የካቲት 16 ፣ 2014

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ይዞት የመጣው አዲስ ነገር

City: Addis Ababaዜናንግድ

ኩባንያው በአዲስ አበባ የገነባውን ዘመናዊ የዳታ ማዕከል በትላንትናው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን አስጎብኝቷል።

Avatar: Solomon Yimer
ሰለሞን ይመር

Solomon is a content editor at Addis Zeybe. He has worked in print and web journalism for six years.

 ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ይዞት የመጣው አዲስ ነገር
Camera Icon

Credit: Solomon Yimer

በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የቴሌኮም ፈቃድ አግኝቶ ወደ ገበያው የገባው የኬኒያው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር የሚያስችለውን የመጀመሪያ ዙር የኔትዎርክ ዝርጋታና የመረጃ ቋት ግንባታ ማጠናቀቁንና ከፊታችን ሚያዝያ ጀምሮ የተመረጡ የቴሌኮም አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚጀምር አስታውቋል።

ኩባንያው በአዲስ አበባ የገነባውን ዘመናዊ የዳታ ማዕከል በትላንትናው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን አስጎብኝቷል። የኩባንያው ኃላፊዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እጅግ ዘመናዊ የዳታ ማዕከል መሳሪያዎች ከቻይና እና አውሮፓ ማስመጣታቸውን፣ በአዲስ አበባ በርካታ የሞባይል ኔትወርክ አንቴናዎች በሕንፃ ጣሪያዎች ላይ እየተከሉ መሆኑን ገልፀዋል።

ሳፋሪኮም አገልግሎቱን በ07 የመነሻ ቁጥር የሚያቀርብ ሲሆን። የድምጽ፣ የአጭር መልእክት፣ የቪዲዮ ጥሪ እንዲሁም የዳታ አገልግሎቶቹን በሙከራ ደረጃ መስራታቸውን በጉብኝቱ ወቅት አሳይቷል። በአዲስ አበባ የሚጀምረው አገለግሎት በመቀጠል በባህርዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ በኮምቦልቻ፣ በሀረር፣ በድሬዳዋና በጅግጅጋ ከተሞች እንደሚያስፋፋ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

መሰረተ ልማቶች ከኢትዮ ቴሌኮም በመከራዬት እንዲሁም የራሱን በመገንባት ስራውን ለመከወን ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ኩባንያው የኢትዮ ቴሌኮምን የቴሌኮሙንኬሽን መሰረተ ልማቶች ለመጠቀም የሚያስችል ድርድር መጀመሩን በድርጅቱ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ኦፊሰሩ ፔድሮ ራባካል ተናግረዋል።

እስካሁን ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለቁሳቁስ ግዥ ከ300 ሚሊያን ዶላር በላይ ያወጣው ሳፋሪኮም በቀጣይ አስር ዓመታት ውሰጥ በኢትዮጵያ 8.5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መዋዕለ ነዋይ ኢንቨስት ያደርጋል ተብሏል።

የታዋቂው የቴሌኮም ኩባንያ ቮዳኮም ቤተሰብ የሆነው ሳፋሪኮም ከሚሰጠው መደበኛ የቴሌኮም አገለግሎቶች በተጨማሪ በተከታታይ በሀገሪቱ የዲጂታል ዘርፍ የጎላ ሚና ይኖራቸዋል የተባለላቸውን በፋይናንስ፣ በትምህርት፣ በጤና በግብርና፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች በርካታ አገልገሎቶችን ለመስጠት ማቀዱ ተነግሯል።

ኩባንያኛው በአሁኑ ሰዓት 200 ኢትዮጵያውያንን ቀጥሮ እያሰራ የሚገኘ ሲሆን በዓመቱ መጨረሻ እስክ 1,000 የሚሆኑ አዳዲስ ሰራተኞች ኩባንያውን ይቀላቀላሉ ተብሏል። በተመሳሳይ ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ይፈጥራቸዋል በተባሉ የተለያዩ የዘርፉ ዕድሎች በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ ለ1.6 ሚሊየን ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሳፋሪኮም ከሳይበር ደህንነት አንጻር ምን ያህል አስተማማኝ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ፔድሮ ሲያብራሩ በዓለም ላይ በአሁኑ ሰዓት አለ የተባለውን አሰተማማኝ የዲጂታል ሴኩሪቲ ሲስተም እንደሚጠቀምና ይህም የደንበኞችንም ሆነ አጠቃላይ የተቋሙን መረጃዎች በአስተማማኘ መልኩ ለመያዝ እንደሚያስችለው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደንበኞች ከአንዱ የቴሌኮም ድርጅት ደንበኝነት ወደ ሌላኛው መቀየር የሚችሉበትን ቴክኖሎጂ የመተግበር የረጅም ጊዜ ዕቅድ እንዳለው ተገልጾአል። የቴክኖሎጂው አቅም ሲፈቅድ  ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገርና የሚከወን ይሆናል ተብሏል።

አሁን ላይ ባለው የኃይል፣ የደህንነት አንዲሁም የማቀዝቅዣ አቅም አንጻር ታየር 3 የተባለውን የመረጃ ቋት ደረጃ በጠበቀ መልኩ መገንባቱን የገለጹት የቴክኖሎጂ ኦፊሰሩ በመረጃ ቋቱ ግንባታም ሆነ በሌሎች የተቋሙ የኔትወርክ ዝርጋታ ላይ በመላው ዓለም የሚገኙ ከ200 በላይ የቴክኖሎጂ መሀንዲሶች በቀጥታ እየተሳተፉ እንደሚገኝና ሳፋሪኮም ወደፊት አገልግሎቱን ዘመኑ በሚፈልገው ደረጃ በፍጥነት እያሳደገ እንደሚሄድ ገልጸዋል። 

የቴሌኮም ተቋሙ በቀጣይ ዓመታት በደንበኞቹ ፍላጎት ላይ በመመስረት በርካታ የቴሌኮም አገልግሎቶችን ለደንበኞች የሚያቀርብ ሲሆን ለዚህም እንደ አፕል፣ ጉግጉግ፣ ሳምሰንግ ከተሰኙትና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን ተቋማትና ባለሙያዎች ጋር በመሆን እሰራለሁ ብሏል።

በፈረንጆቹ 2023 ዓ.ም. 25 ከመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ህዝብ ለማዳረስ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሳፋሪኮም በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባና በአዳማ የገነባቸው የመረጃ ቋቶች እያንዳነዳቸው እስክ 10 ሚሊየን ደንበኖችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ሲሆን ኩባንያው በቀጣይ ተመሳሳይ ማዕከላትን በዘጠኝ ከተሞች እንደሚተክል ታውቋል።

ዋና መሥሪያ ቤቱ ናይሮቢ የሚገኘው ሳፋሪኮም የኬንያ የቴሌኮም ድርጅት ሲሆን፤ ኬንያ ውስጥ ትልቁ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢና በምሥራቅ እና በመካከለኛው አፍሪካ ትርፋማ ከሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።

አስተያየት