ኤልሳቤጥ ዳንኤል ከመኖርያ ቤቷ በ6 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘው ሆጤ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ስትሆን የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነች። ከጦርነቱ በፊት በከተማዋ በሚገኙ 2 ቤተ-መጻሕፍት ትገለገል እንደነበር ታስታውሳለች። መሀል ከተማ ከሚገኘው የደሴ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት እና አየር ጤና ማኅበረሰብ አቀፍ ቤተ-መጻሕፍት እየተገኘች ታጠናለች። ተማሪዋ፤ የአየር ጤናውን በተ-መጻሕፍት የምታዘወትረው ለመኖርያ አካባቢዋ ቅርብ በመሆኑ እንደሆነ ትናገራለች። የ16 ዓመቷ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ኤልሳቤጥ “አሁን የትም አላነብም” ትላለች። ምክንያቷ በከተማዋ የነበሩት አንድ የግል እና አንድ የህዝብ ቤተ-መጻሕፍት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው ሙሉ ለሙሉ ወደ አገልግሎት ባለመመለሳቸው ነው።
ዋና ሳጅን ማማሩ ፍሬው በደሴ ከተማ ልዩ ስሙ አየር ጤና የሚባል አከባቢ የኮምዩኒቲ ፖሊሲንግ ኦፊሰር ናቸው። ከሥራ ባልደረባቸው እና ጓደኛቸው ሳጅን መሀመድ አደም ጋር በመሆን ቤተ-መጻሕፍት ያቋቋሙት በራሳቸው አነሳሽት ነበር። ቢሮው በበኩሉ የቢሮውን ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ነዋሪ እንዲያገለግል ለታቀደው ቤተ-መጻሕፍት አንድ ቢሮ፣ ወንበርና ጠረጴዛ በመፍቀድ አስተዋጽኦ አድርጓል።
“አከባቢያችን በርካታ ወጣት ተማሪዎች የሚገኙበት ነው። ወጣቶቹ ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በኋላ አጋዥ መጻሕፍትን የሚያገኙበት ዕድል ጠባብ ነው። ቤተ-መጻሕፍት ለማግኘት ቢያንስ 6 ኪ.ሜ. ያህል ከሰፈራቸው ይርቃሉ። ይህንን ስናስተውል እጃችን ላይ በሚገኝ ቁሳቁስ በመጠቀም ቤተ-መጻሕፍቱን ለማቋቋም ወሰንን። ራሳችን ከምንገዛው በተጨማሪ ሌሎች ተቋማትን በማስተባበር ቤተ-መጻሕፍቱን አቋቋምን” ብለዋል፤ ዋና ሳጅን ማማሩ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ቤተ-መጻሕፍቱ አጀማመር ሲናገሩ
"ቤተ-መጻሕፍቱን ስናቋቁም በርካቶች ሀሳባችንን አልተቀበሉትም ነበር። ምክንያቱም በደሴ ከተማ የሚገኙ የኮሚዩኒቲ ፖሊሶች የተሰጣቸውን ፖሊሳዊ ኃላፊነት ከመወጣት ባለፈ በእንደዚህ ዓይነት ማኅበረሰባዊ አገልግሎት ያላቸው ተሳትፎ አናሳ መሆኑን በማጤን ነው። ስለዚህ እኔና ሳጅን ማማሩ ይሄንን ሀሳብ ስናመጣ በተለይም በአካባቢያችን በወጣቶች የሚፈፀሙ ወንጀሎች እና ሱሰኝነት መበራከቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ ወጣቱ ውሎውን በማንበብ ቢያሳልፍ ከወንጀል ይርቃል ብለን በማመናችን ይሄንን ቤተ-መጻሕፍት በማቋቋም ወገናዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ ብለን በማሰባችን ነው" በማለት ሳጅን መሀመድ አደም ሀሳባቸውን አካፍለውናል።
ቤተ-መጻሕፍቱ በጦርነቱ ወቅት የጥቃት ዒላማ ከነበሩ ተቋማት መካከል አንዱ ስለመሆኑ፤ ለ5 ዓመታት የተሰባሰቡት ከ3 ሺህ በላይ ብዛት ያላቸው የህፃናት፣ ማጣቀሻ፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ በሁሉም የክፍል ደረጃዎች ያሉ መጻሕፍትና የተለያያ መጽሔትና ጋዜጣዎች ስለመዘረፋቸው፣ ስለመውደማቸው፤ በቀን ከ200 በላይ ተማሪዎችን ያስተናግድ የነበረው ቤተ-መጻሕፍት በተሰባበሩ የወንበርና ጠረጴዛ ቅሪቶች፣ በተቀዳደዱ እና በተቃጠሉ መጻሕፍት ስለ መሞላቱ በሀዘን የሚናገሩት ዋና ሳጅን ማማሩ “ቤተ-መጻሕፍቱ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል። ይጠቀሙበት የነበረው ተማሪዎች፣ የአካባቢው ነዋሪ ወጣቶች፣ የተቋሙ ሰራተኞች የመማማሪያ እና የመዝናኛ አማራጫቸውን ተነጥቀዋል” ይላሉ። እንደ ዋና ሳጅን ገለጻ የተሰባሰቡት መጻሕፍት ኮምፒውተሮቹን ጨምሮ ዋጋቸው ከግማሽ ሚልዮን ብር በላይ ይገመታል።
ቤተ-መጻሕፍቱ በመደበኛ ትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ከመርዳት ባሻገር ወንጀል እንዲቀንስ፣ የሱስ ተገዢነት እንዳይበራከት በማድረግ አማራጭ የጊዜ ማሳለፊያ ሆኖ እንደነበር ተነግሮለታል። ለመዝናኛና ለጠቅላላ እውቀት የሚያግዙ የታሪክ፣ የግለ ታሪክ፣ የልብወለድ፣ የግጥም መጻሕፍትን ጨምሮ ለመደበኛ ትምህርት አጋዥ የሆኑ መጻሕፍትም ከቤተ-መጻሕፍቱ ስብስቦች መካከል እንደነበሩ ተናግረዋል።
የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አቤል ጌታቸው “ሰፈራችን ላይብረሪ ስለነበረ ከህፃናት ጀምሮ አብዛኛው ተማሪ ለትምህርቱ የሚያግዘውን መጻሕፍት ብዙ ርቀት ሳይጓዝ በቅርበት በማግኘቱ ደስተኛ ነበር። እኔ በግሌ ይህ ላይብረሪ ከመከፈቱ በፊት አጋዥ መጻሕፍት ለማግኘት ብዙ መንገድ እጓዝ ነበር። ይህ ሁኔታ ደግሞ ብዙ የማንበብ ፍላጎቴን ቀንሶታል። በአካባቢዬ ሲሆን ከቤትህ ወጥተህ እዚሁ ላይብረሪ ትገባለህ። ወላጆችም የቅርብ ክትትል እነዲያደርጉ ይረዳቸዋል” የሚል ሐሳቡን ለአዲስ ዘይቤ አጋርቷል።
አቶ ሲሳይ በቀለ በደሴ የህዝብ ቤተ-መጻሕፍት ለ20 ዓመታት አገልግለዋል። የቤተ-መጻሕፍቱን ውድመት አስመልክቶ ሲናገሩ “እንደ ደሴ ቤተ-መጻሕፍት ያሉ ቤተ-ንባቦች መሀል ከተማ የሚገኙ በመሆናቸው እንደ አየር ጤና ማኅበረሰብ አቀፍ ቤተ-መጻሕፍት ዓይነቶቹ የተገልጋይን እንግልት የሚቀንሱ ነበሩ” ይላሉ። የተማሪዎችን እንግልት የሚቀንሰው ቤተ-መጻሕፍት በፍጥነት ወደ አገልግሎት እንዲገባ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል። የደሴ ዋናው ቤተ-መጻሕፍት በአነስተኛ ጥገና ሥራ ቢጀምርም በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ መሟላት የሚገባቸው ነገሮች በበጀት እጥረት ምክንያት እንደሚጎድሉ ነግረውናል።
የአየር ጤና የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ቤተ-መጻሕፍትን አገልግሎት ወደነበረበት ለመመለስ ወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ተቋማት ርብርብ እንዲያደርጉ ተጠይቋል።