እድሜያቸው ከአስር አመት በታች የሆኑ ሴት ህጻናትን በእድሜ በሶስት እና አራት እጥፍ ከሚበልጣቸው ወንድ ጋር መዳር እንደ ባህል በሚቆጠርበት የጎንደርና አካባቢው ማህበረሰብ ባሳለፍነው የጥርና የካቲት ወራት ብቻ በሰሜን ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በምዕራብ ጎንደር ዞን ውስጥ ከ789 በላይ ያለ እድሜ ጋብቻ መፈጸሙን አዲስ ዘይቤ ከተለያዬ ምንጮች አረጋግጣለች።
የጥርና የየካቲት ወራት በብዙው የሀገራችን ክፍል ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ጉምሎች ጎጆ ቀልሰው ትዳር የሚመሰሩትበት ወራት ናቸው። ጥር 11 ጥምቀት መዋልን ተከትሎ እስከ አስተርዬ ማርያም በተለያዬ የሀገራችን ክፍል ወሩን በሙሉ ታቦታትን በማንገስ ሲያከብሩ ወጣት ሴቶች አምረውና ተውበው፣ ወንዶችም እንዲሁ የከንፈር ወዳጃቸውን ለመጎብኘት ወይም ውሃ አጣጫቸውን ለማግኘት ወደ ማርገጃ ይወርዳሉ።
የአስተርዮ ማርያም ነይልኝ የኔ አለም
በዘገሊላ ዕለት፣ በዘገሊላ ዕለት ነይልኝ በኔ ሞት።
እያለ ወንዱ የከንፈር ወዳጁን በሚያሞጋግሰበት በእነዚህ ሀይማኖታዊ ክበረ በዓላት ሴቷም በበኩሏ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› እንዲሉ ቀልብን በሚስብ እስክስታ ወዳጇን ታማልለዋለች። በዚሁ አግባብ ተዋውቀው፣ ተቀራርበው ትዳር የሚመሰርቱ፣ ጎጆ የሚቀልሱ እልፍ ኢትዮጵያዊያን ቢኖሩም በአንጻሩ እድሜያቸው ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ የ5 ዓመት ህጻናትም ያለ እድሜ ጋብቻ ሰለባ ይሆናሉ።
‹‹ልጅህን ለልጀ… ›› በሚል ኃላ ቀር ብሂል ወዳጅ ለወዳጁ ገና ያልተወለዱ ልጆቻቸውን ሳይቀር ቀድመው ለትዳር የሚያመቻቹ ወላጆች ቁጥር ቀላል አይደለም። ልጆች ክፉ ደጉን ሳያውቁ፣ ራሳቸው መወሰንና የትዳር አጋራቸውን መመረጥ ሳይችሉ፣ የትዳር አጋራቸውን እንኳን በመልክ ሳያውቁት በወላጆቻቸው የወዳጅነት ማጠናከሪያና ማሰሪያ ገመድ ይሆናሉ። ይህ ኋላ ቀር ድርጊት ከሌላው የሀገራችን ክፍል በባሰ ሁኔታ በጎንደር እና አካባቢው እንደ ባህል ተቆጥሮ ዛሬም ድረስ ይከናወናል።
ያለ እድሜ ጋብቻ በጎንደር ስለምን እንደ ባህል ሊታይ ቻለ?
ይህ ከጥንት እስከዛሬ በሰፊው የጎንደር ህዝብ ዘንድ የሚተገበር ድርጊት ከማህበረሰቡ ውግዘት አልፎ መንግስትንም ያሳሰበ ሁኔታ በመሆኑ ያለ እድሜ ጋብቻ ጎጅ መሆኑ ታምኖበት በህግ ተደንግጎ ከዚህ ልማዳዊ ማህበራዊ ክንዋኔ ወላጆች እንዲቆጠቡ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም ያለእድሜ ጋብቻ በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ የሚደገፍ በመሆኑ ድርጊቱ ከአመት አመት በመቀነስ ፋንታ እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታል።
አዲስ ዘይቤ ያለእድሜ ጋብቻ ዛሬም ድረስ አሳሳቢ በሆነባቸው የጎንደርና አካባቢዋ ተንቀሳቅሳ ሁኔታውን የቃኘች ሲሆን ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት በመንግስትና በህዝቡ ዘንድ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማሳዬት በጎንደር ከተማ እና አካባቢዋ ተንቀሳቅሳ የከተማዋን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችን እና ነዋሪዎችን አነጋግራልች።
ያለ እድሜ ጋብቻ በጎንደር እውን ባህል ነውን? ለሚለው የአዲስ ዘይቤ ጥያቄ መልስ የሰጡት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህልና ቱሪዝም እሴት ቡድን መሪ አቶ ልዕልና አበበ “ያለ እድሜ ጋብቻ በጎንደር በከተማዋ ውስጥ ስለሌለ ባህልና ቱሪዝም መምሪያው ባህል ነው ወይስ አይደለም በሚለው ጉዳይ ግልፅ የሆነ መረጃ የለም። ይሁን እንጅ ያለእድሜ ጋብቻ ጉዳቱ እንዳለ ሆኖ ጥቅምም አለው።
ያለ እድሜ ጋብቻ የሚፈፀመው የልጅቷ ቤተሰቦች የገቢ ምንጫቸው ዝቅተኛ ከሆነና ልጅቷን ተንከባክበው ማሳደግ የማይችሉና ድሃ ከሆኑ ሃብታም ለሆኑት ሰዎች ልጃቸውን በማጋባት አብራ እንድታድግ ይደረጋል። እድሜዋ ለአቅመ ሄዋን እስከሚደረስ በአገባት ባል ቤተሰቦች ትልቅ ጥበቃና እንክብካቤ ይደረግላታል፣ መኝታ እንኳ ከአማቶቿ ጋር እንድታድር ይደረጋል” ብልዋል።
ሴት ልጅ የግብረ ስጋ ግንኙነት እስካልፈፀመች ድረስ ጉልህ ችግር ሊደርስባት አይችልም የሚል እሳቤ በማህበረሰቡ ዘንድ መኖሩ ያለ እድሜ ጋብቻን ለመከላከል ከባድ እንዳደረገው የሚግልጹት አቶ ልዕልና “ያለእድሜ ጋብቻ ሁለት የማይዛመዱ ወገኖችን ያስተሳስራል። ልጆቹም ከቤተሰቦቻቸው በሚሰጣቸው ማጫ የኑሮ ደረጃቸው እየተሻሻለ እንዲሄድ ይረዳቸዋል” ተብሎ እንደሚታመንም ጨምረው ገልጸዋል።
አዲስ ዘይቤ በሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶችና ህፃናት ቢሮ እና በምዕራብ ጎንደር ተዘዋውራ በጎንደርና አካባቢው ዛሬም ድረስ እየተፈፀመ ባለው ያለ እድሜ ጋብቻና ድርጊቱን ለማስቆም በመንግስትና በማህበረሰቡ ዘንድ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ምን እንደሚመስል ለማስቃኘት ስትሞክር ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው ከጥር 25 እስከ ይካቲት 02 ቀን 2015 ዓ.ም 397 ያለ እድሜ ጋብቻ ሊፈፀም እንደሆነ ጥቆማ ደርሷቸው ዞኑ በማጣራት ላይ ሲሆኑ ምዕራብ ጎንደር ዞን ደግሞ 187 ያለ እድሜ ጋብቻ ሲፈፅሙ ተይዞው 119ኙን ማቋረጥ መቻሉን ለመረዳት ተችሏል።
በተመሳሳይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 205 ያክል ያለእድሜ ጋብቻ ሊፈፀም በዝግጅት ላይ የነበረ ሲሆን 85 ያክሉ ጋብቻው እንዲቋረጥ ተደርጓል፣ 6ቱ እንዲያገቡ የተፈቀደ እንዲሁም 6 በድብቅ የተፈፀመ እና 112 ያክሉ በሂደት ላይ ያለ መሆኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሴቶች ግንዛቤና ንቅናቄ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ታደሰ ሙጨ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
በሰሜን ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በምዕራብ ጎንደር ዞን ውስጥ ብቻ 789 ገደማ ያለእድሜ ጋብቻ በዘንድሮው ጥር ወር እና የካቲት ወር መፈጸሙን የገለጹት የሴቶችና ህፃናት ሃላፊዎች ያለእድሜ ጋብቻን የሚፈፅሙ ቤተሰቦች በመንግስት አካል ሲያዙም "የምታገብዋን ህፃን በመደበቅ ሌላ ከ18 ዓመት በላይ የሆናትን ልጅ እንደሚድሩ በማስመሰል እና እድሜዋን ለማወቅ ለሚደረገው ምርመራም ትልቋን ልጃቸውን እንደሚያስመረምሩ" ለመረዳት ተችሏል።
ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም መንግስት የተለያዬ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም የማህበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ ካልታከለበት ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል የሚገልጹት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ቡድን መሪ የአቶ ጌታሰው ታደለ ችግሩ በጎንደር እና አካባቢዋ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሀገራችን ክፍልም እንደሚስተዋል ጠቁመዋል። ለዚህም ማሳያ በቅርቡ አንዲት የ12 አመት ህፃን እና የ 31 ዓመት ዲያቆን በጎጃም ከሞጣ ከተማ ዙሪያ በምትገኜው ግንደወይን ወረዳ በኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት ተክሊል ሲጋቡ የሚያሳይ ፎቶ በሶሻል ሚዲያው ሲዘዋወር እንደነበር ማስታወስ ይቻላል።
"በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚፈፀም ያለ እድሜ ጋብቻ ህፃናትን በጎጅ ልማዳዊ ድርጊት አስገድዶ መዳር ላልተጠበቀ የጤንነት ችግር እንደሚዳርግና ልጆች አዘውትረው ወደ ት/ቤት በመሄድ የእውቀት አድማሳቸውን ማስፈት ሲገባቸው በአጉል የእድሜ ክልል ተድረው በእለት ተዕለት የኑሮ ጣጣ ውስጥ ለከፍተኛ የአዕምሮ ጫና አዙሪት ውስጥ እንድትገባ ያደርጋል" ሲሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪ አቶ አወቀ አሰፋ ይናገራሉ። "ያለ እድሜ ጋብቻ የተፈፀመባቸው ህፃናቶች በወሊድ ምክንያት ፌስቱላ፣ ሞት እና ተያያዥ ችግሮች እያጋጠማቸው ይገኛሉ" የሚሉት አቶ አወቀ ይህ አይነት ድርጊት በአብዛኛው የሚፈፀመው በገጠሩ የሃገራችን ክፍል ሲሆን ከፈቃደኝነት ውጭ የሆነውን ያለ እድሜ ጋብቻ እየሸሹ ከተማ ገብተው የሚንከራተቱ ብዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
"ከረሜላ ወይም ብስኩት እየገዛ ሊያባብላት የሚገባትን ህፃን በቤተክርስቲያንም ይሁን በመስጅድ የጋብቻ ስርዓት ተከልሎ ማግባት ከግድያ የማይተናነስ ወንጀል ነው" የሚሉት አቶ አወቀ ይህ አይነት ልማዳዊ ድርጊት በማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በሀገርም ላይ የኢኮኖሚ ውድቀት ማስከተል የሚችል አጉልና ኋላ ቀር ልማዳዊ ድርጊት ስለሆነ ሊወገዝ እንደሚገባም ያምናሉ።
ከአርሶ አደር ልጆች እስከ ቤተ ክህነት ሰዎች የሚፈጽሙት ይህ ያለ እድሜ ጋብቻ ከማህበረሰቡ በዘለለ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያሉ ትልልቅ የእምነት ተቋማትስ ለችግሩን ምን ያህል ትረት ሰጥተውታል የሚለውን ለማወቅ አዲስ ዘይቤ በጎንደር ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ቤተክርስቲያኖች መካከል በአባጃሌ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የሚያገለግሉትን መምህር ገብረስላሴን አነጋግራለች።
"በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የጋብቻ ስርዓት የቤተ ክህነት ሰዎች ጋብቻቸውን የሚፈጽሙት ክብረ ንፅህናዋን ከጠበቀች ሴት ጋር ነው። ስለሆነም ክብረ ንፅህና ያላት ሴት እድሜዋ ከ18 ዓመት በታች የሆነች ነች ተብሎ ይታመናል። ከ18 ዓመት በላይ ያሉ አብዛኛዎቹ ሴቶች ምንም እንኳ ክብረ ንፅህና ቢኖራቸው ከወንዶች ጋር መላፋት ወይም መሳሳም ተከስቶ ሊሆን ስለሚችል ለዲያቆን ሚስት ለመሆን አትችልም" ይላሉ።
ዲያቆኑ በቤተክርስቲያን ስርዓተ ትምህርት ጊዜውን ስለሚያሳልፍ እድሜው ከሚያገባት ሴት መብለጡ የማይቀር ቢሆንም ከምንም አይነት ግንኙነት ተጠብቆ የሚቆይ ነው። ስለሆነም ዲያቆኑ ህፃኗን ሲያገባት ለአቅመ ሄዋን መድረስ አለመድረሷን የሚረዳና ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ ብቻ ግንኙነት የሚያደርግ እንደሆነ ከመምህር ገብረስላሴ አገላለጽ ለመረዳት ይቻላል።
ጥር እና የካቲት ወር በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ የሰርግ ወራት ናቸው በመሆኑም በርካታ ያለእድሜ ጋብቻ ይፈፀማሉ። ከእነዚህ መካከል በአንድ ሳምንት ውስጥ የማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳ ፍትህ ፅ/ቤት ያለ እድሜ ጋብቻ ሊፈፀምባቸው የነበሩ 18 ህፃናቶችን ማዳን ተችሏል። የማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳ ፍትህ ፅ/ቤት ከወረዳው ፖሊስ ፅ/ቤት እና ከሴቶችና ህፃናት ፅህፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን ያለ እድሜ ጋብቻ ሊፈፀምባቸው የነበሩ እድሚያቸው ከ11 እስከ 16 ዓመት የሆኑ እና የትምህርት ደረጃቸው 4ኛ እስከ 10ኛ ክፍል የነበሩን ህፃናቶችን ማዳን መቻሉን ለአዲስ ዘይቤ በላከው መግለጫ ያመላክታል።
ያለ እድሜ ጋብቻ ሊካሄድባቸው የነበሩ ቦታዎች ፉጨና ፣ ማይነጋድ ፣ ጭርቅኝ ፣ ሳንኪ ፣ ከንፈር ማሪያም፣ ማሰሮ፣ፈልፈል እና ጃንሱማ የሚባሉ ቀበሌዎች ላይ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ህፃናቶቹ በጊዚያዊነት በተዘጋጀ የህፃናት ማቆያ ቦታ እንዲቆዩ መደረጋቸውንም ነግረውናል።