የካቲት 11 ፣ 2014

የዕንባ ጠባቂ ተቋም ከሚቀርቡለት ቅሬታዎች 60% ያህሉ እንደማይመለከቱት ተናገረ

City: Dire Dawaፖለቲካማህበራዊ ጉዳዮች

ተቋሙ በ10 ዓመት ቆይታው 1ሺህ 5መቶ አቤቱታዎች ቀርበውለታል።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የዕንባ ጠባቂ ተቋም ከሚቀርቡለት ቅሬታዎች 60% ያህሉ እንደማይመለከቱት ተናገረ

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ የጀመረው በ2004 ዓ.ም. መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ተቋሙ በ10 ዓመት ቆይታው 1ሺህ 5መቶ አቤቱታዎች ቀርበውለታል። ከቀረቡለት ቅሬታዎች መካከል ግማሽ ያህሉ እልባት ያገኙ ሲሆን ከአጠቃላይ ቅሬታዎቹ 60 በመቶ ያህሉ የተቋሙን ሥልጣን እና ኃላፊነት ያልተረዱ ስለመሆናቸው ተነግሯል። የተቋሙ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዓለማየሁ አድማሱ “ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠባቸው፣ ሐገራዊ ውሳኔ የሚጠይቁ፣ በሕግ ምርመራ ላይ ያሉ፣ በምክር ቤት ውሳኔ የተሰጠባቸው፣ የወታደራዊ ተቋማት ውሳኔዎች፣ በኦዲተር ቢሮ የተያዙ፣ እንዲሁም የግል (የባልና ሚስት፣ የጎረቤት) ጉዳዮችን ተቋማችን አይመለከትም” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይላሉ ቡድን መሪው “ይሁን እንጂ የዕንባ ጠባቂ ተቋሙን ሥልጣንና ኃላፊነት ባለመረዳት ወደ ተቋሙ የሚመጡት ጉዳዮች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውና ተቋሙን የማይመለከቱ ናቸው”

በድሬዳዋ አስተዳደር የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ቃል አቀባይ ወ/ሮ አረጋሽ ንጉሥ ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ሲያብራሩ “አስተዳደራዊ በደል ሲፈጸም ህብረተሰቡ መብቱን እንዲጠይቅ ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነት የመንግሥት ነው” ብለዋል። ቢሮው ግንዛቤውን ለመፍጠር ልዩ ልዩ መንገዶች እንደሚጠቀምም ነግረውናል። “የመጀመሪያው የተለያዩ ጥያቄዎች በማዘጋጀት ወደ ዘጠኙም ቀበሌ እንበትናለን። ቀበሌዎቹ የደረሳቸውን መጠይቅ አስሞልተው መልሰው ይልኩታል። ይህ ሂደት ያለብንን ክፍተት እንድናውቅ ያግዘናል። ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን የት ቦታ ማዘጋጀት እንደሚገባ እንድንወስን ግብአት ይሆነናል” ብለዋል ቃልአቀባይዋ

በድሬደዋ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት የዜና እና ፕሮግራም አዘጋጅ ከነዓን ዮናስ “ለማኅበረሰብ ጠቃሚ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነት የመገናኛ ብዚኃን ነው” ይላል። እንደ ጋዜጠኛው ገለጻ በሰራተኛ እና በተቋማት መካከል በአስተዳደራዊ በደል ምክንያት የሚፈጠር ቅሬታ ቢኖር እዚያው ተቋም ውስጥ በሚገኙ የቅሬታ አፈታት ሂደቶች ለመፍታት ጥረት ይደረጋል። “ሂደቱን የመረዳት ኃላፊነት የራሱ የሰራተኛው ነው። ምክንያቱም መጀመሪያ ሲቀጠር መብትና ግዴታው ተነግሮት፣ ፈርሞ ነው። በተጨማሪም በሁሉም ተቋማት ላይ ብዙ ጊዜ ልብ የማይባሉ ግድዳ ላይ የሚጻፉ ጉዳዮች መካከል ቅሬታ ቢፈጠር ለማን አቤት ማለት እደሚገባ የሚጠቁሙ መልእክቶች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ለሁሉም ተገልጋይና ለሁሉም የቅሬታ ዓይነት ይጠቅማሉ ማለት አይቻልም። በየክልሉ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን አንዱ ኃላፊነታቸው አስተማሪና መረጃ ሰጪ የሆኑ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ነው” ይላል። የሚድያ ባለሙያዎች በሚፈጠሩ ቅሬታዎችና የአፈታት መንገዳቸው ላይ ዘገባ ወይም ፕሮግራም የሚሰሩት በስፖንሰር መሆኑ ጉዳዩ ትኩረት እንዳይሰጠው ስለማድረጉም ይናገራል።

በኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዓለማየሁ አድማሱ በበኩላቸው ችግሩን ለመቅረፍ ተቋሙ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞችን ጨምሮ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ባሉባቸው ክልሎች ተደማጭ በሆኑ የራድዮ ጣቢያዎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን የሬድዮ ፕሮግራሞች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ ይጀምራል። ይህ የሬድዮ ፕሮግራም መጀመሩ ዜጎች ወደተቋሙ የሚመጡትን ጉዳዮች እንዲለዩ፣ ማኅበረሰቡ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ተግባርና ኃላፊነት ምን እንደሆነ እንዲረዳ፣ መብቱን የሚጠይቅ ማኅበረሰብ በመፍጠር ቅሬታዎች ባክነው እንዳይቀሩ ማድረግ፣ ቅሬታዎች በወቅቱ እንዲፈቱ ማስቻል እንደሆነ  ተናግሯል። ከዚህም ባለፈ በየጊዜው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብሮች እንደሚዘረጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሕገ-መንግስቱ እና በሎሎች ሕጎች የተጠበቁ የዜጎች መብቶች በመንግሥት አስፈፃሚ አካላት እንዳይጣሱ ለመከላከልና ለማስጠበቅ በአዋጅ ቁጥር 211/1992 ተቋቁሟል። መገለጫዎቹ የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነት፣ ቅልጥፍና፣ እና ግልፅነት ያለበት ተግባር እንዲሰፍን ለማድረግ የታለሙ ስልጣንና ተግባራት ተሰጥቶታል። ከተሰጡት ስልጣኖች መካከልም አስተዳደራዊ በደልን አስመልክቶ የሚቀርብ ቅሬትን መመርመርና መፍትሄ መፈለግ አንዱ ነው። በአዋጅ ቁጥር 590/2000 መሰረት ደግሞ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅን ማስፈፀም እንዲሁም ሕብረተሰቡ ስለመልካም አስተዳደር መርሆች እና ስለ ሕግ የበላይነት ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ይገኙበታል።

አስተያየት