የዳውሮ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት አስተዳደራዊ መዋቅር ስር ከሚገኙ 6 ዞኖች መካከል አንዱ ነው። ከአዲስ አበባ በሻሸመኔ ወላይታ ሶዶ 455 ኪ.ሜ. ከአዲስ አበባ በጅማ 479 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል። ዳውሮ በደቡብ በጋሞ ጎፋ ዞን፣ በምዕራብ በኮንታ ልዩ ወረዳ፣ በሰሜን በጎጀብ ወንዝ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከጅማ ዞን፣ በሰሜን ምስራቅ ከሀዲያ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች ጋር፣ በምስራቅ በወላይታ ዞን ያዋስኗታል።
የንጉሥ ሃላላ ድንጋይ ካብ (ሃላላ ኬላ) የተገነባበት ዋና ዓላማ ዳውሮን ከውጪ ወራሪ ኃይል ፈረሰኛና እግረኛ ጦር ለመከላከል እንደሆነ ይነገራል። የድንጋይ ካቡ የጠላት መግቢያና መውጫ እንደሚሆኑ በሚገመቱ አካባቢዎች የጦር በሮች (tooraa miis’aa) በማዘጋጀት፣ በእያንዳንዱ የጦር በር ጠባቂ ሹም (Miis’aa Iraasha) ሹመት በመስጠት፣ የግዛት ወሰንና የህዝብ ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሆነ የታሪክ ባለሙያው ዶ/ር አድማሱ አበበ ያስረዳሉ።
(Kawo Halalaa Keelaa) የካዎ ሃላላ ድንጋይ ካብ (ኬላ) መገኛ አሁን ደቡብ ብሔሮችና ብሔርሰቦች ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት በዳውሮ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የጎፋ ዞን ማሎ ኮዛ ወሰን ጀምሮ ነው ኦሞ ወንዝን ተከትሎ ነው። ከዳውሮ ዞን ወረዳዎች መካከል ኢሠራ፣ ዲሳ፣ ሎማ፣ ዛባ ጋዞ፣ ጌና፣ ታርጫ ከተማ አስ/ርና ታርጫ ዙሪያ ወርዳዎችን በማካለል ጋሞ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ከምባታ ጣንባሮ፣ ጅማ ዞኖንና ኮንታ ልዩ ወረዳ መሻገሪያ ድንበሮችን ያካለለ ታሪካዊ የዳውሮ ንጉሥ ጥንታዊ የኪነ-ሕንፃ ግንባታ ጥበብና የዳውሮ ህዝብ የጥንካሬ መገለጫ ነው። ከ1532 እስከ 1822 ዓ.ም. በሐገር በቀል ዕውቀት የተገነባ እንደሆነ የዳዉሮ ዞን የባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳኢሞ ደስታ ይናገራሉ።
“ሃላላ” የዳውሮ ንጉሥ መጠሪያ ሲሆን፤ “ኬላ” የሚለው የድንጋይ ካብ (የመከላከያ ካብ) የሚል ትርጓሜ አለው። ካዎ ሃላላ ድንጋይ ካብ (ሀላላ ኬላ) በአንድ ረድፍ 175 ኪ.ሜ. እና አጠቃለይ ርዝመት በሰባት ረድፍ 1225 ኪ.ሜ. ይሸፍናል። ከ2.5 እስከ 5 ሜትር ስፋትና ከ2.5 እስከ 3.8 ሜትር በላይ ከፍታ አለው። በዳውሮ ዞን ባህል፣ ቱርዝምና ስፖርት መምሪያ የቱሪስት መስህብ ጥናት ልማትና ግብይት መረጃ ዕንደሚያሳየው በውበቱ አግራሞትን የሚፈጥረው ኪነ-ሕንጻ የዳውሮ ህዝቦችን ጥንታዊ ስልጣኔ የሚያሳይ ነው።
በግንባታዉ ሂደት 350 ዓመታት የፈጀ ሲሆን ከ15ኛው እስከ 18ኛው ክ/ዘመን ዳውሮ ዞንን ያስተዳድሩ የነበሩ 14 ነገሥታት በቅብብሎሽ የገነቡት እንደሆነ ኃይሉ ዘለቀ "some notes on the great walls of wolayta and dawro" በሚል መፃጽሐፉ አስቀምጧል። ከቻይናው ‘ግሬት ዎል’ እና ከፐርሺያው ‘ባቢሎን’ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የድንጋይ ካብ አፍሪካ ውስጥ መኖሩ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን ሰፋ ላለ ጥናት የሚጋብዝ ስለመሆኑ ባለሙያው ተናግረዋል።
ዶ/ር አድማሱ አበበ በሀላላ ኬላ የካብ ድንጋይ ላይ ያደረገውን ባካሄዱት ጥናት በሀላላ ኬላ ክብ ድንጋይ ዙሪያ ባደረገው ምርምር እና ጥናት ትርጓሜውን የጥበቃ በር አልያም በእዛን ወቅት የነበረው የድንበር አጠባበቅ ስርዓት የሚያስቀኝ እንደሆነ አንስተዋል። ሀገር በቀል ጥበባዊ የግንብ አሰራር የተላበሰው እና ምንም ዓይነት የሲምንቶ ወይም ዘመናዊ የእንፃ ጥበብ ያላረፈበት የሦስት ትውልድ እድሜ ባፀጋ ነው።
የዳውሮ ዞን የባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳኢሞ ደስታ ጥንታዊ ቅርሱ የብሄሩ የማንነት መገለጫ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ስለመሆኑ ተናግረዋል። “የካብ ድንጋዩ እንደ ቱሪዝም መመሪያ የማስታወቂያ ስራ እና የዶክመንተሪ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በቂ አይደለም” የሚል ሀሳብ ያነሳሉ።
"ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል /UNESCO/ መዝገብ ላይ የሰፈሩ እና በዓለም ቅርስነት እውቅና ለማግኘት የሚጠባበቁ ቅርሶች እንዳሏት ይታወቃል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የዳውሮ ህዝብ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየው እና ከ400 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የንጉሥ ሀላላ ኬላ የድንጋይ ካብ ተጠቃሽ ነው። ነገር ግን አልፎ አልፎ ተፈጥራዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ቢጋረጡበትም እንደ ቱሪዝም መምሪያ ከፌደራል መንግስት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር የቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለስልጣናት ጋር በመተባበር የተለያዩ ጥናቶችን የማካሄድ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ"
በ1368-1644 በሚንግ ስርወ መንግስት የተገነብት ታላቁ የቻይና ጥንታዊ የድንበር ግድግዳዎች በዳውሮ ዞን ከሚገኘው ንጉስ ሀላላ ኬላ ካብ ድንጋይ ጋር ተመሳሳይነት እንደሚኖረውም ጥናቶች ይጠቁማሉ።
“ከ1532 ዓ.ም. ግንባታው ተጀምሮ 1782-1822 ዓ.ም. ዳውሮን በንጉሥነት ይመሩ የነበሩ ንጉሥ ሀላላ የድንጋይ ካብ እንዲጠናቀቅ በማድረጋቸው በስማቸው እንዲሰየም የተደረገው የድንጋይ ካብ የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ አደጋ አልፎ አልፎ ማስተናገዱ ትኩረት እንዲደረግበት ያመላክታል” ይላሉ። የቱሪዝሙ ባለሞያ አቶ ዳኢሞ ደስታ።
ንጉስ ሀላላ ኬላ ስልጣንን በግል ጠቅልሎ ከመያዝ ልማድ በመውጣት አዳዲስ የአመራር ስልቶችን ማሳየት የቻሉ መሪ እንደነበሩ ይነገራል። በተለይም ስልጣንን ለህዝብ በማካፈልና በየደረጃው በማውረድ ህዝባዊ አገዛዝን መመስረቱ ላይ የተዋጣላቸው እንደሆኑ የህዝብ አንድነትን እንደሚጠይቁ የሚያሳዩት የታሪክ ቅርሶች ምስክሮች ናቸው።
ድንጋይ በድንጋይ ላይ በማነባበር ግዙፍ አለቶችን የያዘው እና ያልተወራለት ረዥም ግንብ በመገንባት ለታሪክ ማኖር የቻሉት ቀደምት የዳውሮ ነገስታት ጥለውት ያለፉት ቅርስ ወደ ገንዘብ ሊቀየር፣ ሊጎበኝና የውጪ ምንዛሪ ሊያስገኝ የሚያስችል የቱሪዝም ሃብት እንደሆነ ይታመንበታል።
በ“ድንቁ ዲንኬ” የሙዚቃ መሳሪያ እያጫወቱ እንግዳን ማስተናገድ እንደሚችሉ የሚነገርላቸው የዳውሮ ህዝቦች ማእከል የሚገኘው ካብ ጎብኚዎች በመሳብ እረገድ በማህበረሰብ ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አሁን ላይ እየተሰራ እንደሆነ የነገሩን የዳውሮ ዞን የባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳኢሞ ደስታ ናቸው። "በፌደራል መንግስቱ እና በክልል ቅርሱን የማስተዋወቅ ሂደት በተወሰነ ጀረጃ ቢሆንም ሊሰራበት እና ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ የኢትዮጵያ ቅርስ ነው" ሲሉ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
የዳውሮ ህዝቦች የኪነ-ጥበብ ሥራ ውጤት የሆነው ካዎ ሃላላ ድንጋይ ካብ (ሃላላ ኬላ) ታሪካዊ ቅርስ በግቤ ሦስት 1870 ሜጋ ዋት ኤሌክትርክ ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ሐይቅ አጠገብ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አንዱ አካል በሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት ሃላላ ክላስተር መገኛ ቦታ ነው። ከቱሪስት መዳረሻነት ባሻገር ለአዲሱ ትውልድ ታሪካዊ አሻራና የጥንካሬ መገለጫ በመሆን የሚያበረክተው አሰተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ በዳውሮ ዞን ባህል፣ ቱርዝምና ስፖርት መምሪያ በቱሪስት መስህብ ጥናት ልማትና ግብይት መረጃ ያሳያል።