ሚያዝያ 16 ፣ 2015

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎቹ በስልክ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳሰበ

City: Mekelleወቅታዊ ጉዳዮች

ዩኒቨርሲቲው ከፌደራል መንግስት እስካሁን በጀት ባይመደብለትም ዳግም ሥራ ለመጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል

Avatar: Meseret Tsegay
መሰረት ፀጋይ

መሰረት ፀጋይ በጋዜጠኝነት ስራ ልምድ ያላት ሲሆን የአዲስ ዘይቤ የመቀሌ ከተማ ዘጋቢ ናት።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎቹ በስልክ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳሰበ

በሰሜኑ ጦርነት ውድመት የደረሰበትና ከ35 ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የነበረው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከጦርነቱ በኋላ ስራ ለማስጀመር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በነበረው ጦርነት ሳቢያ ለዓመታት የመማር ማስተማር ስራውን ያቋረጠው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ አሁን የጥገና እና የመረጃ ማጣራት ስራዎችን እየሰራሁ ነው ብሏል።

በጥር ወር 2013 ዓ.ም መከላከያ ሰራዊት መቀሌ መግባቱን ተከትሎ በጊዜያዊ አስተዳደር አማካኝነት መደበኛ ትምህርት ማስተማር ጀምሮ የነበረው ዩኒቨርሲቲው የጦርነቱን ማገርሸት ተክትሎ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቋረጥ የግድ ሆኗል።

የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍል ምክትል ኃላፊ ሳሙኤል ክፋሌ (ዶ/ር) ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የጥገና፣ የበጀት ማስተካከል እና የአእምሮ ማነቃቂያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

ከ8ሺ በላይ ሰራተኞች ያሉት ዩኒቨርሲቲው በተለይም ያልተከፈለ ደመወዝ መኖሩ የተገለፀ ሲሆን የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ግን የአራት ወራት ደመወዝ ስለመከፈሉ ከዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲው ከጦርነቱ በፊት አንደኛ ዓመት የነበሩና ያቋረጡ ተማሪዎች በስልክ መረጃቸውን እንዲሰጡ ማስታወቂያ አውጥቷል። ከሚያዝያ 16 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ስም፣ የትምህርት ክፍልና ስንተኛ ዓመት እንደነበሩ በስልክ መግልጽ እንዳለባቸው ለተማሪዎች አሳስቧል። 

በተጨማሪም በሌሎች ዩኒቨርስቲ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎችም ሲማሩበት የነበረውን ተቋም እንዲያሳውቁ አሳስቧል። የዩንቨርሲቲው ሰራተኞች ሪፖርት እንዲያደርጉ መመሪያ መዘጋጀቱን እና ለመልሶ ማደራጀት ስራው የሰርቪስ ተሽከርካሪዎች ጥገና እየተደረገላቸው ነው ተብሏል። ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው በትክክል ስራ የሚጀምርበት ቀንም ሆነ ወር አልተገለፀም።  

በትግራይ ክልል የትምህርት ሁኔታን በተመለከተ ለመምከር በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የተመራ የፌደራል የልዑካን ቡድን በመቀሌ ቆይታ ማድረጉ ይታወሳል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የበጀት እጥረት ማጋጠሙ በተገለፀበት በዚህ ወቅት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን ስራ ለማስጀመር በፌደራል መንግስት የተመደበ በጀት አለመኖሩን አዲስ ዘይቤ ያገኘችው መረጃ ያመለከታል።

አስተያየት