ታህሣሥ 16 ፣ 2014

የአዳማ ጫማ አምራቾች ፈተና

City: Adamaኢኮኖሚንግድ

አዳማ በቤት ውስጥ እና በአነስተኛ መደብሮች የሚሰሩ ጫማዎች በብዛት የሚገኙባት ከተማ ናት።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የአዳማ ጫማ አምራቾች ፈተና

በዓለም አቀፍ ደረጃ በእጅ የሚሰሩ መገልገያዎች የመሸጫ ዋጋ በፋብሪካ ከሚመረቱት በላይ ነው። የዋጋው ውድነት መንስኤ ለምርት የሚወስደውን ጊዜ እና ጉልበት ግምት ውስጥ ያስገባል። የእጅ ሙያተኞችን የሚያበረታታው ዓለም አቀፋዊ አሰራር ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ተቃራኒውን የሚተገብር ይመስላል። ከሐገር ውስጥ ምርቶች ይልቅ የውጭውን፣ በእጅ ከተሰራው ይልቅ የፋብሪካውን የሚመርጡ ሰዎች ቁጥር በርካታ በሚል ከሚገለጸው በላይ ነው። ዋጋውም በፋብሪካ ከሚመረቱት በታች እንደሆነ የግብይት መረጃዎች አመላክተዋል።

ተገኝ ገ/እግዚአብሄር Impacts of Chinese imports and coping strategies of local producers፡ the case of small-scale footwear enterprises in Ethiopia በሚል ርዕስ ባሰናዳው ጥናታዊ ጽሑፍ ከላይ ያነሳነውን ሐሳብ የሚያጠናክር ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ጥናቱ ከተካሄደበት 2007 ዓ.ም. በፊት በነበሩ ዓመታት ከእስያ በተለይም ከቻይና የሚገቡ ርካሽ ዋጋ ያላቸው የፋብሪካ ምርቶች የሐገር ውስጥ ገበያውን በልጠውታል። ከቻይና የሚገቡት ጫማዎች በ‘ዲዛይን’ እና በዋጋ የተሻለ አማራጭ ማቅረባቸው የብልጫው ምክንያት እንደሆነ አስቀምጧል።

አዳማ በቤት ውስጥ እና በአነስተኛ መደብሮች የሚሰሩ ጫማዎች በብዛት የሚገኙባት ከተማ ናት። በእጅ የሚሰሩት የጫማ ምርቶች በከተማዋ የተለመዱ፣ ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ ስለመሆናቸው አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

አብዛኛዎቹ የጫማ መደብሮች አነስተኛ በሚል የሚለገጹ ናቸው። የንግድ እና የማምረቻ ቦታቸው ተመሳሳይ መሆኑ አነስተኛነታቸውን ከሚያሳዩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

በአራዳ የንግድ ማዕከል ውስጥ በግንብ  አክሲዮን ሕንጻዎች ብሎክ B ላይ  የሰብስቤ ሙሉጌታ የጫማ መስሪያ እና መሸጫ ይገኛል። በሴንቴቲክ ቆዳ፣በሸራ እና የጅንስ ጨርቅ የተሰሩ የሴቶች፣ የወንዶች እና የሕጻናት ሸበጥ እና ጫማዎችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የሴቶች ቆዳ፣ ሸራ፣ ፕላስቲክ ቦርሳ ምርቶችን በሙከራ ደረጃ አምርቶ ለደንበኞቹ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።  

የማምረቻ እና መሸጫ መደብሩ ባለቤት ሰብስቤ ሙሉጌታ ይባላል። ሁሉም ምርቶች ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በእጅ እንደሚሰሩ ይናገራል። “በህዝባዊ እና ሐይማኖታዊ በዓላት ወቅት ባዛሮች እና ኤግዚቢሽኖች ስለሚኖሩ ሥራ ይበዛብናል። ትዕዛዝ በሚበዛብን ወቅት አልፎ አልፎ በጊዜው ማድረስ ያቅተናል” ብሎናል። በስሩ አራት ተቀጣሪ ሰራተኞች ያሉት አቶ ሰብስቤ “በሰው ኃይል የሚሰሩትን አንዳንድ ሥራዎች በማሽን የመቀየር ሐሳብ ቢኖርም ዋጋው እስከ 200ሺህ ብር ነው። ይህ በኛ አቅም አይቀመስም” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

አቶ ሰብስቤ የምርቶቹን ተቀባይነት እና ተፈላጊነት በተመለከተ ሲናገር “የፋሽን ኢንዱስትሪው በፍጥነት እያደገ ነው። አሁን አሁን ሰዎች ከልብሳቸው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጫማ ይፈልጋሉ። ለዚህ ዓይነት ደንበኞች ከልብስ ዲዛይነሮች ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል። በቂ ነው ባይባልም እየሞከርነው ነው” ብሏል። በልምድ የተላለፈው ሙያ በትምህርት አለመታገዙ ሌላው ሰብስቤ በችግርነት ያነሳው ጉዳይ ነው። በዚህ ዘርፍ የሚያሰለጥን ተቋም ቢኖር የተሻሉ ባለሞያዎች እንዲኖሩ እንደሚያግዝ ያለውን እምነት ነግሮናል።

"ገና በእግራችን ለመቆም እየታገልን ነው። በግብር አወሳሰን ጉዳይ እንደትልቅ የማምረቻ ፋብሪካ ዓይቶ ጫና ማድረግ ይታያል። ይኼ ቢስተካከል ትርፉ ለሀገር ነው" ሲል ሀሳቡን ይቋጫል።

በሱቁ ውስጥ ተቀጥረው የስራ እድል ካገኙ ወጣቶች አንዷ ኪያ አልሂሃ ናት። በሱቁ ውስጥ ከሚመረቱት ጫማዎች በተጨማሪ በሚመጣላት ትዕዛዝ የተለያዩ አልባሳትን እና የቦርሳ ምርቶችን እንደምትሰራ ትናገራለች።

"በአብዛኛው የሴቶች ቦርሳ እና አልባሳት፣ ለወንዶች ደግሞ የተለያዩ ሸበጦች እሰራለሁ" የምትለው ኪያ አልሂሃ በልብስ ዲዛይን እና ስፌት ስራን በማሰልጠኛ ብትማርም የጫማ እና የቦርሳ ስራን ግን ባላት ፍላጎት በራሷ እንዳዳበረችው ትናገራለች። በማሰልጠኛዎችም ብዙ ትኩረት እንደማይሰጠው ትናግራለች።

ከዚህ ቀደም የነበራትን ሱቅ በግብር ጫና እና በስራ ቦታ ኪራይ ውድነት እንደዘጋችና ከአልጋ ልብስ ጥልፍ ስራ እንደወጣች የምትናገረው ሒሩት አደም በአሁን ወቅት አነስተኛ ሱቅ ከፍታ የተለያዩ በክር የሚሰሩ ጫማዎችን እየሰራች ትገኛለች።

‹‹ሰራውን ከጀመርኩ ሁለት ዓመት ሆኖኛል። የመስሪያ ቦታ እጦት ዛሬም ያልታለፈ ጉዳይ ነው›› የምትለው ሒሩት የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ስራዋን እንዳታሰፉ፣ ገቢዋን እንዳታሳድግ፣ ለሰዎች ተጨማሪ የስራ ዕድል እንዳትፈጥር ማነቆ እንደሆነባት ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች።

"ስራውን የጀመርኩት በካልሲ ስራ ነው። በኋላ ግን ሶል እያደረግኩ ወደ ጫማ መቀየር ጀመርኩ" የምትለው ሒሩት አደም ምርቷን ለገበያ የምታቀርበው በፌስቡክ እና ቴሌግራም  አማካኝነት በከፈተቻቸው ገጾች ነው።

"አንድ ጫማ ዋጋው 350 ብር ነው። ለማቴሪያል የሚወጣው ወጪ እና በእጅ ስለሚሰራ ከሚወስደው ጊዜ አንጻር እና ዋጋው አዋጭ አይደለም" የምትለው ሒሩት የተሻለ ነገን ተስፋ ከማድረግ ባለፈ ራሱን ከመቻል አልፎ በህይወቷ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያለው ገቢ እንደሌለውም ትናገራለች።

ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ የሆነው ስመኝሽ እሸቱ (እፉዬ ገላ) በሕትመት ስራ ተሰማርታ ትገኛለች። የሒሩትን የምታዘጋጃቸውን የህጻናት አልባሳት እና የሴቶች ጫማዎች ላለፉት ሁለት በተደጋጋሚ መጠቀመሟን እና ውጭ ሐገር ለሚኖሩ ወዳጆቿም ገዝታ እንደምትልክ ትናገራለች።

"ጫማዎቹ በጣም ቀላል እና ለአጠቃቀም ምቹ ናቸው። ዋጋቸውም ርካሽ ነው" የምትለው ስመኝ ስራዎቹ የሚገባቸውን ያክል ትኩረት እንዳላገኙም ትናገራለች። 

የሀገር ምርቶችን መጠቀም ልምድ መበረታታት እንዳለበት ታምናለች። "አዲስ ያልተለመደ የክር ጫማዎችን፣ ሪባኖችን መሞካከር ስጀምር በጣም ሰው ወደደው በዚህ ተበራትቼ ቀጠልኩበት" የምትለው ሰላም አበራ በልብስ ዲዛይን በአጭር ኮርስ መመረቋን ትናገራለች።

ከአዳማ እና አዲስ አበባ የመስሪያ ጥሬ እቃዎች እንደምትገዛ የምትናገረው ሰላም አበራ በመኖሪያ ቤቷ ሰርታ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ በከፈተችው አገርኛ ጫማ የቴሌግራም ገጽ እንደምትሸጥ ለአዲስ ዘይቤ ገልጻለች።

"ሕብረተሰቡ እንደኛ ዓይነት ምርቶች ያለው አመለካከት እጅግ የወረደ ነው። ተጠቅሞበት ጥንካሬውን እና ምቾትን ዕስኪያየው ማሳመኑ ከባድ ነው" የምትለው ሰላም ለወንዶች፣ ለሴቶች፣ ለህጻናት የሚሆኑ የተለያየ ክፍት እና ሽፍን ጫማዎቿ ሽያጭ በእነኚህ ሁሉ ትግሎች ውስጥ ለለውጥ ባይሆን ለእለት ገቢ የሚሆን ገቢ እንደማታጣ ትናገራለች።

“ኑር የገበያ የገበያ አዳራሽ” ውስጥ በወንዶች አልባሳት እና ጫማዎች ሽያጭ ስራ ላይ የተሰማራው ብርሃኑ ገ/መድህን ሪፖርተራችን አነጋግሮት ነበር። ሁለት ዓይነት ክፍት የወንድ ጫማዎች ከአዲስ አበባ አመጣለሁኝ። የቆዳው የሚሰራው ሀገር ውስጥ ነው የሸራው ከቻይና የሚገባ ነው ሲል ለአዲስ ዘይቤ ይናገራል።

"ከዚህ ቀደም እነኚህን ጫማዎች እንድሞክር መጥተውልኝ ነበር። ነገር ግን ከሌሎቹ ሸበጦች አንጻር ተቀባይነታቸው ብዙም ባለመሆኑ ብዙ ቆይተው ነው የተሸጡት" ሲል ይናገራል። እንደምክንያት የሚያቀርበው ጥራት እና ውበታቸው  ከዋጋ ተቀራራቢ ምርቶች አንጻር ዝቅ ስለሚል ነው ይላል።

ዳግም መንግሥቱ በኤሚ ሕንጻ ላይ የሴቶች ልብስ መሸጫ ሱቅ አላት። በሱቋ የተገኘው ሪፖርተራችን ምንም በእጅ በቤት ውስጥ የተሰሩ ጫማዎች አልተመለከተም። በአዳማ በእጅ እየተሰሩ ያሉ የሴት ጫማዎችን ትይዝ እንደሆን ለጠየቃት ጥያቄ "ተቀባይነቱ ገና ነው። የሚጠይቅ ሰው ስለሌለ አልይዘውም" የሚል መልስ ሰጥታለች። በቴሌግራምን በመጠቀም ፎቶዎቹ ሲዘዋወሩ ማየቷን እንደምታስታውስ ነግራናለች። 

 ፍጹም ተስፋዬ በአንድ ዓለም አቀፉ የንግድ ተቋም ዩኒሊቨር  ውስጥ በኢኮኖሚ ባለሙያነት ያገለግላል። ስለሀገር ውስጥ አነስተኛ አምራቾች ሲናገር፡- “የፋይናንስ እጥረት፣ ለብድር በ‘ኮላተራል’ የሚጠየቁ ማስያዣዎች፣ የወለድ መጠኑ መብዛት ዋነኛ ችግሮች ናቸው” ይላል፡፡ እነኚህን አነስተኛ ግለሰቦች እና ቡድኖች ለማገዝ የሀገሪቱን ባንኮች የሚያስገድድ ድንጋጌ ሊኖር ይገባል ይላል።

 "የሀገራችን ባንኮች ከዓመታዊ ትርፋቸው 1% አነስተኛ ተቋማትን ለመደገፍ ያለማስያዣ እንዲያበድሩ በብሔራዊ ባንክ አስገዳጅ ሕግ ቢወጣ፣ አነስተኛ ንግዶች ይህን ለመጠቀም እንደ ንግድ ፍቃድ፣ የሒሳብ መዝገብ፣ የአዋጭነት ጥናት እና መሰል ሕጋዊ ሰነዶችን አዘጋጅተው በጋራ ቢሰሩ መልካም ነው" የሚል የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቧል።