ታህሣሥ 20 ፣ 2014

የኢሚግሬሽን የዜግነት እና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ የአዳማ ቅርንጫፍ አሰራር ላይ የተነሱ ቅሬታዎች

City: Adamaመልካም አስተዳደር

አሰልቺውን ሰልፍ፣ ለቀናት የተራዘመውን ጥበቃ እንደሚያቃልል የታመነበት አገልግሎት የታለመለትን ዓላማ እንዳልመታ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የኢሚግሬሽን የዜግነት እና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ የአዳማ ቅርንጫፍ አሰራር ላይ የተነሱ ቅሬታዎች

የኢሚግሬሽን የዜግነት እና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ቀድሞ በአዲስ አበባ ብቻ ይሰጥ የነበረ የፓስፖርት ማውጣት፣ ማደስ፣ እና መሰል አሰራሮችን ለማቀላጠፍ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከፍቷል። የተቋሙን አገልገሎቶች ፈልገው ከመላው ሐገሪቱ የሚመጡ ተገልጋዮችን ቁጥር ይቀንሳል፣ አገልግሎቱን ፈጣን እና ቀልጣፋ ያደርጋል የተባለለት አገልግሎት አዳማን ጨምሮ በሌሎች 9 ከተሞች ከተጀመረ ጥቂት ቆየት ብሏል። የኢትዮጵያን ፓስፖርት የማደስና አዲስ የማውጣት አገልግሎቱን ለማዘመን ወረፋ ማስያዝ የሚቻለው በተቋሙ ድረ-ገጽ አማካኝነት በኢንተርኔት ነው።

አሰልቺውን ሰልፍ፣ ለቀናት የተራዘመውን ጥበቃ እንደሚያቃልል የታመነበት አገልግሎት የታለመለትን ዓላማ እንዳልመታ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ። እንደ ነዋሪዎቹ አባባል ምስራቅ ኢትዮጵያን ታሳቢ አድርጎ አዳማ ላይ የተከፈተው ጽ/ቤት ችግሮቹን ሙሉ ለሙሉ አላቃለለም።

ወረፋ በኢንተርኔት የማስያዝ አሰራሩ ከተተገበረባቸው ካለፉት 2ዓመታት ወዲህ ከ100 እስከ 500 ብር በማስከፈል ቀጠሮ ማስያዣ ፎርሙን የሚሞሉ ኢንተርኔት አስጠቃሚ ቤቶች እንዳሉ የአዳማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ማንኛውም አመልካች በግሉ እንዲገለገልበት የተሰናዳው ቀጠሮ ማስያዣ ድረ-ገጽ ጠንካራ ኢንተርኔት የሚፈልግ በመሆኑ በእጅ ስልክ በቀላሉ መጠቀም እንደማይቻል ተጠቃሚዎች አንስተዋል።

የ“ትንሳዔ የጉዞ ወኪል” ባለቤት አቶ ትንሳዔ ከሲስተሙ ይልቅ ኢሚግሬሽን ጽ/ቤት ያለው ችግር የበለጠ አሳሳቢ ነው ይላል። የ“ጸጋ ኃ.የተ.የግ.ማኅበር” ባለቤት አቶ ጸጋያለው ሳሙኤል በበኩሉ የጉዞ እና የአስጎብኚ አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅታቸው እስካሁን ወደ 200 ለሚጠጉ ሰዎች በድርጅታቸው አማካኝነት አዲስ ፓስፖርት የማውጣት፣ የማደስ፣ የጠፋን የመተካት ቀጠሮ እንዳስያዙ ነግረውናል። ድርጅቱ ቀጠሮ አስይዞ የባንክ ክፍያ በራሱ ሰራተኞች አስፈጽሞ ለአገልግሎቱ ብር 300 እንደሚያስከፍል ነግሮናል። የአከፋፈል ስርአቱን በተመለከተ ሲያብራራ

"እንደኮምፒውተር ባለሞያነቴ የተዘረጋው ሲስተም ጥሩ ነው። ነገር ግን የሚከፈለው በንግድ ባንክ ብቻ መሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ቅርንጫፎች ላይ አሰራሩ አለመታወቁ ችግር ይሆንብናል" ብሎናል።

“ኤጀንሲው የኦንላይን ቀጠሮውን በሚገባ በክልል ከተሞች አስተዋውቆ ህዝቡንም ከእንግልት መታደግ ቢቻል ለብዙ ዜጎችም የገቢ አማራጭ ቢፈጥር መልካም ነው” ሲል ሀሳቡን ይደመድማል።

ፍራንኮ አእሞሮ ህንጻ ላይ 'ሚ ኢንተርኔት ካፌ' ውስጥ ያገኘናት ዝናሽ የካፌው ተቆጣጣሪ ናት። በድርጅታቸው ከፓስፖርት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ይሰጡ እንደሆን ለደንበኞቻቸው ቀጠሮ የማስያዝ ሥራ እንደሚሰሩ ትናገራለች። 200 ብር የሚያስከፍለው አገልግሎት ከሠላሳ ደቂቃ እስከ ሦስት ሰዓት እንደሚወስድም ነግራናለች።

ከሲስተሙ መዘግየት በተጨማሪ ክፍያ የሚከናወነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ መሆኑና ይህንንም የሚሰሩት አባገዳ እና አዳማ ዋና ቅርንጫፎች ብቻ መሆናቸው ደንበኞችን ምቾት እንደሚነሳ መታዘቧን ነግራናለች።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ዲስትሪክት የብራንች ባንኪንግ እና ኦፕሬሽን ሰፖርት ማናጀር አቶ ጌታሁን አያሌው ቀድሞ በነበረው አሰራሩ ቀድሞ በነበረበት ሁኔታ ላይ አለመሆኑን ይናገራሉ። አስቀድሞ ማንኛውም ፓስፖርት የሚያወጣ ሰው አካውንት ከፍቶ የአገልግሎት ክፍያ የመክፈል ግዴታ ነበረበት ይላሉ።

በአሁን ወቅት ክፍያም በኢሚግሬሽን ጽ/ቤት መከናወኑ ባንኩ ከሀገር ውጪ ለስራ የሚጓዙ ሰዎችን ለማስተማር የሚያደርገውን ጥረት እንደቀነሰ ይናገራሉ።

ከቀጠሮ አስያዥ ድርጅቱ የተነሳውን ቅሬታ በተመለከተ "አብዛኛው ከፋይ የኢሚግሬሽን ጽ/ቤት አካባቢ ያሉ ቅርንጫፎችን ስለሚጠቀም ስለወረፉ ይነሳል። ከዚህ ውጪ ሁሉም ቅርንጫፎች እንደሚሰሩ ነው የምናውቀው" ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ዳግም ታደሰ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ አምርቶ ፎርም መሙላቱን ያስታውሳል። በተሰጠው የ45 ቀናት ቀጠሮ መሠረት ሲገኝ ያጋጠመውን እንዲህ ገልጾታል። “በወረፋ መደራረብ ምክንያት ወረፋዬ ሳይደርስ ወደቤቴ ተመለስኩ። በማግስቱ ግን የተፈጠረው ሌላ ነው። ሄጄ ስጠይቃቸው ትናንትና ነበር ቀጠሮዬ በወረፋ ምክንያት አለማግኘቴን ብናገርም በቀጠሮህ አልተገኘህም ተብዬ 150 ብር ተቀጥቻለው። ይህ ብዙ ህዝብ የሚያገለግል ተቋም ነው። ለዚህ መፍትሔ ሊያበጅ ይገባል”

ህይወት ሙላቱ  ከቴሌግራም መተግበሪያ ላይ ባገኘችው አድራሻ ስልክ ደውላ፣ በተላከላት የአካውንት ቁጥር 200 ብር ከፍላ ቀጠሮ ማስያዟን ትናገራለች። በኢሚግሬሽን ኤጀንሲ አካውንትም ገንዘብ የፓስፖርት ማደሻ 600 ብር መክፈሏን አጫውታናለች። የቀጠሮ ፎርሙም በቴሌግራም እንደደረሳት እንዲሁ። "በቀጠሮዬ ቀን ስሄድ ግን አልደረሰም ብለው እንደአዲስ ሞልተው ቀጠሮ ያዙልኝ። ወደ ሰውየው ደግሜ ስደውል ስልኩን አያነሳም። አቤት የምልበት አጥቼ ዝም አልኩ" ስትል ገጠመኟን እና ኪሳራዋን ነግራናለች።

ስሟን መግለጽ ያልፈለገችው አስተያየት ሰጪአችን ደግሞ "ሰራተኞቹ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ምግባር ችግር ይታይባቸዋል። በተለይ ለሴት ልጅ ከፍተኛ የሆነ ንቀት ያሳያሉ። ስድብና ዘለፋም አለ" የምትለው እጸገነት አዲስ “ፓስፖርት ለማውጣት የሚከፈለው 600 ብር ቢሆንም ለመቀበል ፖስታ ቤት ስትሄድ 215 ብር ተጨማሪ ያስከፍላሉ ይኼ ተገቢ አይመስለኝም” ስትል ስትል አስተያየቷን ትደመድማለች። ክፍያው ሕጋዊ ከሆነ ከፋዩ አስቀድሞ ሊነገረው ይገባል ባይ ነች።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ወ/ሮ ዘይን ገድሉ ስለ ፓስፖርት እደላ ክፍያ ጉዳይ ያላነሳንላቸውን ጥያቄ በአዲስአበባ ክፍያ ዋጋ 50፣ በክልል ዋና ከተሞች  70 ብር ብር እና ከክልል ዋና ከተሞች ወጪ 100 ብር እንደሆነ እና ሌላ ክፍያ ተመን አለመኖሩን ነግረውናል።

ከአገልግሎት መስጫ ስፍራዎች አንጻር በአሁኑ ወቅት በቋሚነት እየሰራ ያለው ትልቁ ፖስታ ቤት ብቻ እንደሆነ የነገሩን ኃላፊዋ "በአብዛኛው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በተመሳሳይ ሰዓት አገልግሎቱን ለመጠቀም ስለሚመጡ መጨናነቅ ይፈጠራል።  በአብዛኛው ከሰዓት በኋላ ነፃ እንደሆነ መረጃው አለን" በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

አገልግሎቱን ወደ ሌሎች ከተሞች ከማስፋፋት ጋር በተያያዘም በቅርቡ ጋምቤላ እና አሰላ ከተማ ላይ የፓስፖርት እደላው እንደተጀመረ ሰምተናል።

በስራ መውጫ ሰዓት ላይ በኢሚግሬሽን ጽ/ቤት በር ላይ ሕጸን ልጇን አዝላ እንድታግዛት ደግሞ ትልቅ ልጇን አስከትላ ጤናዬ ባዩ

ከአርሲ ዞን  ሽርካ ከምትባል መምጣቷን ነግራናለች። "ለሊት 11 ሰዓት ተነስተን ጉዞ የጀመርን ገና አሁን ነው የደረስነው። እዚህ ስንደርስ ደግሞ ተዘግቷል። ለነገ ጠዋት ስላሉን ማደሪያ ልንፈልግ ነው" ስትል ሁኔታውን ለሪፖርተራችን ነግራናለች። ጤናዬ ፓስፖርት የማውጣት ወረፋውን በኢንተርኔት ማስያዝ እንደሚቻል አታውቅም። 

ቢቂላ ዳመና በበኩሉ ከአዳማ 100 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ከምትገኘው አሰላ እህቱን ይዞ መጥቶ ወረፋ እየጠበቀ ነው። "ከወር በፊት ከሌላ ሰው ጋር መጥታ ነበር። ያኔ በቀጠሮዋ መሠረት ስትመጣ ጉዳይዋን የያሰው ሰው የለም ስለተባለ ነው እኔ ያመጣኋት። አሰላ ሆኜ በኢንተርኔት ወረፋ ማስያዝ እንደምችል የሰማሁት ዛሬ ነው” ብሎናል።

የተገልጋዮችን ቅሬታ በመያዝ የሚመለከታቸውን የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች አነጋግረን በቅሬታው ላይ የሚሰጡትን ምላሽ በዘገባው ላይ ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። 

አስተያየት