ሚያዝያ 11 ፣ 2015

አንዷለም አራጌ እና ኢዜማ ተለያዩ

City: Addis Ababaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የኢዜማ ምክትል መሪ ሆነው ያገለገሉት አቶ አንዷለም አራጌ ኢዜማ ከገዢው ፓርቲ ያለው ግንኙነት ለመልቀቃቸው ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

አንዷለም አራጌ እና ኢዜማ ተለያዩ

ታዋቂው ፖለቲከኛ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ(ኢዜማ) አመራር የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌ ከፓርቲያቸው መለይየታቸውን ለፓርቲው ባስገቡት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡ አቶ አንዷለም “ አይነግቡ እና ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ” የያዙት ህልም እውን ስለማይሆን ከፓርቲው ጋር መቀጠል አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ 

አቶ አንዷለም አራጌ ለፓርቲው ባስገቡት እና በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ባሰራጩት የመልቀቂያ ደብዳቤ ላይ “ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ ድርሳን ላይ ከሰፈረው መከራዋ ሁሉ የከፋውን በምታስተናግድበት በዚህ ዘመን” ለሀገሪቱ እና ለዜጎቿ መድህን ይሆናል የተባለው ፓርቲው “የተሳከረ ሚና” እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. የኢዜማ ምክትል መሪ ሆነው ተመርጠው የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌ፣ ኢዜማ አሁን እየተጓዘበት ካለው የተሳሳተ መንገድ “ለመመለስ በማይችልበት መዳፍ” ውስጥ ወድቋል ሲሉም ከፓርቲው ዓላማ እና ከህዝቡ ፍላጎት መራቁን ገልፀዋል።

ኢዜማን አይነ ግቡና ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ለማድረግ እንደድርጅት የያዙትን ህልም ደጋግመው ፈትሸው አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸው ከኢዜማ ጋር እንዳይቀጥሉ እንዳደረጋቸው የገለፁት አቶ አንዷለም ከዚህ በኋላ በፓርቲው ውስጥ ለመቀጠል የሚያስችል ምንም ምክንያት የለኝም ሲሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ከፌደራል መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት አመራር ከተመረጡባቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ሲሆን፣ አሁን የፓርቲው መስራች አባል የሆኑት ፖለቲከኛ ለመልቀቃቸው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ፓርቲው በተደጋጋሚ የገዢው ፓርቲ ተለጣፊ ሆኗል በሚል መታማቱን ያረጋገጠ ሆኗል።

“ሰዎች አሁንም የፓርቲው አመራር እንደሆንኩ እያሰቡ” ለኢዜማ ውሳኔዎች እና እንቅስቃሴዎች የውግዘቱ እና የውዳሴው ተቋዳሽ ሆኛለሁ ያሉት አቶ አንዷለም፣ ኢዜማን “የአገዛዝ ጡጫ እንዲፈረጥም አድርጓል” ሲሉ ወንጅለዋል።

ሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደ የኢዜማ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የአመራር ምርጫ ሲካሄድ አቶ አንዷለም አራጌ 326 ድምፅ አግኝተው ተሸንፈዋል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ኢዜማን ለሶስት ዓመታት እንዲመሩም በጉባዔው ተመርጠዋል። ከኢዜማ ምስረታ አንስቶ የፓርቲውን የምክትል መሪነት ቦታ ይዘው የቆዩት አቶ አንዷለም አራጌም በድምፅ ብልጫ የምክትል መሪነት ቦታውን ለአቶ ዮሐንስ መኮንን አስረክበዋል።

አቶ አንዷለም በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ፖለቲከኛ ሲሆኑ በዚህ ተሳትፏቸው ምክንያት ለበርካታ አመታት ለእስር እና እንግልት ተዳርገው መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ 

አስተያየት