ጥር 27 ፣ 2014

ደረጃውን ባልጠበቀ የፍጥነት መገደቢያ የተማረሩት የድሬዳዋ አሽከርካሪዎች

City: Dire Dawaመልካም አስተዳደር

የፍጥነት መገደቢያዎቹ በርከት ያለ ቁጥር ያለው ህዝብ ያለበት ቦታ ስለሚገኙ በአግባቡ መገንባታቸው የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ደረጃውን ባልጠበቀ የፍጥነት መገደቢያ የተማረሩት የድሬዳዋ አሽከርካሪዎች
Camera Icon

ፎቶ፡ ዝናሽ ሽፈራው

ዘመኑ ታረቀኝ በድሬደዋ ከተማ የሚኖር የደረቅ ጭነት አሽከርካሪ ነው። በዋና መንገዶች እና በመንደር ውስጥ መንገዶች ላይ የሚገነቡት የተሽከርካሪ  የፍጥነት  መገደቢያዎች  የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ቢያምንም ጥራታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳል።  በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙት አብዛኛዎቹ  የፍጥነት መገደቢያዎች በተገቢው አካል፣ በጥራት ተገንብተዋል የሚል እምነት እንደሌለው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

“የአንዳንዶቹ ከፍታ ከሚገባው ባላይ ነው። የፍጥነት መገደቢያ እንዳለ የሚያመለክት የመንገድ ቀለም ወይም አንጸባራቂ የሌላቸውም በርካታ ናቸው” የሚለው አቶ ዘመኑ ፍጥነት ገዳቢዎቹ ሲገነቡ የመንገድ ደህንነት ሕግን አለመከተላቸው አስቀድሞ መንገዶቹን ለማያውቅ አሽከርካሪ ስቃይ እንደሚሆኑ አጫውቶናል። “በተለይ ቦታውን የማያውቀው ሰው ምንም እንደሌለ አስቦ ሲጓዝ ከ‘ሳልቶ’ (የመንገድ ጠርዝ) ጋር ይላተማል። በአስፋልቱ ዳርና ዳር ላይ ጠርዝ የሌለው ከሆነ፤ በባለሙያ ያልተገነባ ‘ሳልቶ’ ከሆነ ደግሞ የትራፊክ አደጋ ሊያደርስ የሚችልበትን አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል” ብሎናል። ነገሩን በምሳሌ ሲያስረዳ “ብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት አካባቢ ያለው የመንገድ ጠርዝ (ሳልቶ) ከሚገባው በላይ ከፍ ያለ በመሆኑ ለመኪኖች ይከብዳል” በማለት አስተያየቱን ይደመድማል።

“የፍጥነት መገደቢያዎቹ በርከት ያለ ቁጥር ያለው ህዝብ ያለበት ቦታ ስለሚገኙ በአግባቡ መገንባታቸው የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው” የሚለው በድሬዳዋ ከተማ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የሚያሽከረክረው ያሬድ ውብሸት ነው። “መገደቢያ ያላቸው ቦታዎች ላይ ስንደርስ ፍጥነታችንን ቀንሰን፣ ባጃጃችን ላይ የመሪ መጣመም እንዳይደርስ ተጠንቅቀን እናልፋለን። ነገር ግን አብዛኛዎቹ በከተማዋ የሚገኙ የፍጥነት መገደቢያዎች በኮንክሪት የተገደቡና የማይመቹ ናቸው። ቶሎ ቶሎ ስለሚበላሹ የተሸከርካሪዎችን ምቾት ያሳጣሉ” ብሏል።

ሌላዋ የድሬዳዋ ነዋሪ ኢማን ሁሴን በተለይ ከእሸት ወደ ሰዒዶ የሚወስደውን መንገድ ምርጫ ካላጣች እንደማትጠቀምበት ትናገራለች። የሰባት ወር ነፍሰጡር የሆነችው ኢማን በተጠቀሰው መንገድ ላይ የተገነባው የፍጥነት መገደያ በከፍታው ምክንያት መንገጫገጩን እንደሚያብሰውና ህመም እንደሚያስከትልባት ነግራናለች።

በድሬደዋ አስተዳደር  የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ኮማንደር ጉልማ ታዩ “ለትራፊክ አደጋ በመንስኤ እንደሆኑ ከተለዩት ጥፋቶች መካከል ዋነኛው ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ነው። በፍጥነት ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ ለማስቀረት ከምንጠቀምባቸው ዘዴዎች መካከል በመንገዶች ላይ የሚገነባ ‘ሳልቶ’ (ፍጥነት መገደቢያ) አንዱ ነው” ብለዋል።

የተሽከርካሪዎችን ፍጥነት ለመገደብ ሁለት ዓይነት መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላሉ። የመጀመሪያው በተሽከርካሪዎች ላይ የሚጠም ሲሆን፤ የተሽከርካሪ መንገዶች ላይ የሚገነባው ‘ሳልቶ’ (የፍጥነት መገደቢያ) ደግሞ ሁለተኛው ነው። በተሽከርካሪ ላይ የሚገጠም የፍጥነት መገደቢያ  ኢትዮጵያ ውስጥ መተግበር  የጀመረው  ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በ27/2011 መመሪያ መሰረት ነው። መመሪያው በ692/2013 መመሪያ ተሻሽሎ ሁሉም አሽከርካሪዎች እንደየአገልግሎታቸው ፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ እንዲገጥሙ አስገድዷል።

እንደ ኮማንደር ጉልማ ገለፃ “በተሽከርካሪ  ላይ  የሚገጠመው  የተቀናጀ  የተሸከርካሪ  ፍጥነት  መቆጣጠሪያ  መሳሪያ  ከዓለም  አቀፍ  ስርዓት  አቅጣጫ  ጋር  የተጣመረ ሆኖ ወደ ተሸከርካሪው ሞተር የሚገባውን ነዳጅ አለያም አየር በመቀነስ የተሸከርካሪውን ፍጥነት የሚቆጣጠር መሳሪያ ነው።”

ሁለተኛው በተሸከርካሪዎች ላይ የሚገጠመው የፍጥነት መቀነሻ በቂ ስላልሆነ ሰዎች በሚሰበሰቡበት አካባቢ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የዕምነት ስፍራዎች እና የንግድ እንቅስቃሴ በሚዘወተርባቸው አካባቢዎች ፍጥነት መገደቢያዎች ይገነባሉ። ፍጥነት ገዳቢዎቹን ለመገንባት  ፈቃድ  የሚሰጠው  የመንገድ  ደህንነት  ሲሆን ስራውን የሚሰራው ደግሞ መንገዶች ባለስልጣን እንደሆነ ሰምተናል።

ኮማንደር ጉልማ ድሬደዋ ውስጥ ስለሚገኙት የመንገድ ላይ የፍጥነት መገደቢያዎች የተነሳላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ፡-  አግባብነት  በሌለው  ሁኔታ  ተገቢው  አካል  ሳይፈቅድ የተሰሩ ‘ሳልቶዎች’ እንደሚገኙ ገልፀዋል። ለምሳሌ በቀበሌው አስተዳደር ፈቃድ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ያለምንም ፍቃድ የተሰሩ ‘ሳልቶዎች’  ይገኛሉ።  እንደ ኮማንደር ጉልማ ገለፃ ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር የሚመለከታቸው አካላት የተቀናጀና የተናበበ አሰራር ይከተሉ እንዳልነበር ተናግሮ በአሁን ሰዓት ችግሩን ለመቅረፍ ከትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዥዎን፣ ትራፊክ ቁጥጥር፣ ትራንስፖርት ሎጂስቲክ ሚንስተር እና መንገዶች ባለሥልጣን በጋራ በመሆን ድሬዳዋ ውስጥ የሚገኙትን የፍጥነት መቀነሻዎች በማስጠናት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

 በድሬደዋ አስተዳደር የትራፊክ ፖሊስና የሽፍት አስተባባሪ ሚካኤል ካሳሁን “የትራፊክ አደጋ  በሚበዛባቸው  ቦታዎች  ከአደጋ  መርማሪዎች  ጋር  በመሆን  የፍጥነት መገደቢያ ካስፈለጋቸው እንዲገነባላቸው ለመንገዶች ባለሥልጣን ጥቆማ እንሰጣለን። ነገር ግን በአንዳንድ ሰፈሮች የሚገኙ ነዋሪዎች አደጋን ከመስጋት በራሳቸው ተነሳሽነት የፍጥነት መገደቢያ ይገነባሉ። በዘፈቀደ የሚከናወነው ግንባታ ተገቢውን ርቀት ላይጠብቅ፣ ከሚገባው በላይ ከፍ ወይም ዝቅ ሊል የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል” ብለዋል።

አስተያየት