በሶማሌላንድ የተከሰተውን ግጭት በመሸሽ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑ ታወቀ። ግጭቱ ወደ አርስ በእርስ ጦርነት ከፍ ብሎ ዳፋው ለጎረቤት ሀገሮችም እንዳይተርፍ ተሰግቷል።
ከሁለት ወራት በፊት በኢትዮጵያ አጎራባቿ ሶማሌላንድ በስተደቡብ ክፍል 'ላሳአኖድ' በተባለችው ከተማ አቅራቢያ በመንግስትና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት በርካቶች ሲገደሉ ቁጥሩ ወደ 100 ሺህዎች የሚጠጋ ህዝብ ደግሞ ቀዬውን ለቆ ተፈናቅሏል። በርካቶቹም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አቋርጠው በመግባት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ተሰባስበዋል።
በርካታ ሴቶችና ሕፃናት ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን እየገቡ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ዋና ኮሚሽን ከሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት ላይ አስታወቆ ነበር። እስካሁንም በዞኑ ቦህ፣ ገልሃሙር እና ዳኖድ በተባሉ ሦስት ወረዳዎች አጠቃላይ ቁጥራቸው ከ90 ሺህ በላይ የሆኑ ስደተኞችን መመዝገቡን ኮምሽኑ አስታውቋል።
በሶማሌላንድ ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በደቡባዊ የሶል ግዛት ከተቀረው የሶማሌላንድ ክፍል ለመገንጠል በተነሱ ኃይሎችና ከሀገሪቱ ጦር ጋር በርዕሰ ከተማዋ በላሰአኖድ ከተማ የተነሳው ግጭት ከቀናት በፊት እንደ አዲስ ተቀስቅሶ በርካታ ህዝብ ከመኖሪያ ቀየው እየሸሸ ወደ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን እየተሰደዱ መሆኑንም አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የቦህ እና የዳኖን ወረዳ ለስደተኞች በበጎፈቃድ የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ላይ የሚገኙት ወጣት ሀሰን በሬ እና ኒማኣ አዳዌ ገልፀዋል።
ዛሬም ድረስ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ባልተቸራት ሶማሌላንድ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ ጦርነት አድጎ ዳፋው ለጎረቤት ሀገራት ሊተርፍ እንደሚችል የሚናገሩት በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍና ፖለቲካዊ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሱራፌል ጌታሁን፣ “የግጭቱ እንደ አዲስ መቀስቀስ በአገራችን ላይ ከኢኮኖሚው ይሁን ከፓለቲካው አንፃር ሊፈጥር የሚችለው ጫና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም” ይላሉ።
እንድምሁሩ ገለፃ በተለይ ግጭቱ በተቀሰቀሰበት አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ በቋንቋ፣ በባህል እንዲሁም በእምነትና በጎሳ ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ ግጭቱ ወደ ኢትዮጵያ ከዘለቀ ሊዛመት አለመቻሉን በእርግጠኝነት መናገር የሚችል አካል የለም።
ስለዚህም የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ተፋላሚ ወገኖች ነፍጣቸውን አስቀምጠው ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመምጣት ችግራቸውን በመፍታት በአፋጣኝ ሰላም እንዲያወርዱ መሰራት ይኖርበታል የሚሉት የዓለም አቀፍና ፖለተካዊ ሳይንስ ተመራማሪው ይህ ካልሆነ የከፋ ችግር እንደሚመጣ ይገልፃሉ።
በኢትዮጵያ በየአካባቢው ግጭትና መፈናቀል ባልቆመበት፣ ሱዳን አሁን ላይ በገባችበት ቀውስ፣ በደቡብ ሱዳን በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል ዳግም ግጭት ላለመቀስቀሱ ዋስትና መስጠት በማይቻልበት፣ ከ4 አስርት ዓመታት በላይ በሶማሊያ ያላባራው ጦርነት፣ በኬንያ እና በጅቡቲ መተማመኛ ለመስጥት በሚያዳግተው ሰላም ሳቢያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አካባቢ ምሰቅልቅሉን የሚያወጣ ሁኔታ እንይዳፈጠር በብዙዎች ዘንድ ስጋት አሳድሯል።
ሶማሌላንድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 1960 ከቀድሞዋ ቅኝ ገዢ እንግሊዝ ነፃ ብትወጣም እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ ከዋናዋ ሶማሊያ ጋር ተቀላቅላ ቆይታለች። ዳግም በ1991 ዓ.ም ነፃ ሀገር መሆኗን አውጃ ዛሬም ድረስ አንድም የዓለም ሀገር እውቅና ሳይሰጣት ራሷን በራሷ ማስተዳደሯን እንደቀጠለች አለች።