የድሬደዋ ምድር ባቡር ለድሬደዋ ነዋሪ ሰዓት ነበር። ተማሪውም ሆነ ሰራተኛው መዘግየቱንና መፍጠኑን የሚቆጣጠረው በጅቦ ነበር። አንድ ተማሪ ጅቦ ሲጮህ ዘወትር የሚያከናውነው ተመሳሳይ ድርጊት ይኖራል። ድምጹ ከትውስታው ጋር አለ። የትምህርት ቤት የደንብ ልብሱን እየለበሰ ወይም እየተመገበ ሊሆን ይችላል። በአጋጣሚ ወይም በስንፍና ዘግይቶ የሰዓቱን ድምጽ ከሰማ (ጅቦ ከጮኸ) ፈፍዷል ማለት ነው። ምክንያቱም ጅቦ ሰዓቱን ዝንፍ አያደርግም። የመቶ ዓመታት እድሜ ያለው እና ለድሬደዋ ከተማ መመስረት ትልቅ ሚና ያለው "የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር" ከትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ በድሬደዋ ነዋሪ ልብ ውስጥ ተደላድሎ እንዲቀመጥ የሆነው የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤም በመቅረፅ ረገድ ትልቅ ሚና ስለነበረው እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
አቶ አንተነህ ሙሉጌታ “ጅቦ”ን ሲገልጽ “ሁላችንም እጅ ላይ ያለ ግን ያልገዛነው ሰዓታችን ነው” ይላል። ድሬደዋ ተወልዶ ያደገው አቶ አንተነህ “ሌሎች አካባቢ ብሄድ የማላገኘው፣ ሳልከፍለው ትልቅ ውለታ ነው የዋለልኝ ነው” ብሎታል። “ት/ቤት እሄድ የነበረው በጅቦ ታግዤ ነበር። አሁንም ስራ የምሄደው ጅቦ ቀስቅሶኝ ነው። በፊት ተማሪ እያለሁ የመጀመሪያ ዙር ሲጮህ ቁርስ የምበላበት ሰዓት ነበር። ለኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የድሬደዋ ተወላጆችና ልጅነታቸውን ድሬደዋ ለሚያሳልፉ ልጆች የምድር ባቡርን ሰዓት መጠቀም የተለመደ ነበር” ሲል ትውስታውን ያጋራል።
ጅቦ ስያሜውን እንዴትና መቼ እንዳገኘ በግልፅ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም በስፋት የድሬዳዋ ነዋሪ ጅቦ በሚለው ስያሜ እየተጠቀመ ይግባባበት ነበር።
የድሬዳዋ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት በሰራተኛ መግቢያና መውጫ፣ የምሳ ሰዓት መውጫ እና መግቢያ ላይ ይጮሀል። የሚጮህባቸው ሰዓቶች ጠዋት ለአንድ እሩብ ጉዳይ ሰራተኞች እንዲገቡ፣ ሰራተኞች ስራ እንዲጀምሩ አንድ ሰዓት፣ የሰራተኛ ከስራ መውጫ ስድስት ሰዓት፣ ወደ ስራ መመለሻ ለዘጠኝ እሩብ ጉዳይ፣ ሰራተኞች ስራ እንዲጀምሩ ዘጠኝ ሰዓት እና ከስራ መውጫ ሰዓት አስራ አንድ ተኩል ናቸው። ይህ ሰዓት የሚዛነፈው የበበዓላት ቀናት ላይ ስለማይጮህ እንዲሁም ለጥምቀት ጊዜ ሰራተኛው እስከ ዘጠኝ ሰዓት ስለሚሰራ የ11፡30 አይጮህም ሌላው ደግሞ እሁድ ሰራተኛ ስራ ስለማይገባ አይጮህም፣ ቅዳሜ ደግሞ እስከ ስድስት ብቻ ነው የሚጮኸው። ከዚህ ሰዓት ውጪ ከጮኽ ግን በድርጅቱ አልያም በድሬደዋ ችግር እንዳለ ነው የሚታሰበው።
ከአርባ ዓመታት በላይ በድሬደዋ ነዋሪ ዘንድ “ጅቦ” እየተባለ የሚጠራውን የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር “አቴሌ” በሚባለው ክፍል ውስጥ የሚገኘውን ደውል የሚደውሉት (የሚያስጮሁት) አቶ ሀሰን ሙሳ ናቸው። “ደውሉ መጮህ የጀመረው እ.ኤ.አ በ1975 ዓ.ም ነው” ይላሉ። ጊዜው የጡረታ ዘመናቸው ስለነበር በስራ ትጋታቸው ምክንያት ከጡረታ በኋላ ወደ ሥራ ሲመለሱ ደውሉን የማስጮህ ኃላፊነት ተሰጣቸው። አቶ ሀሰን በዚህ ስራ ላይ በመሰማራታቸው ለሰዓት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ ምክንያቱም “ጅቦ” በሰዓት ድርድር አያውቅም።
በአቴሌ ክፍል ውስጥ የኤሌትሪክ ክፍል ሰራተኛ በመሆን ያገለገሉት አቶ አበበ አግደው ከ33 ዓመት በላይ በዚህ ክፍል አገልግለዋል። አቶ አበበ “ደውሉ ስምንት አፎች አሉት። የተከፈቱት የተወሰኑት ብቻ ናቸው። ሁሉም ቢከፈት የድምፁ ጥራት ላይ ችግር ስለሚፈጥር ሁሉም አይከፈትም” ያሉ ሲሆን፤ ደውሉ በድፍን ከተማዋ እንደሚሰማና በረዥም ዓመታት አገልግሎቱ ጥራቱ ያልቀነሰ ውድ ንብረት ስለመሆኑ ነግረውናል።
"ጅቦ" በድሬደዋ ኢትዮ-ምድር ባቡር ግቢ ውስጥ አተሌ በሚባለው ክፍል ውስጥ ይገኛል። ይህ ሰአት የሚጮኸው ሰራተኛ የሚገባበትና ስራ የሚጀምርበት ሰዓት ነው። አብዛኛው የድሬዳዋ ነዋሪ ምድር ባቡር ሰራተኞች እንዳያረፍዱ ለማድረግ መጮህ እንደጀመረ ሲናገሩ ይደመጣል።
ከ38 ዓመታት በላይ በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር እያገለገለ የሚገኘው አቶ ዓይነኩሉ ልመንህ በአተሌ ክፍል ውስጥ የሞተር ጥገና ሰራተኛ ነው። እንደ አቶ ዓይነኩሉ ገለፃ ደውሉ በሰራተኛው መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ቢጮህም በድርጅቱ ውስጥ አንድ ችግር ቢፈጠርም ነዋሪውን ለማንቃት አገልግሎት ላይ ይውላል። ዓይነኩሉ ነገሩን በምሳሌ ሲያስረዳ በ1969 ዓ.ም. የተፈጠረውን ያነሳል። “ወቅቱ በሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል ጦርነት የነበረበት ነው። በየአካባቢው ምሽግ ተሰርቶ ነበር። ምድር ባቡር ግቢ ውስጥም “ጅቦ” የሚጮህበት የአተሌ ክፍል አካባቢም ምሽግ ነበር። ታዲያ በወቅቱ ሰራተኛውንና የአካባቢውን ነዋሪ ከአደጋ ለመጠበቅ ሲባል ለህብረተሰቡ ጅቦ ያለሰዓቱ ከጮኸ ችግር አለ ማለት ነው ስለዚህ ወደምሽጎቻችሁ ትገባላችሁ ተብሎ መልእክት ተላልፎ ነበር” ሲል ታሪክ ያጣቅሳል።
አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ጋር በየብስ ትራንስፖርት ለማገናኘት ሲያቅዱ በሁለቱ ሀገራት መሀከል እንደ አማካኝ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ቦታ በአውሮፒያኖቹ ይጠቆማሉ። ንጉሱም ጥቆማውን ተቀብለው ከጅቡቲ ተነስቶ አዲስ አበባ የሚደርሰው የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ ይከናወናል። በ1895 ዓ.ም. ታህሳስ 14 ምሽት ሁለት ሰዓት የመጀመሪያው ባቡር ከጅቡቲ በመነሳት በርካታ በረሀማና ሞቃታማ አካባቢዎችን አቋርጦ ድሬደዋ እንደገባ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ይህ አጋጣሚ ለድሬደዋ መወለድ ምክኒያት ሆነ። የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ከማኅበራዊ መስተጋብሩ ባሻገር የሀገሪቱ ኢኮኖሚና የንግድ ልውውጥ የጀርባ አጥንት ሆኖ ቆይቷል። በአሁኑ ሰዓት ባቡሩ ከድሬደዋ ደወሌ እስከ ጅቡቲም ጉዞ ያደርጋል። አራት ሺህ የነበረው የድሬደዋ ምድር ባቡር ሰራተኛ በአሁን ሰዓት አራት መቶ ሀያ አምስት ደርሷል።
የእጅ ሰዓት በሁሉም ሰው የማይደፈር ውድ እቃ በነበረበት በቀደመው ጊዜ አብዛኛው የድሬደዋ ነዋሪ “ጅቦን” ተጠቅሟል። በማንቂያ ደውሉም መዘግየት መፍጠኑን ለክቷል። ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ለከተማዋ ህዝብ ሰዓት እየነገረ ይገኛል።