የካቲት 29 ፣ 2014

የአዳማ የግል ተቋማት መምህራን ቅሬታ

City: Adamaመልካም አስተዳደር

መረጃው በግል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች በመንግስት ተቋማት እየተማሩ ከሚገኙት ጋር ሲነጻጸር በ2ሺህ 400 ተማሪዎች ብልጫ አለው። በትምህርት ቤቶች ብዛትም የግል ተቋማት ከመንግሥታዊዎቹ በ5 እጥፍ ይበልጣሉ።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የአዳማ የግል ተቋማት መምህራን ቅሬታ
Camera Icon

ፎቶ፡ ምሀበራዊ ሚድያ

በአዳማ ከተማ በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ በድምሩ 134 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚገኙ ከአዳማ ትምህርት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እንደ መረጃው ከቅድመ-መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉ የትምህርት እርከኖች 2መቶ 85 ት/ቤቶች የሚያስተምሩ 2ሺህ 294 መምህራን ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል የግሉ ዘርፍ በ2መቶ 38 ትምህርት ቤቶች 68ሺህ 487 ተማሪዎችን እና 1ሺህ 506 መምህራንን ይይዛል።

መረጃው በግል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች በመንግስት ተቋማት እየተማሩ ከሚገኙት ጋር ሲነጻጸር በ2ሺህ 400 ተማሪዎች ብልጫ አለው። በትምህርት ቤቶች ብዛትም የግል ተቋማት ከመንግሥታዊዎቹ በ5 እጥፍ ይበልጣሉ።

በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የጥናት ወረቀት የሰራው አቶ ተሾመ ነቅዓጥበብ በዚትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ 5 ዓይነት የትምህርት ተቋማት እንዳሉ አብራርቷል፡፡ እነርሱም የማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት፣ ለትርፍ የተቋቋሙ፣ ከሐገራቸው ውጭ ለሚኖሩ የውጭ ሐገር ዜጎች የተቋቋሙ፣ ባህላዊ ናቸው፡፡

በመምህራን ቅጥር ረገድ ያለው ብልጫ ከፍተኛ የሚባል አለመሆኑን የትምህርት ጽ/ቤቱ መረጃ አስቀምጧል። ይሁን እንጂ በግል ተቋማት ውስጥ በማስተማር ላይ የሚገኙት መምህራን “መንግሥት ረስቶናል” የሚል ቅሬታ አላቸው። “በሥራችን ውጤታማነት በመንግሥት ተቋማት ከሚገኙ መምህራን ብንበልጥም። የመንግሥት ትኩረት ግን ተነፍጎናል” ይላሉ። መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያህል ለመምህራኑ አለመስጠቱ አሰሪ ባለ ሐብቶች መሰረታዊ መብቶቻቸውን እንዳያከብሩ ስለማድረጋቸው ያምናሉ።

ከቅሬታዎቻቸው መካከል የደሞዝ ማነስ፣ የስራ ላይ ደህንነት አለመከበር፣ ወቅታዊ  የሙያ ምዘና እና የትምህርት እድሎች መነፈግ እንደሚገኙበት መምህራኑ ያነሳሉ።

መምህር ኤፍሬም ደበበ በግል ትምህርት ቤቶች ማስተማር ከጀመረ 9 ዓመታት እንደሆነው ይናገራል። በአሁን ወቅት የኤክሴል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህርና የት/ቤቱ መምህራን ተወካይ ነው። “የግል ዘርፉ ከባዱን የመንግሥት ሸክም አቅልሏል” ይላል።

የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት እና ከትምህርት ጥራት አንጻር የግል ት/ቤቶች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የሚያምነው መምህር ኤፍሬም ለስኬቱ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት መምህራን ስለመሆናቸው ደጋግሞ ያነሳል።

“ክፍያችን የውለታችን ተቃራኒ ነው። የሚከፈለን ከአበርቷችን በታች ነው” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። ለአባባሉ ማጠናከሪያ ከሙያ ማሻሻያ እስከ መኖሪያ ቤት ያሉ ጥቅማ-ጥቅሞችን ለመምህራን ያዘጋጀው መንግሥት የግሉ ዘርፍ መምህራንን አለማካተቱን እንደ ዋነኛ ችግር አንስቷል።

“የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ አቻዎቻችን የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅም አለማግኘታችን መረሳታችንን ያሳያል። በሌላ በምንም ልንገልጸው አንችልም” ያለ ሲሆን በከተማው የሚገኘው የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ት/ቤት ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ሲያመጡ ለመምህራኑ በመንግሥት ከፍተኛ እውቅና መሰጠቱን አስታውሷል። “በቀጣዩ ት/ቤታችን ከፍተኛ ውጤት ቢያስመዘግብም መምህራኑን ያስታወሰ የመንግሥት አካል የለም” ሲል ልዩነቱን በንጽጽር ያስረዳል።

መቀመጫውን አዳማ ካደረገው ግል ድርጅት ሰራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ደቡብ ምስራቅ ሪጅን ከ6ሺህ 6መቶ በላይ የግል ት/ቤት መምህራኑን መመዝገቡን ገልጿል። ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በ314 ከአጸደ ህጻናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙት መምህራን መሆናቸውን ኤጀንሲው ይገልጻል።

መምህርት ዓለምእሸት ኃይሌ በመህርትነት 15 ዓመታት አሳልፋለች። ያለፉትን 6 ዓመታት ደግሞ በዩኒቲ አካዳሚ በማስተማር ላይ ትገኛለች። የግል መምህራን ማኅበር ያለመኖር መምህራን ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳመጣ ትናገራለች። "በስራ ቆይታዬ አንድም ጊዜ የትኛውም ማኅበር መጥቶ አደራጅቶንም ስላለብን የኑሮ ጫና አወያይቶንም አያውቅም" የምትለው ዓለምእሸት ኃይሌ ከዚህ ቀደም የሰራችበት ትምህርት ቤት ዋናውን የትምህርት ማስረጃ ለ1 ወር ተቋሙ እጅ መቀመጥ አለበት በሚል ከወሰዱት በኋላ የሥራ ቦታ ስትቀይር በፍጥነት ማስረጃዋን ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ብዙ እንዳንገላታት ትናገራለች። ከበዛ እንግልት እና ልመና በኋላ ትምህርት ቤቱ ማስረጃዋን ለቆላታል።

“የግል ተቋማት ላይ በሚያስተምሩ መምህራን ላይ የሚደርሰው ጫና በሴት መምህራን ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍ ያለ ነው” የምትለው መምህርቷ የሙያ ማሻሻያ መውሰድ አለመቻላቸው ከሚወዱት የመምህርነት ሙያ እያራቃቸው እንደሚገኝ ነግራናለች።

ከ2ዓመት በፊት በምታስተምርበት ተቋም የሚያገለግሉ 25 መምህራን ተደራጅተው ከመንግሥት ቦታ ለማግኘት ያደረጉት ጥረትም እንዳልተሳካ ታስታውሳለች።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪአችን እጹብ ድንቅ ተመቸ ትባላለች። የመምህርነት ሥራ የጀመረችው በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ላይ ነው። “በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ መምህራን የሚስተናገዱበት መንገድ አግባብነት የለውም” ትላለች። የምታስተምርበትን ተቋም ደብቀን ሐሳቧን እንድንጠቀምበት ፈቅዳልናለች። "የማስተምረው በዋና መምህርነት ቢሆንም ላለፉት 6 ወራት እየተከፈለኝ የሚገኘው የረዳት መምህራን ደሞዝ ነው። በዋና መምህርነት ተገምግሜ ከ90 በመቶ በላይ ባመጣም የተለወጠ ነገር የለም” ትላለች።

በአሰሪዎቿ በደል ከመስማማት ውጭ ያላት አማራጭ ስራ ማቆም ብቻ መሆኑን ነግራናለች። እንደ እጹብድንቅ ማብራሪያ አቤት የምትልበትን ባለማወቋ ምላሻቸውን እየጠበቀች ወራቶች ተቆጥረዋል። በምታስተምርበት ተቋም 20 መምህራን ቢኖሩም ተደራጅተው ስለራሳቸው ኃሳብ ሚለዋወጡበት መንገድ ባለመኖሩ ሁሉም በደሉን ለብቻው ይዞ ስለመቀመጡ በወራት ቆይታዋ ታዝባለች።

የአዳማ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት የመምህራን እና ት/ቤቶች ልማት የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ ታዬ ተካ "እኛ የምንሰራው ከትምህርት ቢሮ በሚሰጠን መመሪያ መሰረት ነው" ይላሉ። “ከመንግሥት የግል መምህራንን ማብቃት ላይ ይህ ነው ተብሎ የተሰጠን አቅጣጫ ባለመኖሩ ምንም አልሰራንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በመምህራኑ በኩል የተሻለ ትምህርት፣ የሞያ ምዝና ፈተናዎች፣ የመኖሪያ ቤት፣ መስሪያ ቦታ እና መሰል ጥያቄዎች እንደሚነሱ እንደሚያውቁ የነገሩን አቶ ታዬ የቢሯቸው ትኩረት በመንግስት ተቋማት ላይ እንደሆነ ነግረውናል።

“የዲግሪ ተመራቂ የመንግሥት ት/ቤት መምህር መነሻ ወርሃዊ ደሞዝ 4ሺህ 6መቶ 9 ብር በዲፕሎማ እና 5ሺህ 3መቶ 58 ብር ቢሆንም እንደትምህርት ቤቱ አሰራር ይለያያል” የምትለው መምህርት እጹብድንቅ በረዳት መምህርነት በወር 1500 ብር እንደሚከፍሏት ነግራናገራለች።

ከዚህ በፊት በናፍያድ ት/ቤት ይሰራ እንደነበር የሚናገረው መምህር ት/ቤቱ በኮቪድ-19 ወቅት መንግስት ያስቀመጠውን የመምህራን ክፍያ ወላጆች ክፍያ አልከፈሉኝም ብሎ በማስቀረቱ ጉዳዩ እስከፍርድ ቤት መድረሱን ያስታውሳል። ከፍርድቤት ምልልስ በኋላ ጉዳዩ ያለ ተጨባጭ ውጤት መቋጨቱን ነግሮናል።

በ1965 ዓ.ም. በወቅቱ ሕጋዊ ሰውነት የነበረው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በአዳማ ሁለት ቅርንጫፎች አሉት። የምስራቅ ሸዋ እና የአዳማ መምህራን ማኅበራት። ማኅበሩ በሙያ ዘርፉ ላይ የሚገኙ መምህራንን መብት ለማስከበር የቆመ ቢሆንም ከግል መምህራኑ ጋር ያለው ግንኙነት ግን የላላ እንደሆነ የግል ትምህርት ቤት መምህራኑ ይናገራሉ። 

ማኅበሩ በአዳማ ከተማ በሚገኙ ሁሉም ት/ቤቶች እና በአዳማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ  ውስጥ የሚገኙ 1ሺህ 5መቶ 64 መምህራንን በአባልነት አቅፏል። “የአባልነት መስፈርቱ መምህር መሆን ብቻ ነው” ያሉት የአዳማ መምህራን ማኅበር ሊቀ-መንበር አቶ አበራ ቶሎሳ እያንዳንዱ አባል በዓመት 120 ብር ወርሃዊ መዋጮ የመክፈል የአባልነት ግዴታ እንዳለበትም ሰምተናል።

የአዳማ መምህራን ማኅበር ስራ አስኪያጅ መምህር አበራ ቶላ ማኅበሩ የግል መምህራንን ጥቅም ከማስከበር አንጻር ሰራ የሚሉትን ሲያብራሩ "ከዚህ በፊት የግል መምህራን አባል ነበሩ። ለመንግስት መምህራን በመንግስት ውሳኔ የቤት መስሪያ ቦታ ተሰጥቶ ባለማግኘታቸው ማኅበሩን ለቀዋል" ሲሉ ያነሱት ስራአስኪያጁ የማኅበሩ አባል ላልሆኑ የግል ትምህርት ቤት መምህራን ለመከራከር ስለማይቻል ሁሉም የግል ትምህርትቤት መምህራን የማኅበሩ አባል እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል።

አቶ ዋቅሹም ዱጋሳ የሚድላንድ እና የኬኛ ት/ቤቶች ቦርድ አባል ናቸው። ለመምህራን የተሻለ ህይወት እና የስራ ደህንነት እየሰሩ የሚገኙትን በተመለከተ ከአዲስ ዘይቤ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ "ለመንግሥት በተደጋጋሚ ባቀረብነው ጥያቄ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ለግል መምህራን የብቃት ማረጋገጫ ለመፈተን ፈቅዷል። ምዘናው የመምህራኑን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ጥሩ እድል ይፈጥርላቸዋል” ብለዋል። ምዘናው የተፈቀደው ፔዳጎጂ (ስነ-ትምህርት) ለተማሩ መምህራን ብቻ እንደሆነም ሰምተናል።

ከአዳማ ትምህርት ጽ/ቤት የሙያ ምዘና ለመውሰድ በዲፕሎማ እና በዲግሪ ደረጃ 924 መምህራንን መልምሏል። በዲግሪ ደረጃ 181 መምህራን ለምዘና ሲቀርቡ ይህ የመጀመርያው ነው።

አስተያየት