ከ13 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ አካውንት፣ “ከትግራይ የተዘረፉ ቅርሶች ለአለም ገበያ በዚህ አይነት ሁኔታ እየተቸበቸቡ ነው።” የሚል ጽሁፍ በማያያዝ africanews.com ወደተባለ ድረ-ገጽ የሚመራ ሊንክ አጋርቷል።
Africanews.com የተባለው ይህ ድረ-ገጽ በየካቲት 7 ፤ 2014 ዓ.ም “Tigray conflict surge in ancient ethiopian relics for sale.” የሚል ርዕስ ያለውን አንድ ቪድዮ አውጥቶ ነበር።
ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የፌስቡክ ፖስቱ ከ200 በላይ ግብረመልስ ያገኘ ሲሆን ከ90 ጊዜ በላይ ደግሞ መጋራት ችሏል። ይሁን እንጂ ሀቅቼክ ባደረገው ማጣራት መሰረት ቪድዮው ከትግራይ ክልል ተዘርፈው በኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ድረ-ገጽ ላይ ለሽያጭ የቀረቡ ቅርሶችን እንደማያሳይ አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ የፌስቡክ ፖስቱን ለመደገፍ የቀረበውን ቪድዮ ትክክለኛነት መርምሮ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።
ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሓት) እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተከሰተው ግጭት ከአንድ አመት በላይ አሳልፏል።
በጦርነቱ ወቅት በተለያዩ አጋጣሚዎች እና ወቅቶች ትላልቅ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ለውድመት የተዳረጉ ሲሆን የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስትም በጦርነቱ ምክንያት ለወደሙት እድሜ ጠገብ እና ጥንታዊ መስጊዶችን እንዲሁም ቤተክርስትያኖችን ለመጠገን እና ወደቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ ቃል ገብቷል።
የእንግሊዙ ጋዜጣ The independent እንደዘገበውነ e-bay የተባለው የመገበያያ ድረ-ገጽን ጨምሮ በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ከቤተ-ክርስትያኖች የተዘረፉ እንደሆኑ የሚገመቱ ቅርሶች ለሽያጭ እየቀረቡ እንደሆነ ዘግቧል።
E-bay የተባለው የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ድረ-ገጽ ለሽያጭ ቀርበው የነበሩ አንዳንድ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶችን ከገጹ ላይ ያወረደ ቢሆንም አሁንም ድረስ አንዳንድ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ የሆኑ ቅርሶች በዚህ ድረ-ገጽ ላይ ለሽያጭ ቀርበው ይገኛሉ።
Africanews.com የተባለው ድረ-ገጽ ባያያዘው ቪድዮ ላይ “ከአንድ አመት በላይ በፈጀው ጦርነት ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ቅርሶች መካከል ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠሩ የብራና ላይ ጽሁፎች በጥቂት ዶላሮች ዋጋ በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ እየቀረቡ ነው” በማለት ይናገራል።
እነዚህ ለሽያጭ የቀረቡት ቅርሶች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የተዘረፉ ቅርሶች ሊሆኑ እንደሚችሉም ይህ የዜና ድረ-ገጽ ይዘግባል።
ሀቅቼክ የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት ባደረገው ጥረት በፌስቡክ ፖስቱ ላይ የተያያዘው ቪድዮ ለመጀመርያ ጊዜ የታተመው በህዳር 14 ፤ 2014 ዓ.ም ከ4.5 ሚልዮን በላይ ተከታይ ባለው አንድ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ነበር።
ይህ የዩቲዩብ ቪድዮም “ተዘርፈው የነበሩ 13 ጥንታዊ ቅርሶች ከ150 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።” የሚል ርዕስ የቀረበ ነበር።
ይህ ጽሁፍ ለንባብ እስከበቃበት ጊዜ ድረስ ይህ ቪድዮ ከ5000 ጊዜ በላይ ታይቷል።
የተለያዩ ጥንታዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች በጦርነቱ ምክንያት ከትግራይ ክልል እንደተዘረፉ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም የፌስቡክ ፖስቱም ሆነ የድረ-ገጹ ቪድዮ መረጃውን አያረጋግጥም።
በዚህም መሰረት፣ መረጃውን ለመደገፍ ከፖስቱ ጋር የተያያዘውን ቪድዮ ሀቅቼክ ሀሰት ብሎታል።