብም እየሳበ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ እየሆነ የመጣው የምሽት ጨዋታ ከእግር ኳስ ሜዳ የራቀውን ስፖርት አፍቃሪ ወደ ሜዳ በመመለስ እና የድሬዳዋን በስፖርት ስመ ጥር መሆን ያድሳል ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸዋል ሲሉ ነዋሪዎቹ ጨምረው ይናገራሉ።

አዲስ ዘይቤ በድሬደዋ ከተማ ተዘዋውራ የተመለከተቻቸው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 6 የሰው ሰራሽ ሳር የለበሱ የእግር ኳስ መጫዋቻ ሜዳዎች በአንድ ጨዋታ ማለትም ለአንድ ሰዓት እስከ 900 ብር እየተከፈለባቸው በኪራይ ያጫውታሉ።

ባልተለመደ መልኩ እስከ ምሽቱ 6 እና 7 ሰዓት ድረስ ለጨዋታ ክፍት የሚሆኑት ኳስ ሜዳዎቹ የስራ ሰዓታቸው በራሱ በበርካታ ወጣቶች ዘንድ ተመራጭ እያደረጋቸው መጥቷል ተብሏል። 

ከሜዳዎቹ አንዱ በሆነው ኮኔል የአርቴፊሻል የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ዳኛና የሜዳው ተቆጣጣሪ ወጣት መሀዲ መሀመድ በአንድ ምሽት እስከ 8 ጨዋታዎችን እንደሚያስተናግዱ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

የድሬ ከነማ የስፖርት ክለብ ደጋፊ ነኝ የሚለው ሙጃሂድ ሱሌ የተባለ ወጣት በበኩሉ በጥቂት ጎልማሶች የተጀመረው የምሽት ጨዋታው ወጣቶችን ከተለያዩ ሱስና የወንጀል ድርጊቶች እንዲጠበቁ ማድረጉን ይጠቁማል።

ከልጅነት ጀምሮ ለረጅም ዓመታት የድሬዳዋን እግር ኳስ በመደገፍ የሚታወቀው አቶ ዲዲዬ ዩሱፍ የምሽት እግር ኳስ ጨዋታ ከተጨዋቾች ባለፈ ደጋፊዎች የምሽቱን ድባብ ተጠቅመው ወደ ሜዳ እየተመለሱ ነው ባይ ነው። 

ለእግር ኳስ ውጤታማነት ደጋፊዎች ያላቸው ሚና ትልቅ መሆኑን የሚገልጹት በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ  የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ማንደፍሮ ዳኘው በእግር ኳስ ጨዋታዎቹ ምክንያት ከሜዳ ርቆ የቆየውን የስፖርት አፍቃሪ ወደ ሜዳ ከመመለሱ ባሻግር እግር ኳስ አፍቃሪው ክለቡን በመደገፍ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የተጀመሩት የምሽት እግር ኳስ ጨዋታዎች በር እንደሚከፍቱ ተናግረዋል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ከዋንጫ ተፋላሚነት ይልቅ ሁሌም ላለመውረድ ይጫወታል በሚል የሚተቸው የእግር ኳስ ፊት አውራሪ ከተማዋን ድሬዳዋን ለወከለው የድሬዳዋ ከተማ የእግር ኳስ  ክለብ እነዚህ የምሽት ጨዋታዎች ምናልባት ተተኪዎችን በማፍራት የእግር ኳስ ዝናውን እንደሚመልስ ተስፋ ተጥሎበታል። 

አስተያየት