ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በግብዓት እጥረት ምክንያት ስራ ሊያቆም እንደሆነ የአዲስ ዘይቤ ምንጮች ገለፁ። ባሳለፍነው ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ዓመታዊ የምርት ስራውን የጀመረው ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ከአራት ወራት ቆይታ በኋላ በሸንኮራ አገዳ እጥረት ሳቢያ ስራ ሊያቆም እንደሆነ ከአካባቢው ምንጮች አረጋግጠናል።
የፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ እርሻ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዋቄ ጢዮ፣ ዶዶታ እና ወለንጪቲ አካባቢዎች እየተካሄደ እንደሆነ ከዚህ ቀደም ተገልፆ የነበረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 16 ሺ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ መሬት እንደሚኖረውም ሲጠበቅ ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚያጋጥም የሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት ምክንያት ወትሮውን እስከ ሰኔ ወር መጀመሪያ ድረስ የሚሰራው ፋብሪካው፣ አሁን ላይ ስራ ለማቆም እንዲሁም ለምርት መቆረረጥ እየተዳረገ ይገኛል። የአዲስ ዘይቤ ምንጮች እንደገለፁት ከቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የስኳር ምርት ግብዓት የሆነው የሸንኮራ አገዳ ቆረጣ ቆሟል።
ፋብሪካው በመጀመሪያ ምዕራፍ በቀን 6 ሺህ 250 ቶን አገዳ እየተጠቀመ በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን 749 ሺህ 46 ኩንታል በላይ ስኳር የማምረት አቅም ነበረው። የማምረት አቅሙን ለማሳደግ እና ዓመታዊ የስኳር ምርቱን እስከ 2 ሚሊዮን 207 ሺህ ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ እንደነበረ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ መረጃ ያመለክታል።
ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ከስኳር ምርቱ በተጨማሪ ሞላሰስ ከተባለው ተረፈ ምርቱ ኤታኖል እንዲያመርት የታቀደለት እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለፋብሪካው እና ለብሔራዊ ቋት የሚያቀርብ ቢሆንም አሁን ላይ ስራ የማቆም ስጋት ተጋርጦበታል።
ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ድረ ገፅ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 496/2014 ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ከተደረጉት አምስት ስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ነው።
የቀድሞ ስኳር ኮርፖሬሽን በደንብ ቁጥር 500/2014 መሰረት በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከተተካ ወዲህ ፋብሪካው በራሱ ቦርድ እየተመራም ይገኛል። አዲስ ዘይቤ ስለጉዳዩ ለማጣራት ወደ ፋብሪካው ህዝብ ግንኙነት የእጅ ስልክ በመደወል ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
ከ72 ዓመታት በፊት በይፋ ስራውን የጀመረው ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ስኳር ፋብሪካ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። የተለያየ ፋብሪካ የነበሩት ወንጂ እና ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች በእርጅና ምክንያት በ2004 እና 2005 ሥራቸውን አቁመው የነበረ ሲሆን በወቅቱ 750 ሺህ ኩንታል ስኳር አማካይ ዓመታዊ ምርታቸው ነበር። ፋብሪካዎቹ በአዲስ መልክ መሰራታቸው ከተገለፀ በኋላ በ2006 ዓ.ም ወደስራ ተመልሷል።