ሚያዝያ 10 ፣ 2015

ኢትዮጵያዊያን በሱዳን ግጭት የማንነት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ሰግተዋል

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

ለግጭቱ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስታት እጅ አለበት በሚል መወራቱ ለሃገራቱ ዜጎች ከፍተኛ ስጋት ቢደቅንም በሀገራቱ በኩል ስለ ጉዳዩ የተባለ ነገር የለም

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ኢትዮጵያዊያን በሱዳን ግጭት የማንነት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ሰግተዋል

ባለፈው ቅዳሜ ለተነሳው የሱዳን ግጭት “የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስታት ጣልቃ ገብነት አለበት” በሚል እየተወራ መሆኑን ተከትሎ የሃገራቱ ዜጎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተዋል። 

በካርቱም ከተማ ጅሬፍ በተባለው አካባቢ ነዋሪ የሆንችው ኢትዮጵያዊት ኤዶም ንጉሴ (ስሟ የተቀየረ)  ቃለ-መጠይቁን እየሰጠችን ባለችበት ወቅት እንኳን በቅርብ ርቀት የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማት ትናገራለች።

ከወራት በፊት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አቅራቢያ አል-ፋሻጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የሱዳን ወታደሮች ተገድለዋል በሚል በሱዳናዊያን ዘንድ "እኛ እያኖርናችሁ መንግስታችሁ ወታደሮቻችንን ይገድላል" የሚል ተቃውሞ በኢትዮጵያውያን ላይ መድረሱን የመረጃ ምንጫችን ታስታውሳለች። 

በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምንም የተለየ ነገር እያደረገ አይደለም የምትለው አስተያየት ሰጪዋ የሚሆነውን በትዕግስት ከመጠበቅ ውጪ መረጃ የሚሰጥ እና አይዟቹ ባይ አካል እንደሌለ ትናገራለች።

ሌላኛው የካርቱም ነዋሪ ኢትዮጵያዊ አቶ ጌታቸው ምህረቱ (ስሙ የተቀየረ) የጦርነቱ መጠን እየጨመረ እንጂ የመቀነስ ነገር አለማሳየቱን ጠቁሞ የሱዳን ህዝብ ገራገር ቢሆንም ወደ ፊት ግን የነገሮች መለዋወጥ እንደሚያሰጋው ገልጿል። በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ለዜጎች አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ስጋቱን መቀነስ ይገባል ይላል።

የመብራት አገልገሎት ባለመኖሩ የመረጃ ልውውጥ መቋረጡን የገለፀው አቶ ጌታቸው ከካርቱም ውጪ ስላለው ሁኔታ በቂ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን ይናገራል።

የሱዳን ህዝብ መልካም ህዝብ ነው የሚሉት በሱዳን ያሉ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአሁኑ ወቅት የግጭቱ  ሁኔታ መልክ ባለመያዙ ሁኔታው አደጋ ሊደቅን እንደሚችል ሰግተዋል። በግጭቱ ኢትዮጵያና ኤርትራ እጃቸው አለበት የሚለው ወሬ ቢናፈስም በጉዳዩ ዙሪያ ተጨባጭ መረጃ ካለመኖሩ ባሻገር ከሱዳን መሪዎችም ሆነ ከኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት የተባለ ነገር የለም።

እንዲያውም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሱዳን ህዝብ ግጭትን የመፍታት አቅምና ልምድ ያለው መሆኑን በመጥቀስ ችግሩ ወደ መረጋጋት እንዲመጣ የኢትዮጵያ መንግስት ምኞት መሆኑን ገልፀዋል። 

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ልኡክ ወደ ሱዳን ሊያመራ እንደነበር መረጃዎቸ ቢኖሩም በግጭቱ መከሰት ምክንያት ጉዞው ተሰርዞ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በኢትዮጵያ ከሱዳኑ አምባሳደር ጀማል ኤል ሼክ ጋር የተወያዩ ሲሆን ችግሩ በውይይት እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ፋናቢሲ አስፍሯል።

በካርቱም ኤምባሲ፣ በኦምዱሩማንና አል_አረቢያ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት ያላት ኢትዮጵያ ኤምባሲው በፌስቡክ ገጹ ካወጣው አጭር መግለጫ እና ካጋራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአረብኛ ልጥፍ ውጪ ስለተገደሉት እንዲሁም አል-ጃውዳ ሆስፒታል አስክሬናቸው ተቀምጦ ቀብራቸው ስላልተፈጸመ ኢትዮጵያውያን ያለው ነገር የለም።

የጃንጃዊድ ሚሊሺያ መሪ እና በዳርፉርና ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ለበርካቶች ህይወት ማለፍ ምክንያት እንደሆነ የሚጠቀሰው ሃምዳን ዳጋሎ በቅጽል ስማቸው ሄሚቲ ከወራት በፊት ወደ ኤርትራ ማምራታቸውን ተከትሎ የምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ ጋዜጠኛው ማርቲን ፕላውትን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ይዞት ሊመጣ የሚችለውን የጸጥታ ስጋት አደጋ ማስፈራቸው ይታወሳል።

አሁን በሱዳን የተከሰተውን ደም አፋሳሽ ግጭትም ከዚህ ጋር የሚያያይዙት አልጠፉም፡፡ ይሁን እንጂ በኤርትራ መንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም። ከዚህ አለፍ ሲልም የማእድን ከበርቴው ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ከወራት በፊት ወደ ሩሲያ ያደረጉትን ጉዞ ከወቅታዊው ችግር ጋር በማያያዝ መሳሪያ ስለማምጣታቸው የሚገልጹ አሉ። 

በሌላ በኩል የግብጽ ድጋፍ አላቸው የሚባሉት መከላከያ ጀነራሉ አብደልፈታህ አብደልራህማን አል ቡርሃን ባለፈው አመት በካይሮ በነበራቸው ጉብኝት ስለሁለቱ ሀገራት መልከ ብዙ ግንኙነትና ትብብር ቢወያዩም ግብጽ ዋነኛ ወዳጅ እንደማትሆን ሲገለጽ ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ ጀነራሉ በአረብ ሀገራት በኩል ድጋፍ እንዳላቸው ይነገርላቸዋል።

ያም ሆነ ይህ ሁለቱ ፈርጣም ሃይል ያላቸ የሠራዊት አዛዦች በፈጠሩት ግጭት ከ200 በላይ ንጹሃን መገደላቸንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ስለመቁሰላቸውን መረጃዎች እየወጡ ነው። አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ቢያቀርቡንም ግጭቱ እንደቀጠለ ነው።

አስተያየት