በጎንደር ከተማ የሸቀጦችን ዋጋ ለማረጋጋት የተቋቋሙ 34 የሸማቾች ማኅበራት እንደሚገኙ ከከተማዋ ሕብረት ስራ ማኅበር ማስፋፊያ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከማኅበራቱ መካከል 22 ያህሉ “ራስ ዳሽን ዩኒየን” በሚል ስያሜ በጋራ ይንቀሳቀሳሉ። የሸማቾች ማኅበራቱ በቦርድ የሚመሩና ዓመታዊ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን የግብርና ምርቶቹን ከገበሬው፣ የፋብሪካ ምርቶችን ከፋብሪካው በቀጥታና በቅናሽ ወደ መሸጫ መደብሮቻቸው አስመጥተው ለአባሎቻቸው በቅናሽ ዋጋ ያቀርባሉ።
ማኅበራቱ ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የ10 ሚሊየን ብር ብድር ማግኘታቸው ተሰምቷል። ብድሩ ገበያውን እንደሚያረጋጋ ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል። በኮቪድ ወረርሽኝ እና በጦርነቱ ምክንያት የተቀዛቀዘውን እና የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እየሰሩ እንደሆነ የሚናገሩት የጎንደር የሕብረት ስራ ማኅበር ማስፋፊያ ጽ/ቤት ኃላፊ የሺዓለም ጎበዜ “የምግብ ሸቀጦችን ለማኅበራቱ ያከፋፈልነው በእጅ በእጅ ሽያጭ ብቻ አይደለም” ይላሉ። “በሁለት ወራት በሚመለስ ዱቤ ለሠላሳ አራቱም ማኅበራት አዳርሰናል። የእኛ ዋጋ ከሌሎች የሽያጭ ቦታዎች ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ቅናሽ አለው” ብለዋል። ተጽእኖውንም ለመገምገም ሳምንታዊ የገበያ ጥናት እና ግምገማ ስለማካሄዳቸውና የተሻለ የዋጋ መረጋጋት ዕንደታየ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሰንበት ገበያን ለማስጀመር በሂደት ላይ እንሚገኙ ሰምተናል። “የእሁድ ገበያ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል። ለተግባራዊነቱ 90 በመቶ የዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀዋል” ብለውናል። በገጠሩ አካባቢ የሚኖሩትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለማኅበሩ እንዲያስረክቡና ከማህበሩ እንዲሸምቱ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።
ማኅበራቱ ይህንን ይበሉ እንጂ ጥቂት የማይባሉ የከተማዋ ነዋሪዎች የዋጋ መረጋጋት ተፈጥሯል በሚለው ሐሳብ አይስማሙም። “የማኅበራቱ መደብር የት እንደሚገኝ አናውቅም” ከሚሉት ጀምሮ እንደ ዘይት እና ስኳር ያሉ ምርቶች ወደ ገበያተኛው ሳይሆን በቀጥታ ወደ ቸርቻሪው ነጋዴ ይተላለፋሉ፣ ምርቶቹ የሚመጡበት እና የሚጠፉበት ጊዜ አይታቀቅም የሚሉ ቅሬታዎች ይሰነዘራሉ።
የጎንደር ከተማ ንግድና ገቢያ ልማት የመምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በከተማዋ ከ17ሺህ በላይ ነጋዴዎች በዘርፉ ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልዖአል። በከተማዋ የታየው የዋጋ ንረት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር እንዳሻቀበና ይህንንም ለመቀነስ ቢሮው ያዋቀረው ኮሚቴ እንቅቃሴ በማድረግ ላይ እንሚገኝ አንስቷል። ሕጋዊ መስመርን ሳይከተሉ ወደ ሐገር ውስጥ የገቡ የኮንትሮባንድ ምርቶችን መቀነስም ከኮሚቴው ተቀዳሚ ተግባራት መካከል አንዱ ስለመሆኑ ሰምተናል።
ከ2ሺህ በላይ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው፣ የሸማቾችን ሕግ የተላለፉ 17 ግለሰቦች ክስ እንደተመሰረተባቸው ቢሮው አስታውቋል። እየተወሰደ በሚገኘው እርምጃም ከ94 በመቶ በላይ ጉድለቶችን ማስተካከል ተችሏል ተብሏል። የጎዳና ላይ ንግድን ለመከላከልም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞችን ተሞኩሮ በመውሰድ የእሁድ ገበያን ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁ ተነግሯል። በተጨማሪም የሰዓት እላፊ ገበያ (ከሥራ ሰዓት ውጭ የሚከናወን) እና የመስሪያ ቦታ ማዘጋጀት ገበያውን እንደሚያረጋጉ በማመን በቅርብ ጊዜያት የሚከናወኑ እቅዶች ናቸው ተብሏል።