የካቲት 9 ፣ 2014

ጦርነቱ በደቡብ ወሎ ዞን የውሃ አቅርቦት ላይ የደቀነው ፈተና

City: Dessieዜናወቅታዊ ጉዳዮች

በጦርነቱ ወቅት ወድመው በፍጥነት ወደ አገልግሎት ካልገቡት መካከል የውሃ አቅርቦት አንዱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ይመር “የውሃ ነገር አንገብጋቢ ነው። አፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልገዋል።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ጦርነቱ በደቡብ ወሎ ዞን የውሃ አቅርቦት ላይ የደቀነው ፈተና
Camera Icon

ፎቶ፡ ኢድሪስ አብዱ መሃመድ

ይመር አደም ይባላሉ። የሚተዳደሩት በግብርና ነው። በደሴ ዙሪያ ወረዳ የጉጉፍቱ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢያቸውን ነዋሪዎች የሚያገለግለው ቦኖ ውሃ አገልግሎት በማቋረጡ ለእንግልት እንደተዳረጉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ከመኖርያ ቤታቸው ከ100 ሜትር ባላነሰ ርቀት ላይ የነበረው የቦኖ ውሃ አሁን ከ4 ኪ.ሜ. በላይ ተጉዘውም ንጹህ የመጠጥ ውሃ የማያገኙበት ጊዜ እንዳለ ነግረውናል።

በጦርነቱ ወቅት ወድመው በፍጥነት ወደ አገልግሎት ካልገቡት መካከል የውሃ አቅርቦት አንዱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ይመር “የውሃ ነገር አንገብጋቢ ነው። አፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልገዋል። እኛም እንደ እንስሳቶቻችን ከወንዝ እየቀዳን ለመጠጣት ተገደናል” ይላሉ። በተለይ ህጻናት ልጆቻቸው በውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይጠቁ እንደሚሰጉም አጫውተውናል። እንደ አርሶአደር ይመር ገለጻ በቂ የህክምና አቅርቦት በሌለበት የውሃ እጥረት መኖሩ ለተወሳሰበ ችግር የሚዳርግበት ዕድል ሰፊ ነው።

“በተመሳሳይ ምክንያት ደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙ 15 ወረዳዎች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ውስጥ ወድቀዋል” የሚሉት የደቡብ ወሎ ዞን ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት መምሪያ ተወካይ ኃላፊ  አቶ ንጉሥ ተፈራ ናቸው። 

አቶ ንጉሥ ተፈራ

“ከጦርነቱ በፊት 14ሺህ 372 የገጠርና 88 የውሃ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ነበሩን” የሚሉት ኃላፊው በጦርነቱ 672 የገጠርና 56 የከተማ የውሃ ተቋማት በተለያየ ደረጃ ጉዳት ስለደረሰባቸው ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን ተናግረዋል። “37 የውሃ አገልግሎቶች እና 57 ተጠሪ የውሃ ተቋማት ዝርፊያና ውድመት ተፈጽሞባቸዋል” ብለዋል። ሁኔታው የዞኑን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ከ64 በመቶ ወደ 54 በመቶ እንዳወረደውም ለማወቅ ተችሏል።

ከ212 ሺህ በላይ የዞኑ ነዋሪዎች ንጽህናው ባልተጠበቀ ውሃ እንዲገለገሉ፣ ለውሃ ወለድ በሽታዎች ስጋት እንዲዳረጉ ምክንያት የሆነው ጉዳት ለጥገና 1.5 ቢልየን ብር በላይ እንደሚያስፈልገለው ተዘግቧል።

በጦርነት ወቅት የደረሰው ውድመትና ዘረፋ የዞኑን የንፁህ ውሃ ተደራሽነት ሽፋን ከ64 ከመቶ ወደ 54 ከመቶ ዝቅ እንዳወረደው ይናገራሉ። እንደ ኃላፊው ገለጻ “ችግሩ ለጤና ሴክተሩ ላይም ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። 80 ከመቶ በላይ የሚሆኑ በሽታዎች ውሃ ወለድ በመሆናቸው ይህ ከፍተኛ የጤና ስጋት ከመፍጠር ባለፈ እናቶችንና ህፃናትንም ውሃ ለማግኘት የሚደርስባቸውን እንግልት እንዲጨምር አደርጎታል” ሲሉ ኃላፊው ይናገራሉ። ቀውሱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ያሳደረ ሲሆን አሁን ላይ በወረዳዎቹ በተደረገ ጥናት ጉዳቶች ተጠቃለው ቀርበዋል። በጥገናም፣ እንደገና በመገንባትም ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል ያነጋገርናቸው አርሶ አደር ይመር አደም ሲጠቀሙበት የነበረው የባዮ ጋዝ ማብለያ ከባድ መሳሪያ ተመቶባቸው አሁን ከአገልግሎት ውጭ በመሆኑ የእንጨት ማገዶ እየተጠቀሙ በመሆኑ

“የባለቤቴንም የቤተሰቤንም ጤና የጠበቀው የባዮ ጋዝ መገልገያየ ወድሟል። አሁን በስተርጅና ለዳግም እንግልት ተዳርገናል። የሶላር መጠቀሚያዎቻችንን ሁሉ ወታደሮቹ ቤት ለቤት እየገቡ ወስደውብናል” ሲሉም ነግረውናል።

አቶ ንጉስ ተፈራ የውሃ ተቋማትን ማውደም ብቻ ሳይሆን ለውሃ ህክምና የሚውሉ ኬሚካሎች መለዋወጫና የጥገና መሳሪያዎች ሁሉ የዝርፊያው አካል ነበሩ ሲሉ ያስታውሳሉ። “በኢነርጂ ዘርፍም የብዙ አርሶ አደሮችን ሕይት ያሻሻሉና የእናቶችን ጤና የጠበቁ የባዮ ጋዝና ሶላር ቴክኖሎጅዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘረፋዎች ተፈፅመዋል። 8 ሺህ በጸሐይ ኃይል የሚሰሩ የአርሶ አደር መገልገያዎች ተዘርፈዋል፣ 22 የባዮ ጋዝ ማብላያ ተቋማት በወረኢሉና ጃማ ወረዳዎች በነበሩ ጦርነቶች በከባድ መሳሪያ ተመተዋል” ሱሉም ተወካይ ኃላፊው ይናገራሉ። ስራውን እንደገና ለማስጀመር የጠየቀው ወጭ ከፍተኛ በመሆኑ በአንድ ጊዜ አገልግሎቱን መጀመር አልቻልንም። አሁንም ቢሆን ግን ከ20 ከመቶ እስከ 60 በመቶ በሚሆን ደረጃ በአካባቢው መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማስተካከል እየሰራን ነው” ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ውሃ በቦቴ ከማቅረብ ጀኔሬተር እስከመደገፍና ውስን የሙያ ድጋፎችን ከማድረግ የዘለለ ድጋፍ አለማቅረቡን፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ዘርፉን ለመደገፍ ያደረጉት ጥረት በቂ አለመሆኑን፤… የሚናገሩት ተወካይ ኃላፊው በቀጣይ ጊዜያት ሁሉም ባለድርሻዎች ተረባርበው ችግር ውስጥ የገቡ አርሶ አደሮችን መታደግ ያስፈልጋልብለዋል።

አስተያየት