ናፍቆት ታደለ ይባላል። ማየት የተሳነው ነው። የባህርዳር ከተማ የእግረኛ መንገዶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸውን ሲያስረዳ “በእግረኛ መንገድ ላይ ከመሄድ ዋናውን አስፋልት ይዞ መሄድ ይሻላል” ይላል። አካል ጉዳተኞችን ከሚያጋጥሙ መሰናክሎች መካከል አካባቢያዊ መሰናክል አንዱና ዋነኛው ስለመሆኑ አንስቷል። የሕንፃዎች፣ የመንገዶች፣ የመገናኛ ዘዴዎች፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትና ሌሎች ምቹ አለመሆናቸው አካል ጉዳተኞችን ሕይወት አክብዶታል።
“አብረውኝ የሚማሩ ማየት የሚችሉ ልጆች ባይረዱኝ ለተጨማሪ ጉዳት ልዳረግ እችል ነበር” የሚለው ተማሪ ናፍቆት የቅርብ ጊዜዎቹ ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶች ማየት የተሳናቸውን እንዲያግዙ ቢጠበቅም በደንብ እንዳልታሰበባቸው ያብራራል። “የእግረኛ መንገዱ የተለየ ቅርጽ ያለው ሸክላ አንድ መስመር ይዞ ተነጥፎባቸዋል። ይህ የተደረገው ዓይነ ስውራን ያንን ተከትለው መጓዝ እንዲችሉ ነው። ነገር ግን መስመሩን ተከትለን ስንሄድ ከመብራት ፖል ወይም ከዛፍ ወይም ከሌላ ነገር ያጋጨናል” ብሎናል።ሌላው ገጠመኙን ያጋራን አቶ ይመኑ ዘሪሁን የመግሥት ሰራተኛ ነው። ዊልቸር የሚጠቀም አካል ጉዳተኛ ነው። በባህርዳር ከተማ ለረዥም ዓመታት መኖሩን ይናገራል። "እጀግ ጥቂት የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ዊልቸር ለሚጠቀሙ አካል ጉዳተኞች መወጣጫ (ትራፕ) አላቸው። ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ ግን አላጋጠመኝም” ብለውናል።
በአንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ታችኛው የሕንጻው ክፍል ወርደው አካል ጉዳተኞችን የሚያስተናግዱ ሰራተኞች ቢኖሩም አብዛኛውን ጊዜ በተወካይ እና በሰው ሸክም ጉዳያቸውን እንደሚያስፈጽሙ ነግረውናል።
የከተማዋ የእግረኛ መንገድ ዊልቸር ለሚጠቀም አካል ጉዳተኛ ምቹ አደሉም የሚለውን ሐሳብ ሌሎች አካል ጉዳተኞችም ይጋሩታል። አቶ ፍሬሰላም ዘገየ የአማራ ክልል አካል ጉዳኞች ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ናቸው። "የከተማዋ የእግረኛ መንገዶች ተቆፍረው ያልተዘጉ ጉድጓዶች ያሏቸው። ከፍት የተተዉት ጉድጓዶች አካል ጉዳተኞችን ለተጨማሪ ጉዳት እየዳረጉ ነው"
እንደ አቶ ፍሬሰላም ገለፃ "በከተማዋ የንግድ አገልግሎት የሚሰጡ ምግብ አና መጠጥ ቤቶች የእግረኛ መንገዱን ላይ ወንበር ዘርግተው አግልግሎት ይሰጣሉ። ይህ ለሁሉም ዓይነት አካል ጉዳተኞች ፈተና ሆኗል። በግንባታ ላይ የሚገኙ አንዳንድ የከተማዋ ሕንፃዎች እግረኛ መንገድ ላይ የግንባታ ግብአቶችን በማስቀመጥ ወይም የእግረኛ መንገዱን በማጠር አካል ጉዳተኞችን እየፈተኑ ይገኛሉ”
እንደ አቶ ፍሬ ሰላም ማብራሪያ የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የትራፊክ መብራቶች አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይገባል። ለዚህ መሳያ የሚሆነው ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች ሰከንድ በሚቆጥሩበት ጊዜ ማየት ለተሰናቸው ወገኖች ታሳቢ በማድረግ ሊረዷቸው የሚችሉ ድምፆች አላቸው። ይህ ድምፅ መብራት ካለበት ቦታ መድረሳቸውን እንዲረዱ ከማድረግ በተጨማሪ የትኛው መንገድ ክፍት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ያደርጋል። ነገር ግን ባህርዳር ከተማ የሚገኙ የትራፊክ መብራቶች የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ያካተቱ አይደሉም ወይም ምቹ አይደሉም።
የችግሩን መሰረታዊ ምክንያት የሚሰሩ መንገዶችንና ሕንፃዎችን አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እንዲያደርጉ የወጣ አዋጅ ተግባራዊ መሆን አለመቻሉ ነው። በተጨማሪ የሚመለከተው አካል ቢኖርም በቂ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንዳላደረገ የአካል ጉዳተኞች ማኅበሩ ፕሬዝዳንት ያብራራሉ።
አቶ ዘመኑ ፀጋው በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መመሪያ የማኅበራዊ ደህንነት ቡደን መሪ ናቸው። ችግሩ ለመቅረፍ ሁለት ዓይነት ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
“አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የሚሰሩ ህንፃዎችና መንገዶች አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ እንዲሆኑ መመሪያዎች መተግበር አለባቸው። ሀገር አቀፍ የህንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 እና ሁሉም ተቋማት የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በመደበኛ ተግባሩ አካቶ እንዲፈፅም የወጣውን መመሪያ ቁጥር 41/2012 ተግባራዊ ለማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ፈጠራ ስራ በታቀደ መልኩ እየተሰራ ነው” ሲሉ ለአደስ ዘይቤ ተናግረዋል። ውሱን በጀት ቢኖራቸውም የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ሰምተናል።