የካቲት 11 ፣ 2014

አስደንጋጩ የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብል (ፖስት ፒል) አጠቃቀም

City: Adamaጤና

በሳምንቱ መጨረሻ የእረፍት ቀናት እና በበዓላት ሰሞን ከፍተኛ ሽያጭ የሚያስመዘግበው ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብል ‘ፖስት ፒል’ ሽያጭ በቫለንታይን ደይ ማግስት ባሉ ሁለት ቀናት ከፍ ያለ ሽያጭ እንደሚያስመዘግብ ተሰምቷል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አስደንጋጩ የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብል (ፖስት ፒል) አጠቃቀም
Camera Icon

Credit: Social Media

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በፌብሯሪ ወር በ14ኛው ቀን የካቲት 7 በሚከበረው የ“ቫለንታይን” ቀን የስጦታ ዕቃዎች ሽያጭ የሚያሻቅብበት መሆኑ ይታወቃል። በዓለም ዙርያ በሚገኙ ጥንዶች በድምቀት የሚከበረው ዓመታዊ በዓል ሬስቶራንቶችና መዝናኛ ስፍራዎች የሚጨናነቁበት ነው። ሽያጫቸው ከሚጨምር ምርቶች መካከል የተፈጥሮ አበባ፣ ቸኮሌት፣ አሻንጉሊት እና ሌሎችም ጌጣጌጦች ይገኙበታል። ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያዎችም በተለይ ከበዓሉ ቀን ማግስት ጀምሮ ባሉት ቀናት ተፈላጊነታቸው እንደሚጨምር የወፍ በረር ምልከታዎች ያሳያሉ። 

በሳምንቱ መጨረሻ የእረፍት ቀናት እና በበዓላት ሰሞን ከፍተኛ ሽያጭ የሚያስመዘግበው ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብል ‘ፖስት ፒል’ ሽያጭ በቫለንታይን ደይ ማግስት ባሉ ሁለት ቀናት ከፍ ያለ ሽያጭ እንደሚያስመዘግብ ተሰምቷል። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችው ርኆቦት ፈጣን ምግቦች የሚሸጡበት መደብር መጸዳጃ ቤት ከ3 በላይ የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብል ካርቶኖች መመልከቷን ነግራናለች። አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የመድኃኒት መደብር ባለቤቶች እና አከፋፋዮች የያዝነው ሳምንት ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ሽያጭ የሚጨምርበት መሆኑን አረጋግጠዋል።

መድኃኒቶችን ከአስመጪዎች ተቀበሎ በጅምላ የሚያከፋፍል ድርጅት ውስጥ የምታገለግለው ፍሬሕይወት አጥላው ከዚህ በፊት በ500 ብር ከአቅራቢ ድርጅቱ የሚረከቡትን ምርት 610 ብር ስለመግዛታቸውና የዚህም ምክንያት የወቅቱ ተፈላጊነት መሆኑን ነግራናለች። "አንዱ ካርቶን 20 እሽግ  ይይዛል። ሌላ ጊዜ 10 የሚወስዱ ደንበኞቻችን እስከ 15 እና 20 ካርቶን ድረስ ወስደዋል። በፍቅረኛሞች ቀን ሰሞን እንደ ‘ፖስት ፒል’ እና ‘ሜላወን’ የመሰሉ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ፍላጎት የሚጨምርበት ነው” ብላናለች።

ባሳለፍነው ሳምንት አዳማ የሚገኙም ሆነ ከአዳማ ውጭ ያሉ የመድኃኒት መደብሮች የተረከቧቸው የ‹ፖስት ፒል› እንክብሎች መጠን ከሌላ ጊዜው እንደጨመረ ነግራናለች።

በአዳማ ከተማ አዳማ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኝ የመድኃኒት መደብር ያገኘነው ፋርማሲስት እንዳለ ግርማ ይባላል። በቫለንታይን ዴይ ማግስት ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን ጠዋት ስራ ከጀመሩበት ሰዓት እስከ  ማታ ሰዓት ባለው ጊዜ 20 ሰዎች እንክብሉን እንደገዙ ነግሮናል። የገዢዎች ቁጥር መጨመር ምክንያትም ከ1 ቀን በፊት የተከበረው የፍቅረኛሞች ቀን (ቫለንታይን ዴይ) ስለመሆኑ ይናገራል። በፍቅረኛሞች ቀን ማግሥት የመድኃኒቱ ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ 80 ብር ቢደርስም በፍጥነት ተሸጦ መጠናቀቁን ነግሮናል።

ሌላዋ የፋርማሲ ባለሙያ በምስትሰራበት መደብር ከ6 እስከ 12 ሰዓት ባለው የሥራ ሰዓቷ ለ10 ደንበኞች እንክብሉን ስለመሸጧ ትናገራለች። “በመደበኛው ቀን ምንም ላይሸጥ ይችላል። ከፍተኛ ሽያጭ ከተባለ እንኳን ከ (3-5) ቢሆን ነው። የዚህ ቀን ሽያጭ ግን ከእጥፍ በላይ ከፍ ያለ ነው” ያለችን ሲሆን አብዛኛዎቹ ገዢዎች ወጣቶች መሆናቸውን እና ስለ ጥቅሙ እንጂ ስለሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ምንም ዐይነት ግንዛቤ እንደሌላቸው መታዘቧን ጨምራ ተናግራለች። “በሳምንት ወይም በ15 ቀን ልዩነት የድንገተኛ መከላከያ እንክብሉን ለመግዛት የሚመጡ ደንበኞች አጋጥመውኛል” ያለች ሲሆን፤ ወጣቶቹ ምክር ለመስማት ጊዜውም ፍላጎቱም እንደማይኖራቸው ትናገራለች።

“ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል” የሚለው ስሙን መግለጽ ያልፈለገ መድኃኒት አከፋፋይ ነው። ለአዳማ እና አካባቢዋ መድኃኒት በማከፋፈል ስራ ላይ የተሰማራው ወጣቱ “ፋርማሲዎች ትክክለኛውን መረጃ ስለማይናገሩ እንጂ፤ ቁጥሩ ከተጠቀሰውም በላይ ነው” የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል። ትክክለኛውን ዳታ ለማግኘት ጥልቀት ያለው ጥናት መካሄድ እንደሚገባውና በፋርማሲዎች የወፍ በረር መረጃ ብቻ ድምዳሜ ላይ መድረስ አስቸጋሪ መሆኑን በማንሳት አጽንኦት ሰጥቶበታል።

“በፍቅረኞች ቀን የሚኖረው የእንክብሉ ፍላጎት ከመደበኛው ፍላጎት ቀን መጨመሩ እውነት ነው" የሚለው ወጣቱ እንክብሉ ሕጋዊ መስመርን ተከትለው ወደ ሐገር ውስጥ ከሚገቡት በተጨማሪ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሐገር ውስጥ በስፋት ከሚገቡት ተፈላጊ መድኃኒቶች መካከል እንደሆነም አንስቷል።

የፋርማሲ ባለሙያዋ ትእግስት ሙላቱ በበኩሏ እንክብሉ አለአግባብ ከተወሰደ የወር አበባ ዑደትን ከማስተጓጎሉም በላይ መካንነት ሊያስከትል እንደሚችል ተናግራለች።

"ድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብሎች በተደጋጋሚ ሲወሰዱ የሆርሞን መዛባትን በማስከተል የወር አበባ ማስተጓጎል፣ ማህጸን እርግዝና እንዳይዝ በማድረግ እስከ መካንነት የሚያደርስ ጉዳት የሚያስከትል ተጽዕኖ አላቸው" የምትለው ፋርማሲስቷ ሴቷ ዋነኛ ተጎጂ በመሆኗ የምትጠቀምባቸውን የእርግዝና መከላከያ ዐይነቶች በጥንቃቄ መምረጥ እንደሚገባት ትመክራለች።

የስነ-ተዋልዶ ጤና ባለሙያዋ ሰባህ ነዚም “አካሄዱ አደገኛ ነው” ትላለች። እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ‹ፖስት ፒል› ድንገተኛ እንጂ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ አይደለም። ተደጋግሞ የሚወሰድ ከሆነም የሚያስከለው የጎንዮሽ ጉዳት አለ። የብልት መድማት፣ የማህጸን ጽንስን መሸከም አለመቻል ከሚያስከትላቸው ዘላቂ የጤና ጉዳቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

“ሌሎቹ የወሊድ መከላከያ መንገዶች የተዘነጉ ይመስላል” ያለን የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያው የጤና መኮንን ማንያዘዋል እስጢፋኖስ ነው። “በተለይ ወጣቶች ከቅድመ ጥንቃቄ ይልቅ የድህረ-እርምጃዎች ላይ አተኩረዋል። የሚፈሩት እርግዝናን ብቻ ነው። የሚጠነቀቁት እንዳያረግዙ ብቻ ነው። ይህ መሆኑ የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብሎችን ሽያጭ ብቻ ሳይሆን ኤች.አይ.ቪን ጨምሮ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን ስርጭትም ጨምሯል” ብሏል።

የአዳማ ከተማ ጤና ጽ/ቤት ባልደረባ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደስ አለኝ የጤና መኮንን ማንያዘዋልን ሐሳብ ያጠናክራሉ። ያሉ ሲሆን በተጨማተሪም “ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ጨምሯል ወይም ቀንሷል ለማለት ግን በቁጥር የተደገፈ ዳታ ሊኖር ይገባል። ሽያጩ ሴንትራላይዝ ባለመሆኑ ያስቸግራል። በዙርያችን በምንመለከተው እንናገር ከተባለ ግን ጨምራል” ብለዋል።

ዶ/ር ታሪኩ ገላሼ በሙሴ ጠቅላላ ሆስፒታል የሚሰሩ ጠቅላላ ሐኪም ናቸው። “የፖስት ፒል አጠቃቀም ‘መረን የለቀቀ ነው’ የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በጥናት ላይ የተደገፈ መረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል” ብለውናል። “ማንኛውም መድኃኒት ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በተገቢው ሐኪም ሊታዘዝ፣ በታዘዘው መሰረት ሊወሰድ ይገባል። መድኃኒት መደብር ውስጥም ሆነ በቤት ውስጥ ሲቀመጥ በአምራች ድርጅቱ በተፈቀደው የአየር ንብረት እና እርጥበት ሊሆን ይገባል። እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉ የመድኃኒቱ ፈዋሽነት ሊቀንስ፣ ታካሚውን የተወሳሰበ የጤና ችግር ውስጥ ሊከት የሚችልበት አጋጣሚ ከፍ ያለ ነው” የሚሉት ሀኪሙ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ከሆርሞን ጋር ግንኙነት ስላላቸው በዓመት በተደጋጋሚ ሊወሰዱ እንደማይገባ መክረዋል። የእንክብሎቹ በተደጋጋሚ መወሰድ ከማሕጸን ውጭ ለሚፈጠር እርግዝና ሊያጋልጥ እንደሚችል ያነሱት ዶክተሩ “የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ስሙ እንደሚያመለክተው ከብዙ ጊዜ አንድ ጊዜ በድንገት ለሚፈጠር ክስተት እንዲያገለግሉ እንጂ እንደ ቋሚ መከላከያ እንዲቆጠሩ አይመከርም” ሲሉ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

አስተያየት