የካቲት 12 ፣ 2014

በትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች በስራ ላይ የነበሩ መምህራን ደሞዝ ስለተቋረጠባቸዉ ችግር ላይ መሆናቸውን ገለፁ

City: Addis Ababaዜና

ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመድባቸዉ ቢጠይቁም ምደባ እንዳልተደረገላቸዉ የሚገልጹት መምህራኑ ደሞዛቸዉ በመቋረጡ ምክኒያት ለከፋ ችግር መዳረጋቸዉን ገልጸዋል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች በስራ ላይ የነበሩ መምህራን ደሞዝ ስለተቋረጠባቸዉ ችግር ላይ መሆናቸውን ገለፁ
Camera Icon

ፎቶ፡ መሀበራዊ ሚድያ

በትግራይ ከልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ያስተምሩ የነበሩ መምህራን ደመወዝ እየተከፈላቸዉ አለመሆኑና በትምህርት ላይ የነበሩትም ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ ባለመመደባቸዉ ችግር እንደገጠማቸዉ ለአዲስ ዘይቤ ገለጹ። 

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት ላይ የነበሩ መምህራን ትምህርታቸዉን ቢያጠናቅቁም ያስተምሩባቸዉ የነበሩ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በጦርነቱ ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደት በማቋረጣቸው ወደ ዩኒቨርሲቲዎቹ መመለስ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመድባቸዉ ቢጠይቁም ምደባ እንዳልተደረገላቸዉ የሚገልጹት መምህራኑ ደሞዛቸዉ በመቋረጡ ምክኒያት ለከፋ ችግር መዳረጋቸዉን ገልጸዋል።

እዮብ ረታ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ሆኖ ለአንድ ዓመት ካገለገለ በኋላ የሁለትኛ ዲግሪ ትምህርቱን ለመማር ከነበረበት ዩኒቨርሲቲ ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ ተመድቦ በሕዳር ወር 2014 ዓ.ም. ተመርቋል።

የትምህርት እድሉን ያገኘበትና የሚያስተምርበት የነበረው አክሱም ዩኒቨርሲቲ ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከወርሃዊ ደሞዝ በተጨማሪ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ በመማር ላይ ለሚገኙ መምህራን የሚሰጠው የኪስ ገንዘብ የሚባለው (በወር ሁለት ሺህ ብር አካባቢ) ከተቋረጠ ስድስት ወራት ማለፋቸውን እዮብ ይናገራል።

ታዲያ በመጀመሪያ ይሰራበት የነበረው በትግራይ ክልል የሚገኘው የአክሱም ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደቱን በማቋረጡ ወደ ዩኒቨርሲቲው መመለስ አልቻለም። ሁለተኛ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ ከሁለት ሳምንታት ለሚበልጥ ጊዜ የትም ዩኒቨርሲቲ ሳይመደብ ያለስራ ቆይቷል። 

ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለተኛ ዲግሪዉን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ካገኘ በኋላ ከትምህርት ሚኒስቴር ወደሌላ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀጠሩ ብቻ ተነግሯቸዉ ያለ መፍትሄ መሰናባታቸዉ ይናገራሉ። 

በመቀጠልም የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን ትምህርት ክፍል ህዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ማስታወቂያ እሱን ጨምሮ ለሰባት መምህራን ስራ እንዲጀምሩ ጥሪ አድረጎላቸዉ በዩኒቨርሲቲ ማስተማር ቢጀምሩም አሁንም ወርሃዊ ደመውዝ ሳይከፈላቸዉ ሁለት ወራት ማለፋቸዉን ይናገራል።

“ይህ ነገር በእኔ ላይ ብቻ አይደለም፤ ከሰኔ እና ግንቦት ወራት 2013 ጀምሮ ከአክሱም፣ መቐለ እና አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በስራ ላይ የነበሩ እና በመንግስት አማካይነት በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ በመማር ላይ የሚገኙ የነበሩ መምህራን ደሞዝ መከፈል ካቆማቸው ወራት አልፈዋል” ብሏል እዮብ ።

መምህር እዮብ ረታ እና ሌሎች ባልደረቦቹ ጉዳይን ለማጣራት ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ከ20 ጊዜ በላይ ቢመላለሱም መፍትሄ አንዳላገኙ ይናገራሉ።

ሌላ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች መምህርትም ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ነበረች። የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት ሲቋረጥ እንደበርካቶች ለመሸሽ ስትል ወደ አዲስ አበባ መምጣቷን ትገልፃለች። “በሰላሙ ጊዜ በወር ሰባት ሺህ ብር ይከፈለኝ ነበር፤ ከዛ በኋላ የተፈጠረውን ሳላውቅ ሁለት ሺህ ብር ከህዳር 2014 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ደሞዝ ሳይከፈለኝ ቀረ” ትላለች።

አዲስ ዘይቤ መምህራኑ ችግራቸውን አቤት ያሉበትን የትምህርት ሚኒስቴር አንድ ዳይሬክተር የስልክ ጥሪም ሆን የፅሁፍ መልዕክት አልመለሱም። በተጨማሪም የሚኒስቴሩን ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ባለሙያ ስለ መምህራኑ ቅሬታ ከገለፅንላቸው በኋላ የሚመለክተውን ክፍል አገናኛችኋለው ብለው ቢመልሱም ከዛ በኋላ ባለሙያዋን ማግኘት አልተቻለም።

ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው መረጃ ካለ በቀጣይ አዲስ ዘይቤ ይዛ ትመለሳለች። 

በመቐለ፣ አክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ይሰሩ የነበሩ መምህራን በደሞዝ አለመከፈል እና ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት ምደባ አለመደረጉ ለችግር ዳርጎናል አሉ። መምህራኑ ከሦስት እስከ አምስት ወርታ ለሚደርስ ጊዜ ደሞዝ ያለመከፈል፣ ምክንያቱ ሳይታወቅ የተቆራረጠ ደሞዝ በወራት ልዩነት መግባቱን ገልፀዋል። አሁንም በስራ ላይ የሚገኙት መምህራን ለቤት ኪራይ፣ ትራንስፖርት እና ለእለት ወጪዎች በብድር እየተጨናነቁ መሆኑን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

አስተያየት