ታህሣሥ 19 ፣ 2014

የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የሚመለከት ውይይት ተካሄደ

City: Bahir Darዜናወቅታዊ ጉዳዮች

የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የምዕራቡን ዓለም የጅኦፖለቲካ ፍላጎት ለማስቀጠል ያለሙ ዘገባዎች በትኩረት አድረገው ማቅረባቸው አሁን በስፋት በሚደረገው የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ማሳያ ነው።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የሚመለከት ውይይት ተካሄደ

የባህርዳር ዮኒቨርሲቲ ከወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሀሰተኛ መረጃ በዲፕሎማሲው ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ የሚገመግም የውይይት መድረክ በርካታ አካላት በተሳተፉበት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጠቅላላ ሁኔታ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ከ1847/8 እስከ 2014 ዓ.ም. ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች የአፍሪካ ገጽታ  በዲፕሎማሲ ላይ ያሳደሩት ጫና የኢትዮጵያ የመረጃ ጦርነት እንደማሳያ እና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በጦርነት ወቅት  ድክመቶች ጥንካሬዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚሉ አራት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በውይይቱም መድረኩ የፌድራልና የክልል የመንገግስት ኮሚኒኬሽን አመራሮች፣ በክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች፣ ምሁራን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች ከተለያዩ ተቋማት የተጋበዙ እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት እና  ከውጭ ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የጠቅላይ ሚንስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዳንኤል ክብረት ሂደቱን ሲያብራሩ "በኢትዮጵያ ላይ እየተጠናከረ የመጣው የሐሰተኛ መረጃ ችግር በአጋጣሚ የተፈጠረ ስህተት ሳይሆን ሆን ተብሎ ታቅዶ የሚሰራ ክስተት ነው። በኢትዮጵያ የሚካሄው የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻ በርካታ ዓለም አቀፍ ተዋናዮች የሚሳተፉበት ድርሰት ነው” ያሉት አማካሪው "የስለላ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት እና ፖለቲከኞች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።" በማለት በድርጊቱ የሚሳተፉትን አካላት ያብራራሉ። የተከፈተብን የሀሰተኛ መረጃው ጦርነት ዓላማ "የርስበርስ ጦርነት አንዲከሰት እና እርስ በርስ ማባላት ነው" ብለዋል አማካሪው።

አቶ ዘሪሁን አበበ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ድንበርና የድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ዲፕሎማት ባቀረቡት ጽሑፍ የቀጠናው ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ የሚወሰነው ከሁለት ጉዳዮች አንፃር  መሆኑን አንስተዋል። ጉዳዮቹ "ቀይ ባህር እና ዓባይ” ናቸው ያሉት ዲፕሎማቱ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ለቀጠናው ዲፕሎማሲ ወሳኝ ስለመሆናቸው ተናግረዋል። "አዳዲስ ቀጣናዊ ውህደት ጅማሮች፣ የልዕለ ኃላያን ፉክክር እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ" የኢትዮጵያ የወቅቱ የዲፕሎማሲ ተግዳሮቶች ስለመሆናቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል። ዲፕሎማቱ አቶ ዘሪሁን አበበ። እነዚህ ትልልቅ ዲፕሎማሳዊ ጉዳዮች አሁን ባለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሉታዊ ተፅኖ እያሳደሩ እንደሚገኙ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ በስፋት ዳሰዋል።

ሌላኛው ጥናት አቅራቢ አደም ጫኔ (ፒ.ኤች.ዲ) የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን በስፋት አንስተዋል። "በምዕራባዊያን ሚዲያ የአፍሪካ ምስል የጠለሸ ነው። ተስፋ የሌላት አህጉር ተደረጋ ነው የምትሳለው። ይህ የአሁን ብቻ ሳይሆን የቆየ ክስተት ነው" ያሉት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኛነትና ኮምዩኒኬሽን መምህርና ተመራማሪው ጽሑፍ ባቀረበበት ወቅት "የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ውጤት ነው" በማለት ጥናታቸውን ያጠናክራሉ።

“የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዓለም አቀፍ ሽፋን ያለው የመረጃ ጦርነት ነው። ሁሉንም ዓይነት የመረጃ ብክለት ዓይነቶች ስራ ላይ ውለዋል” ያሉት ጹሑፍ Disinformation (ሀሰተኛ መረጃ ሆን ብሎ ማሰራጨት) በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል" ብለዋል።

እንደ አደም ጫኔ /ፒ ኤች ዲ/ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የአፍሪካን ምስል ለማጠልሸት በርካታ ቴክኒኮችን ይጠቀማሉ። ከእነዚህም ውስጥ የሚቀርቡ ዘገባዎችን አጋንነው ማቅረብ፣ አነስተኛና ነገሮችን ማጮህ "ለምሳሌ የሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት"፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ሆን ብሎ "ድራማታዝድ" ማድረግ፣ የምዕራቡ ዓለም ትኩረት ሊያደርግባቸው የማይፈልጋቸውን ጉዳዮች ሆን ብሎ ማቃለል (oversimplifications)፣ የግጭት ዘገባን በተደጋጋሚ ማቅረብ፣ የአንድ አካባቢ ድርጊት ሁሉንም የሚወክል አድርጎ ማቅረብ፣ አንድ ቦታ የተከሰተ ድርቅ የአፍሪካ ድርቅ አድርጎ ማቅረብ፣ አንድ ቦታ የተከሰተ ግጭት ሀገር አቀፍ የብሄር ግጭት አድርጎ ማቅረብ፣… በብዛት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች ስለመሆናቸው ከጥናት አቅራቢው ሰምተናል።

በሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ለዓለም የተሳሳተ ምስል ለመፍጠር በርካታ ስልቶችን ተጠቅመዋል። በዚህም የተቀናጀና ተከታታይነት ያለው የመረጃ ማዛባት ስልቶችን የተጠቀሙ ሲሆን የመረጃ ማዛባት ኔትወርኮችን ከመጠቀም በተጨማሪ ጋዜጠኞች፣ ሙሁራን እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በስፋት የተሳተፉበት ነው።

የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የምዕራቡን ዓለም የጅኦፖለቲካ ፍላጎት ለማስቀጠል ያለሙ ዘገባዎች በትኩረት አድረገው ማቅረባቸው አሁን በስፋት በሚደረገው የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ማሳያ ነው።

በውይይት መድረኩ የተሰነዘሩ የመፍትሄ ሀሳቦች

ጥናት አቅራቢው የመፍትሔ ሐሳብ ያሉትን ሲያብራሩ “ለምዕራባውያን ሚዲያዎች ያለን ዕይታ መቀየር ያስፈልጋል። ምክንያቱም እነሱን ሀሳብ ማስቀየር አስቸጋሪ ነው። በተጨማሪም ድርጊቱ ታስቦበት እና ታቅዶ የሚሰራ ነው። በአንፃሩ የምዕራባዊን ሚዲያ አመለካከት ከመቀየር እነሱን ምናይበት መነጽር መቀየር ያስፈልጋል” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪም በተመሳሳይ “የራሳችንን እውነት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ማስገንዘብ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል” የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

የጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን ሙህር አደም ጫኔ /ፒ ኤች ዲ/ በበኩላቸው "መንግስት ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ስርዓት መዘርጋት አለበት። የመንግስት የሚመለከተው አካል የኮሚኒኬሽን የቀውስ ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ሊመራ ይገባል። የዲጅታል ሰራዊቱ በዘመቻ መልክ ብቻ ሳይሆን በተደራጀ መልኩ መተግበር ያስፈልጋል" ያሉት ዶክተር አደም  በረጅም ጊዜ በታቀደ መልኩ በመስራት ከምዕራቡን ዓለም ሚዲያ ውጭ የአፍሪካን ድምፅ ሊያሰማ የሚችል የሚዲያ አመራጭ ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ።

ዲፕሎማቱ አቶ ዘሪሁን አበበ በዲፕሎማሲው መስክ ያጋጠመን ችግር ለመቅረፍ ጥቅምን ማዕከል ያደረግ ግንኙት መፍጠር፣ በሀገር፣ በተቋምና በግለሰብ ደረጃ ወዳጆችን ማፍራት፣ የሙህራን ተሳትፎ ማሳደግ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አመላክተዋል። የአካታች ብሄራዊ የምክክር መድረክን እንደ መልካም አጋጣሚ ከመመልከት በተጨማሪ ሀገራችን በዲፕሎማሲው መስክ ያጋጠሟትን  ተግዳሮቶች ወደ  መልካም አጋጣሚ ለመቀየር መስራት እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው በሀገራችን የተከፈተውን የተቀናጀ የዓለም አቀፍ የውሸት ፕሮፖጋንዳ ለመመከት መስራት ያስፈልጋል። ለዚህም በዕውቀትና በስልት ላይ ሊመሰረት ይገባል። በዚህም የምሁራንን ሚና  ማጠናከር አስፈላጊ ነው። ችግሮን ለመቅረፍ ሲቪክ ማኅበራት፣ አርቲስቶች ሌሎችም  የሕበረተሰብ ክፍሎች በዲፕሎማሲው ስራ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል” ብለዋል አምባሳደሩ።

የውይይት በመድረኩ ተካፋዮች የማኅበረሰብ አንቂው እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ የሀሰተኛ መረጃ የእኛ ብቻ ችግር  ሳይሆን ዓለም አቀፍ ችግር ስለመሆኑ አንስተዋል። ይህን ዓለም አቀፍ ችግር ለመቅረፍ የውስጥ አድነታችን ማጠናከር እና በጋራ መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።

አስተያየት