የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ሊጓዙ የነበሩ የቤተ-እስራኤላውያንን ጉዞ በጊዜያዊነት እንዲቆም ወሰነ።
ፍርድ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የእስራኤል የስደት ፖሊሲ ማእከልን ጨምሮ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች “ወደ እስራኤል መመለስ የሚፈልጉት ኢትዮጵያ የሚገኙት ዜጎችን አይሁዳዊነትን ለማረጋገጥ ትክክለኛ መመዘኛ አለመቀመጡ እና ዜጎቹ የዘር ሀረጋቸው ከእስራኤል የሚመዘዝ መሆኑ ወደ አስራኤል ሳይገቡ መረጋገጥ ይኖርበታል” በማለት ያሰባሰቡትን ቅሬታ ተመልክቶ ነው።
ወደ እስራኤል መመለስ የሚፈልጉ 3 ሺህ ኢትዮጵያውያን በጊዜያዊነት በአዲስ አበባ እና ጎንደር በሚገኙ የትራንዚት መጠለያዎች የሚገኙ ሲሆን በእስራኤል የሚገኙት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች “በመጠለያዉ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ዜጎች ቤተ-እስራኤላዊ አይደሉም” ብሏል።
ቅሬታውን ያሰባሰቡት ድርጅቶች ስደተኞቹ ወደ እስራኤል እንዲመለሱ የተዘጋጀው መስፈርት እና በቀጥታ እንዲገቡ በእስራኤል መንግስት የተደረሰበት ውሳኔ “የሀገሪቱን ወደ እስራኤል መግቢያ ህግ የጣሰ ነው” ማለታቸውን የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ አስነብቧል።
የእስራኤል የስደት ፖሊሲ ማእከል እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቅሬታቸው መነሻ “በእስራኤል ህግ መንግስትም ሆነ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር በስደት ፖሊሲ፣ ዜግነት በማግኘት ጉዳይ እና በመኖሪያ ፈቃድ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አይችሉም” የሚል ነው።
በመስከረም ወር ጋዜጣው የእስራኤል መንግስት በርካታ ኢትዮጵያውያንን ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ወደ እስራኤል መመለሱን ተከትሎ ስደተኞቹ እስራኤል ከደረሱ በኋላ ብዙኀኑ ቤተ-እስራኤላውያን አለመሆናቸውን ዘግቦ ነበር።
የመረጃ ምንጩ ስደተኞችን ወደ እስራኤል የማምጣት ሂደቱ “የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል እና የኢትዮጵያና እስራኤልን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያሽክር እርምጃ ነው” ብሎታል።
በመስከረም 2014 ዓ.ም. የእስራኤል የስደት ጉዳዮች ሚኒስቴር ከሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ጋር ባወጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጦርነት ተከትሎ ከተፈጠረው የደህንነት ስጋት ቤተ-እስራኤላውያን እና የቤተ-እስራኤላውያን ቤተሰቦችን ከኢትዮጵያ ለመመለስ መወሰናቸውን ገልፀው ነበር።
በእስራኤል የሚኖሩ ቤተ-እስራኤላዉያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ወደ 140 ሺህ እንደሚደርስ ይገመታል።