ታህሣሥ 14 ፣ 2014

ከ7 ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠሩት የድሬዳዋ የድንጋይ ላይ ስእሎች

City: Dire Dawaባህል ታሪክ

ድሬዳዋ የቅድመ-ታሪክ ባለቤት መሆኗን ከሚመሰክሩ ቅርሶቿ መካከል የለገኦዳ፣ የፓርክ ኤፒክ፣ የጎደ አጃዋ፣ የዋሻ ስዕሎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ከ7 ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠሩት የድሬዳዋ የድንጋይ ላይ ስእሎች

ድሬዳዋ ከተማ በ1902 (እ.አ.አ) በዘመናዊ ከተማነት እንደተቆረቆረች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ ከተማዋ እንደ ከተማ ከመቆርቆሯ አስቀድሞ የጥንት ዘመን ሰዎች ባልተደራጀ ሁኔታ እንደኖሩባት አንዳንድ የአርኪዮሎጂ ማስረጃዎች ያሳያሉ። በከተማዋ በሰው ልጆች ታሪክ መካከለኛው የድንጋይ ዘመን (Middle Stone Age) በመባል በሚታወቀው ጊዜ የዘመኑ ሰዎች በዋሻ ውስጥ እንደኖሩ የሚመሰክሩ ቁሳቁሶች ተገኝተዋል። የእጅ መሳሪያቹ እና የድንጋይ ላይ ስእሎቹ ብዙ ያልተነገረላቸውና የማይታወቁ የከተማዋ ቅርሶች ናቸው።

ድሬዳዋ የቅድመ-ታሪክ ባለቤት መሆኗን ከሚመሰክሩ ቅርሶቿ መካከል የለገኦዳ፣ የፓርክ ኤፒክ፣ የጎደ አጃዋ፣ የዋሻ ስዕሎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

አንደኛው እና እድሜ ጠገቡ የለገ ኦዳ ዋሻ በተፈጥሮ ከተነባበሩ አለቶች የተፈጠረ ዋሻና በአለታማው ድንጋይ ላይ በተለያየ ቀለማት የተሳሉ ከ600 በላይ የቤትና የዱር እንስሳትንና የሰዎች ምስል ይገኙበታል። የዋሻ ውስጥ የአለት ስዕሎቹ ከ7ሺህ ዓመት በፊት እንደተሳሉ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

ሁለተኛው የፖርክ ኤፒክ ዋሻ ነው። ከድሬዳዋ ከተማ በስተ ደቡብ በ2 ኪ.ሜ. ርቀት በተራራ ላይ ይገኛል። የቅድመ-ታሪክ ቅርሱ ከታወቀበት በ1929 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ በተካሄዱ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮዎች በርካታ የመካከለኛው የድንጋይ ዘመን ጥቅም ላይ የዋሉ የድንጋይ መሳሪያዎችና የእንስሳት ቅሪት አካላት ተገኝተዋል።

ዋሻው በተለያዩ ቀለማት የተሳሉ ስዕሎች ይገኙበታል። ስእሎቹ ከ5ሺህ ዓመት በፊት እንደተሳሉ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ሦስተኛው የጎደ አጀዋ ዋሻ በ2050 ሜትር ከፍታ በተራራ ላይ ይገኛል። ይህ ዋሻ ለምለም በሆኑ እጽዋት የተከበበ ሲሆን ከ5ሺ ዓመታት በፊት በአለታማው ድንጋይ ላይ የተሳሉ በርካታ ስዕሎች በውስጡ ይገኛሉ። በዚህ ዋሻ ውስጥ የሚገኙ ስእሎችን ከሌሎቹ የሚለያቸው በነጭ፣ በቀይ እና በቡኒ ቀለማት መሳላቸውና አካባቢው በአረንጓዴ ተክል በተከበበ መሆኑ ነው።

በድሬደዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ማሳወቅና ጥበቃ ክፍል ኃላፊ አቶ ገበየሁ ወጋየሁ “የዋሻ ስዕሎቻችን ሁለት ዓይነት ናቸው” ይላሉ። ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ የቅብ /Paintings/ እና የጭረት /curving/ ባህሪ ያላቸው እንደሆኑ ነግረውናል። “ኢትዮጵያ በብዛት የሚታዩት የቅብ ሰራዎች ናቸው” የሚሉት አቶ ገበየሁ “በድሬዳዋ አስተዳደር ከቅድመ-ታሪክ ዘመን ቅርሶች ውስጥ የለገኦዳ፣ ፓርክኤፒከና ጎዳ አጃዋ የተፈጥሮ ዋሻዎችና በዋሻዎቹ ጣሪያና ግርግዳ ላይ የተሳሉ ጥንታዊ ስዕሎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የዋሻ  ስዕሎቹ ድሬዳዋ ላይ መገኘታቸው በመካከለኛው የድንጋይ ዘመን ጥንታዊው ሰው በድሬዳዋ  ይኖር እንደነበር ህያው ምስክሮች ናቸው። የዋሻ ስዕሎቹ እድሜ ከ5ሺህ – 7ሺህ ዓመት የሚገመት ይገመታል። ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙትና ወይም መኖራቸው የታወቀው እ.አ.አ በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ በፈረንሳይና አሜሪካን ተመራማሪዎች እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዋሻዎቹና ስዕሎቹ ከአገራችን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎች በግብዓትነት ጠቀሜታ እንዳላቸው ይታመናል። በዋሻዎቹ በተለያዩ ቀለማት ከተሳሉ ስዕሎች  ውስጥ የሰው ምስል፣ ከቤት እንሰሳት ላም፣ በሬ፣ ፍየል፣ ግመል፣ ሲሆኑ አሁን በካባቢው ከማይታዩ የዱር እንሰሳት ዝሆን፣ አንበሳ፣ ቀበሮ፣ ጎሽ ዋና ዋናዎቹ ናቸው” ብለዋል።  

አቶ ገበየሁ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ጥናቶች እንደተካሄዱ ተናግረዋል። በዋሻዎቹ ላይ በተካሄዱ የጥናትና የቁፋሮ ስራዎች ከድንጋይ፣ ከእንጨት፣ ከአጥንትና ከቀንድ የተሰሩ የተለያዩ የእጅ መሳሪያዎችና መገልገያዎች እንደተገኙ መረዳት ተችሏል።

የመካከለኛው የድንጋይ ዘመን ተብሎ በሚታወቀው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ6000 – 1000 ዓ.ዓ. የኖረው ጥንታዊ ሰው በስልጣኔ ከፍተኛ እምርታና እድገት ያሳየበትና ያሰመዘገበበት የታሪክ ጊዜ ተደርጎ ይወሰዳል። ስለሆነም በአስተዳደሩ የሚገኙ የዋሻ ውስጥ የድንጋይ ስዕሎች የቅድመ ታሪክ ዘመን ቅርስ እንዲሆኑ ካስቻሏቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ የሰው ልጅ አካባቢውንና ተፈጥሮን መገንዘብ ሲጀምር የነበረውን ዕወቀት ስለሚያሳዩ፣ ጥበብ /Art/ የተጀመረው በድንጋይ ላይ መሆኑን፣ ለስዕሎቹ ቀለማትን የመቀመም ክህሎቱንና የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የሚያሳዩ፣ የቤት እንሰሳትን በማላመድ ሀብት ማፍራት መጀመሩን፣ ለምግብነት አደን መጀመሩን፣ ራሱን ከዱር እንሰሳት ጥቃት ለመከላከልና ለአደን የሚጠቀምባቸውን የጦር መሳሪያዎች ማምረት መጀመሩን፣ በታሪክ ዘመን ፊደላትን ቀርጾ ታሪክንና ባህሉን በጽሑፍ ለተተኪው ትውልድ ለማቆየትና ለማስተላለፍ ከመጀመሩ በፊት ስዕሎችን መጠቀሙን፣ ወ.ዘ.ተ በግልፅ የሚያስረዱና የሚመሰከሩ በመሆናቸው እንደሆነ ከኃላፊው ማብራሪያ ተረድተናል።

ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ነጋ አበራ በበኩላቸው “እንደምንገኝበት ዘመን ቃላት ላይ መራቀቅ ሳንጀምርና ፊደላት ሳይቀረፁ የሰው ልጆች ታሪክን ለቀጣዩ ተውልድ ለማስተላለፍና መረጃን ለመለዋወጥ ስእሎች ጥቅም ላይ እንደዋሉ ይታወቃል። ለምሳሌ መረጃን ለመለዋወጥ አንድ ዋሻ ውስጥ ጥቂት ጊዜያት ያሳለፉ ሰዎች ዋሻውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱ በዋሻው ቆይታቸው የገጠማቸውን በስዕል ያሰፍራሉ። ዋሻ ውስጥ እባብ የሚገኝ ከሆነ ቀጥሎ የሚመጣው ሰው የእባቡን ስዕል ተመልክቶ ይጠነቀቃል” ያሉ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የዋሻ ውስጥ ስዕሎች ታሪክን ለትውልድ ለማሻገር እያገለገሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል። “ለምሳሌ በዚያ ዋሻ ውስጥ እረኞች ይኖሩ ከነበረ የራቸውን ስዕል ከሳሉ ቀጥሎ የሚመጡት ሰዎች በዛ አካባቢ መተዳደሪያቸው ምን እንደነበር ለመረዳት ይችላል”

ዶ/ር ነጋ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ዋሻዎቹ ሲያብራሩ “የዋሻ ውስጥ ስዕሎቹ የሰው ልጅ ዛሬ የደረሰበት እጅግ ዘመናዊ አኗኗርና አደረጃጀት ላይ ከመድረሱ በፊት በርካታ ግን ፈታኝ የሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግሮችን ደረጃ በደረጃ ማለፉን የሚያሳዩ የድንቅ ጥበብና ፈጠራ ትሩፋቶች ናቸው ማለት ይቻላል። በእነዚህ ጥንታዊ ዋሻዎች ይኖሩ የነበሩ ማኅበረሰቦች ስልጡን ህዝቦች ነበሩ” የሚሉት ዶ/ር ነጋ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ “ሰዎቹ ሀሳባቸውን በንግግር ከመግለፅ አልፈው፣ ምንም ዓይነት የጽሕፈት ወይም የስዕል መሳሪያ ባልነበረበት በዚያን ወቅት ሐሳባቸውን በስዕል ማስቀመጥ መቻላቸው ስልጡን እንዳስባላቸው ነገረውናል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ማስተዋወቅና ጥበቃ ክፍል ኃላፊ አቶ ገበየሁ ወጋየሁ ቅርሶቹን ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ቢሯቸው እየሰራ ያለውን ነግረውናል። “በአስተዳደሩ የሚገኙ የዋሻ ስዕሎች እየደረሰባቸው ካለው አደጋ ለመታደግ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል ለአካባቢው ሕብረተሰብ ሰለቅርሶቹ ምንነት፣ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ቀዳሚው ሥራችን ነበር። ቅርሱ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ጉዳት ሊያደርሱበት ከሚችል የሰዎች ንኪኪ ለመከላከል ዙሪያቸውን ታጥሯል። ዋሻዎቹ ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ የእግር መንገድ ተዘጋጅቶላቸዋል። በዋሻዎቹ አቅራቢያ ቱሪስቱ በጊዜያዊነት የሚያርፍበትና የሚቆይበት ባህላዊ ቤት የመገንባት ሥራ፣ የአካባቢ ወጣቶችንና ሴቶችን በማደረጃት የዕደ-ጥበብ ምርቶችን ማምረት የሚያሰችላቸው የክህሎት ስልጠና፣ የዋሻ ስዕሎችን ከፌደራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በቅርስ የማስመዝገብ ሥራ ተሰርተዋል። ከማስተዋወቅ አንፃር ስዕሎቹን በተለያዩ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች እንዲሁም በአስተዳደርና በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ንግድ ትርዒቶች፣ ባዛሮችና ኤግዝቢሽኖች በተደጋጋሚ የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል። ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ሰዓት በዋሻ ስዕሎቹ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱ የሐገር ውስጥ እና የውጭ ተመራማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። የጎብኚዎች ቁጥርም እያደገ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ከሚያደርገው የጥበቃና እንክብካቤ በተጨማሪ የአካባቢው ሕብረተሰብ የበኩሉን አስተዋፆኦ ሊያበረክት ይገባል። ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቅርሶች ለማልማትና ለማሰተዋወቅ እየተደረገ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።