የካቲት 17 ፣ 2014

ደሴ፣ ጎንደር እና ባህርዳር ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ያንገላታቸው “ሜትሮፖሊታንት” ከተሞች

City: Bahir Darጤናመልካም አስተዳደር

በቀን 13,322 አምርታ ለነዋሪዎቿ ማከፋፈል ብትችልም ከፍላጎቱ አንጻር ማዳረስ የቻለችው 22 በመቶውን ብቻ ነው።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ደሴ፣ ጎንደር እና ባህርዳር ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ያንገላታቸው “ሜትሮፖሊታንት” ከተሞች
Camera Icon

ፎቶ፡ መሃበራዊ ሚድያ

በአማራ ክልል ከሚገኙ “ሜትሮፖሊታንት” ከተሞች መካከል የሚመደቡት ባህርዳር፣ ደሴ፣ እና ጎንደር ነዋሪዎቻቸው እያንዳንዳቸው በቀን 80 ሊትር ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው የክልሉ ውሃና ኢነርጅ ልማት ቢሮ መረጃ ያሳያል። ከ22 ሚልዮን በላይ ህዝብ መኖርያ የሆነው ክልሉ የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት መጠኑ ያልተመጣጠነ ነው። ከከርሰ ምድር እና ከገጸምድር የውሃ ሃብቶች የሚመረተው ንጹህ የመጠጥ ውሃ በበቂ ሁኔታ መዳረስ አለመቻሉ የዘወትር የነዋሪዎች ምሬት ነው።

ገነት ማረው የጎንደር ከተማ ነዋሪ ስትሆን በመንገድ ዳር የጀበና ቡና በመሸጥ ራሷን እና ሁለት ልጆቿን ታስተዳድራለች። "በምትሰራበት አካባቢ ወሃ የሚገኘው በአስር ወይም በአስራ አንድ ጊዜ ነው" ትላለች። የአቅርቦት ችግሩ ንጽህና የሚጠይቀውን ሥራዋን እያስተጓጎለባት እንደሚገኝም ትናገራለች።

ይህ ችግር የገነት ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ነዋሪ መሆኑን የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ታዝቧል። ከ750 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ያሏት ጎንደር ከ9 የተለያዩ ተቋማት ውሃ ታገኛለች። በቀን 13,322 አምርታ ለነዋሪዎቿ ማከፋፈል ብትችልም ከፍላጎቱ አንጻር ማዳረስ የቻለችው 22 በመቶውን ብቻ ነው።

ከ1994 ዓ.ም  ጀምሮ ከአገልግሎት የሰጠው አንገረብ ግድብ በደለል በመሞላቱ ውሃ ማምረት አቅሙ እየቀነሰ መጧል። ግድቡን መልሶ ወደ አገልግሎት ለማስገባት 3 ሚልዮን ኪ.ሜ. የሚጠጋ ደለል ማስወገድ ግዴታ እንደሆነ የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ ወርቅነህ አያል። ለሥራው 216 ሚልዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል። በከተማ አስተዳደሩ ጥረት 50 በመቶውን ማስወገድ መቻሉንም ኃላፊው ተናግረዋል።

በከተማው ወሃ አገልግሎት በኩል የጣና ሀይቅ ውሃን "ከቆላድባ ፕሮጀክት" ጋር በማገናኘት ለመጠጥ ውሃ እንዲውል የማድረግ ሙከራም የጎንደር ከተማን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ከተካሄዱ ጥረቶች መካከል ይገኝበታል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በ127.5 ሚልዮን ብር የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ በመካሄድ ላይ ስለመሆኑ የጎንደር ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት መረጃ ያሳያል።

በተመሳሳይ የክልሉ መናገሻ የሆነችው ባህር ዳር ዓባይ እና ጣናን ተንተርሳ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የሚቸግራት ከተማ ናት። በተማዋ 28 የውሃ ተቋማት ይገኛሉ። ከተቋማቱ በቀን 30 ሚሊዮን ሊትር ውሃ ይመረታል። ይሁን እንጂ ከ350 ሺህ በላይ ህዝብ ለሚኖርባት ባህርዳር በቂ አይደለም። መሸፈን የተቻለው የፍላጎቱን 50 በመቶ ብቻ ነው።

አቶ ይርጋ አለሙ የከተማዋ ወሃ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ናቸው። ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለነዋሪው ለማዳረስ በየ4 ቀን ልዩነት ውሃ እያዳረሱ እንደሚገኝ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ሥራ አስኪያጁ ይህንን ይበሉ እንጂ በከተማዋ የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ይታገሱ ውሃ የሚያገኙት በሳምንት አንድ ቀን እንደሆነ ይናገራሉ። “ውሃ የሚመጣልን በሳምንት አንድ ቀን ነው። እሱንም ልናጣ የምንችልበት አጋጣሚ አለ” የሚሉት ነዋሪው “በአካባቢያችን የሚገኙ የመኪና ማጠቢያዎች ውሃውን በማሽን እየሳቡ መጠቀማቸው እጥረቱን የበለጠ አባብሶታል” ብለዋል።

የውሃ አገልግሎት ሥራ አስኪያጁ በመኪና ማጠቢያዎች ላይ የተነሳውን ቅሬታ አስመልክተው በሰጡት ምላሽ “ችግሩን በመገንዘብ ፈቃድ እንዳይሰጥ አግደናል” ብለዋል። ካሳለፍነው 2 ዓመት ጀምሮ አዲስ ፈቃድ እንዳይሰጥ ቢታገድም፤ ቀድመው ሥራ የጀመሩትን ማስቆም አስቸጋሪ እንደሆነባቸውም አክለዋል። “ሥራው ወጣቶች ተደራጅተው በሥራ ፈጠራ መልክ ብድር ወስደው የሚሰሩት በመሆኑ የጀመሩትን ማስቆም አንችልም” የሚሉት ሥራ አስኪያጁ ከዚህ በኋላ በከተማዋ በመኪና እጥበት የመሰማራት ፍላጎት ያለው አካል የውሃ ጉድጓድ ማስቆፈር እንደሚጠበቅበት አስምረውበታል።

በስድስት ክፍለ ከተሞች በተከፋፈለችው ባህር ዳር የግንባታ ሥራዎች ለውሃ እጥረቱ ምክንያት ስለመሆናቸው ጥቂት የማይባሉ ነዋሪዎች ያነሳሉ። የውሃ አገልግሎት ሥራ አስኪያጁም የነዋሪዎችን ቅሬታ ይጋራሉ። እንደ አቶ ይርጋ አለሙ ገለፃ በበዓላት ሰሞን ግንባታ ስለማይከናወን የውሃ እጥረት እንደማይኖር አንስተዋል። በግል እና በመንግሥት ተቋማት አማካኝነት በከተማዋ እየተካሄዱ የሚገኙ ግዙፍ ግንባታ ፕሮጀክቶች የራሳቸውን የውሃ አማራጭ ቢጠቀሙ ለእጥረቱ መሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመው ለተግባራዊነቱ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የክልሉ ደማቅ ከተማ ደሴ አንደ ሌሎች የከልሉ ከተሞች ሁሉ የውሃ ችግር እንደሚስተዋል ነዋሪዎች ይናገራሉ። የደሴ ውሃና ፍሻስ አገልግሎት ስራአስኪያጅ አቶ ወርቁ አሞኘ "በከተማዋ በቀን የሚመረተው ንጹህ የመጠጥ ውሃ 8,000 ሚ.ኩ ብቻ ነው። ይህም የከተማዋን 40 በመቶ ፍላጎት ብቻ ይሸፍናል” ይላሉ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ውሃ እና ፍሳሽ ጽ/ቤት ስራአስኪያጅ አቶ ወርቅነህ አሞኘ የከተማዋን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት ከአራት ዓመት በፊት ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የማስፋፋያ ስራ ጀምሮ በበጀት እጥረት ምክንያት መቋረጡን ነግረውናል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት የደረሰው ውድመትና ዘረፋም ለችግሩ መባባስ የራሱን ከፍ ያለ ሚና ስለመጫወቱ ዘርዝረዋል። እንደ አቶ ወርቅነህ ማብራሪያ የጎንደር ከተማ የውሃ ሽፋን ከሌሎች አቻ ከተሞች አንጻር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ ነው።

የውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ለባህር ዳር ከተማ በ165 ሚሊዮን ብር እየተሰራ መሆኑን ያስረዱት አቶ ይርጋ አለሙ  “የውሃ ማስፋፊያ ግንባታዎች በቂ አደሉም” ብለዋል።

እንደ ክልሉ መረጃ የከተሞች አማካኝ የውሃ ሽፋን 67 በመቶ ሲሆን የእነዚህ ሦስት ከተሞች (ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ) ሽፋን ከአማካኙ ያነሰ ነው። የሦስቱ ከተሞች ውሃ አገልግሎት ጽ/ቤቶች ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባባር እየሰሩ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

የአማራ ክልል አጠቃላይ የውሃ ሽፋን 69.4 በመቶ ነው፡፡ የገጠር ሽፋን 69.8፣ የከተማ 67 በመቶ መሆኑን የክልሉ የውሃ እና ኢነርጅ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አደም ወርቁ ሳልህ ያስረዳሉ። እንደ ኃላፊው ማብራሪያ የክልሉን የውሃ ሽፋን በሂደት ለማሳደግ እየተሰራ ሲሆን "በአስር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ሽፋኑን መቶ በመቶ ለማድረስ ታቅዷል። ቢሮው የክልሉን የውሃ ሽፋን ለማሳደግ በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ 3.5 ቢልዮን ብር መድቦ እየተሰራ ይገኛል።”

የክልሉ የውሃ እና ኢነርጅ ቢሮ እንደሚለው የውሃ አግልግሎት ስራ በባህሪው ከሌላ ተቋም ጋር በጋራ የሚሰራ ነው። የኤሌትሪክ ኃይል የሚሻ በመሆኑ የኃይል አቅርቦቱም አብሮ ማደግ እንዳለበት የህዝብ ግንኙነቱ ነግረውናል።

“ሦስቱ ሜትሮፖሊታንት ከተሞች በራሰቸው በጀት የሚተዳደሩ በመሆናቸው በራሰቸው አቅም የውሃ አግልግሎት ማስፋፊያ መገንባት ይጠበቅባቸዋል። ነግር ግን ክልሉ በርካታ ህዝብ የሚኖርባቸው ከተሞች በመሆናቸው ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል። ስለሆነም ክልሉ ከውሃ ሃብት ልማት ፈንድ ብድር የሚገኙበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛል” ያሉት አቶ አደም ወርቁ ሳልህ ናቸው። የከተማውን ነዋሪ የውሃ አቅርቦት እየተጋፉ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም የራሳቸውን የውሃ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ በማድረግ የመፍትሔ እርምጃው ስለመጀመሩ ነግረውናል።