በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የውጭ ሐገራትን ምግቦች በቋሚነት የሚያቀርቡ ሬስቶራንቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። በጣም ከተለመዱት ‘በርገር’፣ ‘ፒዛ’፣ ‘አይስክሬም’፣ ‘ኬክ’ ቤቶች በተጨማሪ እንደ ‘ኑድልስ’፣ ‘ሱሺ’ን የመሳሰሉ የካሪቢያን፣ የሜዲትራንያን፣ የአረብ፣ የቻይና፣ የቱርክ፣ የጣሊያን ምግቦችን ብቻ በልዩነት የሚያዘጋጁ ምግብ ቤቶች በርክተዋል።
በአዳማ ከተማም እንዲሁ ለውጭ ሐገር ምግቦች ብቻ ትኩረት የሰጡ ሬስቶራንቶች ይገኛሉ። በርካታ ተጠቃሚ ካላቸው የውጭ ሐገራት ምግቦች መካከል “መንዲ” ይጠቀሳል። አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የበሰሉ ምግቦችን በማድረስ ሥራ የተሰማሩ ተቋማትም ይህንን አረጋግጠዋል። የ“ዴሊቨር አዳማ” ባለቤት እስራኤል የኔሰው እና “የአዳማ ገበታ” መስራች ናትናኤል ምትኩ እንዳሉት “መንዲ” በየዕለቱ ተደጋግመው በደንበኞች ከሚታዘዙ የምግብ ዐይነቶች አንዱ ነው።
ኢዘዲን አብደላ የ“መንዲ” ሬስቶራንቶችን እንደሚያዘወትር ይናገራል። “አርብ ከጁምዓ ሰላት በኋላ እና እሁድ ከሰዓት በኋላ ወደ መንዲ ሬስቶራንቶች ጎራ እላለሁ” የሚለው ኢዘዲን ከጓደኞቹ ጋር ሰብሰብ ብለው ሲመገቡ “ሸዝኒ” (ዳጣ) በዛ ያለበት “መንዲ” ያዘወትራሉ። “ሬስቶራንቶች የራሳቸው አቀራረብ አላቸው። ተጠቃሚውም እንደ ፍላጎቱ እንዲበዛ እና እንዲያንስ የሚፈልገውን፣ እንዲኖር እና እንዳይኖር የሚፈልገውን ጠቅሶ ማዘዝ ይችላል”
የሒልዋ ሬስቶራንት ባለቤት ሼፍ አብድልቃድር ምትኩ “መንዲ የአረቢያን ምግብ ነው” ብለውናል። “በስቲም የሚበስል ስጋና ሩዝ ዋነኛ የምግቡ ግብአቶች ናቸው። ቂጣ እና ‘ቺዝኒ’ እንደ ማባያ ጥቅም ላይ ይውላሉ” ያሉ ሲሆን አበሳሰሉን በተመለከተ ሲናገሩ “ከጉድጓድ ውስጥ በሚወጣ እንፋሎት አልያም በመረቅ ሊበስል ይችላል” ብለዋል።
ሒልዋ መንዲ ሬስቶራንት
ሒልዋ መንዲ ሬስቶራንት በመሃል አዳማ ፖስታ ቤት አካባቢ ይገኛል። አሰላ መውጫ በሚወስደው መንገድ ምስራቅ ሸዋ ፖሊስ አካባቢ አምስት ዓመት አካባቢ ቆይቷል። በስቲም፣ በበሰለ ስጋ፣ በአሳ፣ በስጋ ወጥ፣ በስጋ ጥብስ፣ ሩዝ አና በቂጣ ይቀርባል። መጠኑም እንደ ተጠቃሚው ፍላጎት ሙሉ እና ግማሽ ሊሆን ይችላል።
ሼፍ አብዱልቃድር እንደሚናገሩት በስቲም በስሎ የሚጠበስ ስጋ የያዘ የመንዲ አሰራርም አለ። ሬስቶራንቱ “ከመንዲ” በተጨማሪ በሌሎች ሬስቶራንቶች የሚቀርቡ ባህላዊ እና ዘመናዊ ምግቦች ያቀርባሉ። በክረምት ወቅቶች የተሻለ ተፈላጊነት እና የተጠቃሚ ቁጥር እንዳለ የሚናገረው ሼፍ አብድልቃድር በጾም ወቅትም የተሻለ ተፈላጊነት አለው ብለውናል።
አፍናን ሬስቶራንት
አፍናን ሬስቶራንት ሀኒ ኬክ ጀርባ ይገኛል። በአዳማ ድሬዳዋ መንገድ እንደመገኘቱ አዳማን አልፈው በሚሄዱ መንገደኞች ይዘወተራል። የሬስቶራንቱ ስራ አስኪያጅ ዑስማን ጣሂር የቤቱ ተወዳጅ ምግብ መንዲ ቢሆንም ሌሎች ምግቦችም ያቀርባል። "በዋናነት ስጋ እና ሩዝ ነው። ከእነዚህ ሌላ የተለያዩ ማባያዎች ይጨመሩለታል። በአፍናን ሬስቶራንት የሚሰራው መንዲ ዓሳ፣ ዶሮ፣ የተለያዩ ማባያ ሶስ፣ አትክልት እንዲሁም ቂጣ አለው። እንደተጠቃሚ ፍላጎትም ሙሉ እና ግማሽ ሆኖ ይቀርባል” ብሎናል።
ነጅማ ሬስቶራንት
የነጅማ ሬስቶራንት ባለቤት አህመድ ዑስማን ሬስቶራንቱ በአሁን ወቅት የተለያዩ ስጋ ነክ ምግቦችን እና ጁሶችን ለደንበኞቹ እያቀረበ እንደሆነ ነግሮናል። በከተማዋ ሃኒ ኬክ ጀርባ ወደ ሙገር መንገድ አካባቢ ይገኛል። ነጅማ ሬስቶራንት ከሚያዘጋጃቸው ምግቦች አንዱ እና ተወዳጁ “መንዲ” ነው። "መንዲ ከሌላው የምግብ አበሳሰል ልዩ የሚያደርገው በእንፋሎት መብሰሉ ነው። እኛም በእንፋሎት አብስለን ነው ምንሰራው። ከስጋው ጋር ሩዝ በተጨማሪ ደቃ (በደቀቀ ስጋ የሚዘጋጅ ‘ሶስ’)፣ የተለያዩ ወጦች ጥብስ እና ቂጣ ይኖረዋል” ብሎናል።
በአሁን ሰዓት በእድሳት ላይ የሚገኘው ሬስቶራንቱ ሲጠናቀቅ መንዲን ከአሰራር እስከ አቀራረብ እና ዓይነቶች በተሻለ ለማድረግ ማሰቡንም ለአዲስ ዘይቤ ሰምታለች።
የውጭ ሐገር ምግቦችን በማቅረብ ላይ የተሰማሩት ተቋማት የባለሙያ እጥረት እንዳለባቸው ይናገራሉ። በከተማዋ አንድ የግል እና አንድ የመንግሥት ማሰልጠኛ ት/ቤቶች ቢኖሩም የሰልጣኞቹ ቁጥር ገበያው የሚፈልገውን ያህል እንዳልሆነ ያምናሉ።