ጥር 27 ፣ 2014

በደቡብ ወሎ ለጦርነቱ ተጎጂዎች በቂ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም ተባለ

City: Dessieወቅታዊ ጉዳዮች

ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ስንዴ፣ 7.5 ኪሎ ግራም ዱቄት እና 0.4 ሊትር ዘይት ለአንድ ወር መሰጠቱ በቂ አለመሆኑን ያነሳሉ።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በደቡብ ወሎ ለጦርነቱ ተጎጂዎች በቂ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም ተባለ
Camera Icon

ፎቶ፡ ኢድሪስ አብዱ

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል 11.6 ሚልዮን፣ በደቡብ ወሎ ዞን ደግሞ ከ3 ሚልዮን በላይ ሰዎች የእለት ደራሽ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ከደቡብ ወሎ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ “496ሺህ 246 ኩንታል ያስፈልጋል። እስካሁን (እስከ ጥር 18 ድረስ የቀረበው) ወደ 168 ሽህ 207 ኩንታል ወይም ወደ 34% ማለት ነው። ስለዚህ ሰፋ ያለ ሀብት አሁንም መግባት አለበት። ከቀረበው የተሰራጨው ወደ 134 ሺህ 350 ኩንታል ነው" ብለዋል።

የእለት ደራሽ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ተጠቃሚ የሆኑት ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እየቀረበ ያለው ድጋፍም ያልተሟላና ወቅቱን ያልጠበቀ ስላለመሆኑ በተዘዋወርንባቸው የተለያዩ የእርዳታ ማስተባበሪያ ማዕከላት ተገኝተን ያነጋገርናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ያስረዳሉ።

አቶ ተስፋዬ መኮንን አቶ ተስፋዬ መኮንን ደሴ ከተማ ውስጥ የመናፈሻ ክ/ከ ነዋሪ ናቸው። እድሜአቸው ከ55 ዓመት በላይ ሲሆን የእለት ደራሽ ድጋፉ ተጠቃሚ ናቸው። “ምዝገባ በተደረገበት ሰዓትና ወቅት አስፈላጊው ግብአት እየደረሰ አይደለም። ሕብረተሰቡ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየተጉላላ ነው። በጣም ይዘገያል” ብለዋል።

የዞኑ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰይድ ረሺድም በአቶ ተስፋዬ ሐሳብ ይስማማሉ። “መሟገት የማይችልና አቅመ ደካማ የሆነ ሰው ልክ እንደ ሌሎች ርዳታው በአግባቡ ላይደርሰው ይችላል” ይላሉ። አቶ ተስፋዬ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ተረጂዎችም ስማቸው ተመዝግቦ በየወረዳቸው ከተላከ በኋላ እስካሁን ምንም እርዳታ እንዳልቀረበላቸው ያስረዳሉ። ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ስንዴ፣ 7.5 ኪሎ ግራም ዱቄት እና 0.4 ሊትር ዘይት ለአንድ ወር መሰጠቱ በቂ አለመሆኑን ያነሳሉ።

የደቡብ ወሎ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ “የዕለት ደራሽ ድጋፎች በወቅቱ ላለመድረሳቸው የተለያዩ  ምክንያቶች አሉ” ይላሉ። ከምክንያቶቹ መካከል ዋነኛው በራሳቸው ተነሳሽነት እርዳታ የሚያሰባስቡ ሰዎች፣ የእርዳታ ሰጪ ተቋማት እና የመንግሥት አለመናበብ እንደሆነ ተናግረዋል። 

“የአቅርቦት መጓተት አለ። በተለይ በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂ በነበሩት የደቡብ ወሎ ምስራቅ ወረዳዎች የገባላቸው እርዳታ ከነበረባቸው ችግር አንጻር ተመጣጣኝ አይደለም። የሚቀርበው የእለት እርዳታ አቅርቦትም የተሟላ ፓኬጅ አይደለም። ስንዴ፣ ዱቄት ወይም ዘይት ሊሆን ይችላል። የወጥ እህል እና ዘይት መሰል ድጋፎች በፓኬጁ ሊካተቱ ሲገባ አብዛኛው ይሄንን እያገኘ አይደለም። በዚህ መልኩ መንግስት ያልሸፈናቸውን ክፍተቶች ሊሸፍኑ የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል” ብለዋል።

“በተለያዩ ጊዜያት በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ሰንሰለት የተለያዩ ድጋፎች ቢደረጉም በተናበበ መልኩ አለመከናወናቸው ችግር ፈጥሯል። ድጋፉ ክፍተትን የለየ፣ ቀጥታ ለሕብረተሰቡ ተደራሽነት ያለው አሰራር መዘርጋት ይገባል” ብለዋል።

በግለሰቦችና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚደርሱ እርዳታዎች ወደ አንድ ቋት እንዲሰበሰቡ የማድረግን አስፈላጊነትም አቶ መሳይ ማሩ ያስረዳሉ። “እርዳታ ከውጭ ይመጣል፣ ድጋፍ የሚደረግለት ከውስጥ ነው። በጎ አድራጊዎች የመሰላቸውን ገዝተው ያቀርባሉ። ስለዚህ ከምንም ሊጠቅም ይችላል ግን የመጣው ሃብት ስንት ነው? ምን ያህሉ ስራ ላይ ውሏል? አልዋለም? የሚለውን ጭምር ማረጋገጥ አልቻልንም። ስለሆነም በተለይ ከውጭ እርዳታ የሚልኩና በውክልና የሚያስተባብሩ ከመንግስት አካላት ጋር ይበልጥ ተቀራርበው የሃብት ስርጭቱ በጋራ ካልተሰራ በስተቀር ብልሽትና ጉድለት ቢኖር ማረም የሚቻልበት አሰራር ወይም እድል አይፈጥርም”

ይህ በዞኑ ብቻ ሳይሆን እንደ ክልልም ቢሆን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ድጋፎችን አሰባስቦ ለተጠቃሚ በማድረስ በኩል ክፍተት እየፈጠረ የመጣ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ እታገኝ አደመ ተናግረዋል።

“የኛ ኮሚሽን አስተባባሪ ነው። ስለዚህ ሁሉም ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ አካላት በዚህ ተቋም ማለፍ ቢችሉ። እስከ መልሶ ማቋቋም ድረስ የሚሰራው በአዋጅ የተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ነው።

ከዚህ ባለፈ በግላቸው ድጋፍን ይዘው የሚቀርቡትን ድጋፉን ብንፈልገውም አካሄዱን አናበረታታም” ብለዋል። ስለሆነም ተገቢውን ድጋፍ በወቅቱ፣ በፍትሃዊነትና ችግርን በለየ መልኩ ለማቅረብ የበጎ አድራጊ ተቋማትና ግለሰቦች ትብብር ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ኃላፊዎቹ የሚመጡ ድጋፎች በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ በኩል እንዲያልፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አስተያየት