ታህሣሥ 20 ፣ 2014

የ ‘3D’ ማተሚያ የሰሩት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

City: Hawassaቴክ

ቅርጾችን እና ሞዴሎችን ለማተም የሚያገለግለው ስሪዲ ማተሚያ ማሽን (3D Printer) በቅርብ ዓመታት ለዓለም የተዋወቀ አዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የ ‘3D’ ማተሚያ የሰሩት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሐገር ውስጥ ማምረት በርካታ ጥቅሞች አሉት። ምርቱን ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማዳን በተጨማሪ ለሌሎች አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች እንደሚያነሳሳ የባለሙያዎች እምነት ነው። ቅርጾችን እና ሞዴሎችን ለማተም የሚያገለግለው ስሪዲ ማተሚያ ማሽን (3D Printer) በቅርብ ዓመታት ለዓለም የተዋወቀ አዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው። የፕላስቲክ ክር (ABS /PlA ፕላስቲክ)ን የሚጠቀመውን ማሽን የሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተማሪዎቹ ለመጀመርያ ዲግሪ የመመረቂያ ሥራቸው አድርገውታል። በወረቀት የሰፈረውን ውጥናቸውንም ማሽኑን በመገንባት በስኬት አጠናቀዋል። ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ባለሙያ ተማሪዎቹን ለማበረታትት ካፕስቶን የተባለ ፕሮጀክት ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም ታውቋል።

 “ካፕስቶን” የሚል መጠሪያ ያለው ፕሮጀክት የፈጠራ ሥራ ያላቸውን ተማሪዎች ለመደገፍ የተቋቋመ ነው። የፈጠራ ሥራውን ከሌሎች የፈጠራ ሥራዎች ጋር በማነጻጸር አስፈላጊነቱን እና አዋጭነቱን የሚያጠናው “ካፕስቶን” ለፈጠራ ባለሙያዎቹ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል።

 መምህር ሳምራዊት ፈጠነ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት የማተሚያ ማሽኑ ገንቢዎች መካከል አንዷ ነች። በሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግ እና የኮሙፒዮተር ምህንድስና ት/ክፍል መምህር ነች። የስሪ ዲ ማተሚያ ለመመረቂያ ጽሑፍ ሟሟያ እንዲሆን ከሁለት ጓደኞቿ ጋር በመሆን ፕሮፖዛል ቀርፀው የፈጠራ ስራውን እንደጀመሩ ነግራናለች። “በመጀመሪያ ተቀባይነት አላገኘልንም ነበር” የምትለው ሳምራዊት ስሪ ዲ ማተሚያው እንደ ሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ የመጀመሪያ በመሆኑ ፈንድ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ነግራናለች።

 “ከሌሎች የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች ጋር ተወዳድረን በካፕስቶን ፕሮጀክት ተቀባይነት በማግኘት ማሽኑን እንዲሰራበት የገንዘብ እና የቁስ ድጋፍ አግኝቻለሁ” ብላለች። ተማሪዎቹ ለፈጠራ ስራው ያነሳሳቸው ማሽኑ በኢትዮጵያ እንደልብ አለመገኘቱ እና ተማሪዎች ወረቀት እና ካርቶን በመቅደድ የሚሰሯቸውን ‹ፕሮጀክቶች› ድካም ለማቃለል መሆኑን ይናገራሉ።

 “ተማሪ እያለን ለልምምድ የተለያዩ ወረቀቶችን እና ካርቶኖችን በመቀዳድ ነበር ፕሮጀክቶችን የምንሰራው። ይህን ለማስቀረት ደግሞ ስሪ ዲ ማተሚያ ማሽን እጅግ ተመራጭ ነበር” ብለዋል። ስለ ሂደቱ ሲያብራሩም “በሂደት ሁሉም አምኖ፣ ስራችንን እንዲቀጥል ተደርጎ፣ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመወዳደር በካፕስቶን ፕሮጀክት ተመራጭ ሆነናል”

በወጣቶቹ የተሰራው የስሪ ዲ ማተሚያ የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆችን እያተመ ይገኛል። “ማሽኑ አሁን ባለው ገበያ ከሠላሳ እስከ አርባ ሺህ ብር እንደሚሸጥ ሰምተናል” የሚሉት ተማሪዎቹ ማሽኑን በብዛት በማምረት ከውጭ ከሚመጣበት ባነሰ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ማስቻል የወደፊት እቅዳቸው ነው።

የፈጠራ ሥራው ዩኒቨርሲቲው አሉኝ ብሎ ከሚመካባቸው በተማሪዎች የተሰሩ የፈጠራ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ለመሆን እንደቃ አዲስ ዘይቤ ሰምታለች። ዩኒቨርሲቲው በሚያሰናዳቸው የፈጠራ ሥራዎች አውደ ርዕይ ተደጋግሞ ለዕይታ በቅቷል።

 ተማሪ ሞኢቦን አርፋሳ የአምስተኛ ዓመት የኢንጅነሪንግና የኮሙፒዮተር ምህንድስና ት/ክፍል ተማሪ ነው። የማሽኑን ጠቀሜታ አስመልክቶ ሲናገር

 "በዚህ ዓመት የአምስተኛ ዓመት ተማሪ ነን። ከዚህ ቀደም የነበሩ ተማሪዎች በተግባር የሚመለከቱት ነገር ባለመኖሩ አሁን ላይ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል። እኛ ግን እድለኞች ሆነን ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የፈለግነውን ቅርፃ-ቅርፅ በፕላስቲክ አማካኝነት እየሰራን ነው” የሚል ሐሳብ ሰጥቷል።

 የተማሪዎችን የመመረቂያ ጽሑፍ የሚያማክሩት በሀዋሳ ዮኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኤሌትሪካል እና ኮሚፒዩተር ኢንጅነሪንግ ት/ክፍል ባልደረባ የሆኑት መምህር ሙሉነህ ኃይሉ የፈጠራ ስራውን ወደ ገበያ ለማውጣት ጥቃቅን ስራዎች ብቻ እንደሚቀሩ ይናገራሉ። እንከኖቹ ታርመው በቅርብ እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

 "ስሪ ዲ ፕሪንተሩ ምንም እንኳን ተማሪዎቹ ለመመረቂያ ጽሑፍ ለምርቃት ማሟያ የሰሩት ቢሰሩትም ተወዳጅነት አግኝቷል። በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ አማካኝነት ተመዝግቦ የፈጠራ ሰርተፍኬት ለማግኘት ከጫፍ ደርሷል። ማሽኑን በጥቃቅን እና አነስተኛ ለተደራጁት ወጣቶች ለማስተላለፍ በጣም ጥቂት ስራዎች ይቀሩናል” ብለዋል።

አስተያየት