የካቲት 12 ፣ 2014

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተነገረ

City: Addis Ababaዜና

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከነገ የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተነገረ።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተነገረ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከነገ የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተነገረ።

የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት መንግስት ባለስልጣናት ነግረውኛል ብሎ ባወጣው መረጃ ግድቡ የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ስራውን ይጀምራል ብሏል።

በተጨማሪም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በአረብኛ ቋንቋ የህዳሴው ግድብ ተሟጋች በመሆን የሚታወቀው መሀመድ አል አሩሲ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ፣ “ኢትዮጵያ በ24 ሰአት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከሀገራዊ ፕሮጀክቷ ዋነኛው ከሆነው የህዳሴ ግድብ የህዳሴዋን የመጀመሪያ ፍሬዎች ታጭዳለች” ሲል አስፍሯል።

4.2 ቢልየን ዶላር ወጪ የሚደረግበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ስራው ሲተናቀቅ ከ 5 ሺህ ሜጋዋት ኃይል በላይ ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ነገ በሚጀምረው የመጀመሪያ ኃይል ማመንጨት ስራ አቅሙ ምን ያህል እንደሆነ አልተገለፀም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከአንድ ሳምንት በፊት በዱባይ ከሚገኘው ከአልአረቢያ የቴሊቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት በተደጋጋሚ የተገለፀውን የኢትዮጵያ አቋም አንፀባርቀዋል። 

አምባሳደሩ እንደገለፁት፣ “የግድቡ መገንባት ግብፅን በድርቅ ወቅት እንኳ የውሃ ቋት ሆኖ የሚያገለግል ፕሮጀክት በመሆኑ ፕሮጀክቱን ልትደግፈው ይገባል” ብለዋል። በተጨማሪም ሱዳን በአነስተኛ ግድቦቿ ላይ ይደርስብኛል ብላ የምታነሳውን የደህንነት ስጋት በሚመለከት መደበኛ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል።

አምባሳደር ሬድዋን አክለውም “ሱዳን በአሁኑ ወቅት የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የሶስተኛ ወገን ጉዳይ አስፈፃሚ አየሆነች ነው” ሲሉ ለአል አረቢያ ገልፀዋል።

ለሳምንታት የኃይል ማመንጨት ሙከራ ስራ ላይ የነበረው ግድቡ ሙከራው በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ ነው በነገው እለት በይፋ ስራውን ይጀምራል የተባለው።

በዓለማችን ረጅሙ አባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ግድቡ በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም. በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ሳሊኒ በተባለው የጣልያን የግንባታ ኩባንያ ግንባታው የተጀመረ ሲሆን ፕሮጀክቱ 11ኛ ዓመቱን ሊደፍን አንድ ወር ቀርቶታል።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲወጠን ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አማካይነት ይሸፈናል መባሉን ተከትሎ በቦንድ ሽያጭ፣ ወርሐዊ ደሞዝ ተቆራጭ በማድረግ እና እንደ ህዳሴ ዋንጫ ያሉ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት በቢልየን የሚቆጠር ብር መሰብሰብ ተችሏል።

በርካታ ዙር የሶስትዮሽ ድርድር ያስተናገደው ግድቡ ግብፅ እና ሱዳን ገዳቢ ማዕቀፍ እንዲፈረም የሚፈልጉ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግድቡ ለቀጠናውና ተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ከመናገር ወደኋላ አላለችም።

አስተያየት